እሑድ 28 ዲሴምበር 2014

ገዥው ፓርቲ ባህርዳር ላይ  የግዳጅ ሰልፍ ሊጠራ ነው።

ታኀሳስ ፲፯(አስራ ሰባትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ   ከቀናት በፊት በባህርዳር የተካሄደውንና  ምእመናን የተገደሉበትን የተቃውሞ ሰልፍ – የሚቃወም  ሌላ የግዳጅ ሰልፍ  ሊጠራ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች  ገለጹ።
እንደ ምንጮች ገለጻ በግዳጁ ሰልፍ የማይገኝ የባህርዳር ነዋሪ ቅጣት ይጣልበታል ተብሏል።
ገዥው ፓርቲ በአማራ ክልል አስተዳደር ባህር ዳር ከተማ የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውን የታቦት ማደሪያ ለመንገድና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች መስሪያ እንዲነጠቅ ማዘዙን ተከትሎ የባህር ዳር  ህዝበ-ክርስቲያን የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በሰልፉ ሰላማዊ ሰዎች ከመገደላቸውም ባሻገር በርካቶች መጎዳታቸው በምእመናኑ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ቅሬታ  በቀሰቀሰበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ፓርቲ ቀደም ሲል የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ የሚቃወም  ሌላ የድጋፍ ሰልፍ ሊጠራ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል።
መንግስት ታህሳስ 9/2007 ዓ.ም የተደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞ የ‹‹ፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ እንዳለበት›› በመግለጽ ‹‹ህገ-ወጥ ሰልፍ›› ማለቱ  ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት  ባህር ዳር ከተማ የሚገኙት የቀበሌ ካድሬዎች የኢህአዴግን የግዳጅ ሰልፍ ለማሳካት   እያስተባበሩ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቀበሌ ካድሬዎች በየ ቤቱ እየሄዱ የነዋሪዎችን ስም በመመዝገብ በሰልፉ የማይሳተፍ ሰው ቅጣት እንደሚጠብቀው እያስጠነቀቁ  እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የግዳጅ ሰልፉ ታህሳስ 21 ወይንም 22 ቀን 2007 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በ15 ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችን ሊያደርግ ነው

ታኀሳስ ፲፯(አስራ ሰባትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ያወጣውን ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩን ታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ይፋ ሲያደርግ፣ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩም ለ2 ወራት የሚቆይ እንደሚሆን አስታውቋል።
የትብብሩ አመራሮች በሰማያዊ ጽ/ቤት የሰጡትን  መግለጫ ተንተርሶ ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው በሁለተኛ ዙር የትብብሩ መርሃ ግብር መሰረት የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 የሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ላይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ይደረጋሉ።  በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በባህር ዳርና በአዳማ ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚደረጉ የትብብሩና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢ/ር) በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡
ይህን የሁለተኛ ዙር የሁለት ወር ዕቅድ ከታህሳስ 16 እስከ የካቲት 15 /2007 አውጥቶ በቀዳሚነት ለዋነኛ ባለቤቶቹና ፈጻሚዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሲያቀርብ እንደመጀመሪያው ዙር ከጎኑ እንደሚቆሙ ሙሉ እምነት በማሳደር ነው›› ያለው መግለጫው፣ በትብብሩ በኩል በአመራር ከፊት ቆመው ትግሉን ለመምራት ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መኖሩን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል።
የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ለእንቅስቃሴው ማስፈጸሚያ 1 ሚሊየን 200 መቶ 15 ሺህ  ብር በጀት አጽድቋል። በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ ትብብሩ ጥሪውን  አስተላልፏል፡፡

ዓርብ 26 ዲሴምበር 2014

ምርጫ ቦርድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ሊያካሂድ ላቀደው ብሔራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ በዛሬው ዕለት ጀመረ፡፡

ታኀሳስ ፲፮(አስራ ስድስትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በየምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤቶች ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም ምዝገባ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ቢሆንም አንድነትና መኢአድ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ጋር ከገቡት አሰጥ አገባ ጋር ተያዞ በምርጫው የመቀጠላቸው ነገር አጠራጣሪ መሆኑ ታውቆአል፡፡
አንድነት እና መኢአድ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ወስነው የምርጫ ምልክት ለቦርዱ ካስገቡት  ፓርቲዎች መካከል ሲሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ያቀረቡትን ምልክት ላይ ለመወሰን ያላሟሉት የሕግ ጉዳይ አለ በሚል ሰሞኑን መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች አላሟሉም ከተባሉት መካከል አንዱ በፓርቲዎቹ ውስጥ ከተፈጠረ ውዝግብ ጋር ተያይዞ ትክክለኛ አመራሮቻቸውን አላሳወቁም ፣ የምርጫ ሕጉንና ሕገደንባቸውን አላከበሩም የሚለው የምርጫ ቦርድ ክስ ይገኝበታል፡፡ ፓርቲዎቹ ይህንን ችግር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አስተካክለው እንዲቀርቡ ቦርዱ ታህሰስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ወስኖአል፡፡
በዚህም ውዝግብ ምክንያት ፓርቲዎቹ ለአምስት ሳምንት ገደማ በሚቆየው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች ምዝገባ ብቁ አይደሉም በሚል ከወዲሁ ሊሰርዛቸው ይችላል የሚል ግምት መኖሩን ምንጮቻችን ዋቢ በማድረግ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጿል፡፡ ቦርዱ በአሁኑ ሰዓት ከፓርቲዎቹ ጋር እየተጻጻፈ ያለው ደብዳቤ በኃላ ለሚወስደው እርምጃ ሕጋዊነት ለማላበስ ታቅዶ መሆኑን ምጮቻችን አስታውሰው ፓርቲዎቹ ሕግና ስርዓትን አላከበሩም በሚል ከምርጫው በማስወገድ ኢህአዴግ ከጥቂት አጃቢ ታማኝ ፓርቲዎች ጋር ለምርጫው ሊቀርብ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃ /ማርያም ደሳለኝ በምርጫ የሚፎካከሩዋቸውን ፓርቲዎች በሶስት መደቦች በመክፈልና ቀይ እና ቢጫ ካርድ የተሰጣቸው እንዳሉ በመግለጽ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ሰሞኑን ማስተላለፋቸው ኢህአዴግ ለነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳልተዘጋጀ የሚያሳይ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ታህሳስ 12/ 2007 ዓ.ም የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ “በሀገራችን የምርጫ ቦርድ አለ ወይ” እንዲል አድርጎታል በማለት አንድነት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
የታህሳሱ 12 “የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ነፃና ገልልተኛ አልነበረም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የምርጫ ህጉን ተከተሎ ያልተካሄደ ሌላው ይቅርና የራሱ የምርጫ ቦርድ መመሪያን እንኳን ያልተከተለ ከመሆኑ አንፃር ተካሄዷል ብለን አናምንም” ሲል ፓርቲው አስታውቋል።
ህዝቡ በምርጫ ቦርድ በእኩል በይፋ የስብሰባ ጥሪ ያልተደረገለት መሆኑ፣  ፓርቲው ባሰማረባቸው የምርጫ ጣቢያ ቦታዎች ከሞላ ጎደል በአንድ ለአምስት ስርዓቱ ካደራጃቸው የራሱ አባላትና ደጋፊዎች በስተቀር ሌላው ህዝብ ሳያውቅ የተካሄደው መሆኑ፣  ከአስር ሺዎች በላይ ነዋሪ ያለባቸው አከባቢዎች ሀምሳ እና መቶ ሰው በተገኘባቸው አዳራሾች መካሄዳቸውን በችግርነት አንስቷል።
በመላ ሀገሪቱ የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ የተሰማሩ አባሎቻቸው በፀጥታ ኃይሎች ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን፤  በበርካታ አከባቢዎች ምንም ዓይነት ምርጫ ያልተካሄደ መሆኑ ፤ በ2002 ምርጫ ታዛቢ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ ለዘንድሮው የ2007 ምርጫም ታዛቢ እንዲሆኑ በጅምላ እንዲፀድቅላቸው መደረጉ በተለይም በአከባቢው የሌሉና የሞቱ ሰዎችም ጭምር የህዝብ ታዛቢ ሆነው የተመረጡበት ሁኔታ መፈጠሩ በተጨማሪ ችግርነት ተገልጿል።
በዘንድሮ የሚካሄደው የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ተኣማኒ እንደማይሆን ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ነው የሚለው አንድነት፣  ኢህአዴግንና ምርጫ ቦርድን እያጋለጠ በህዝባዊ ንቅናቄ ህዝቡን አደራጅቶ ትግሉን በቆራጥነት ይቀጥላል ሲል መግለጫውን ደምድሟል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደሴ ዙሪያ የሚገኙ ቀበሌዎች ህዝቡ ኢህአዴግን እንደሚመርጥ ቃል የሚገባባትን ፎርም እንዲሞላ እየተገደደ ነው። ፎርሙን ያልሞላ ከማንኛውም ጥቅም እንደሚገለል የተገለጸ ሲሆን፣ አንዴ ፎርሙን የሞላ ሰው በሁዋላ ላይ መቀየር እንደማይችል ተገልጾለታል።

አየር ሃይል እየታመሰ መሆኑን ምንጮች ገለጹ


ታኀሳስ ፲፬(አስራ አራትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የአየር ሃይል ባልደረባ የሆኑት ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ ከበረራ ቴክኒሻኑ ጸጋ ብርሃን ግደይ ጋር በጋራ በመሆን የሚያበሩትን ሄሊኮፕተር ይዘው ከጠፉ በሁዋላ የአየር ሃይል አዛዦች አስቸኳይ ግምገማ ከተጠሩ በሁዋላ እርስ በርስ እየተገማገሙና ከእነዚህ ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው የሚያስቡትን የአየር ሃይል አባላት ለማሰር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በተለይም የትግራይ ተወላጅ ከሆኑት ሻምበል ሳሙኤል ግዴይና ቴክኒሻኑ ጸጋ ብርሃን ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቻው የተባሉ ሰዎች እየተጠሩ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል። የመከላከያ ሚኒስትር ሻምበል ሳሙኤል ግደይን ከሃዲ ሲል ሲፈርጀው፣ መቶ አለቃ በልልኝ ደሳለኝንና ቴኒኪሻን ጸጋ ብርሃንን ደግሞ ተገደው መብረራቸውን ገልጿል።

የኢሳት ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ከፍተኛ የበረራ ልምድ ያላቸው ሻምበል ሳሙኤል የህወሃት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ አየር ሃይል ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ከሚቃወሙት የትግራይ ተወላጆች መካከል አንዱ ነው። መቶ አለቃ ቢልልኝ ደግሞ በአየር ሃይል ውስጥ የተስፋፋውን ዘረኝነት ከሚኮንኑ አብራሪዎች መካከል መሆኑ ታውቋል። በ2 ሺ ዓም አየር ሃይልን የተቃለቀለው መቶ አለቃ ቢልልኝ ሱዳን ውስጥና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሄሊኮፕተር በማብረር ብቻውን የተለያዩ ግዳጆችን መወጣቱን ምንጮች ገልጸዋል። ሁሉም ስርዓቱን በመቃወም ጥለው የጠፉ እንጅ፣ መንግስት እንዳለው አንዱ  ሌላውን አስገድዶ እንዲጠፋ አለማድረጉን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግስት አብራሪዎቹ ሄሊኮፕተሩን ኤርትራ አሳርፈውታል የሚል መግለጫ ቢሰጥም፣ የኤርትራ መንግስት ምንም መግለጫ አልሰጠም። ኢሳት ሄሊኮፕተሩ የት እንዳረፈ ለማወቅ ያደረገው ሙከራም እስካሁን አልተሳካለትም። በአየር ሃይል አዛዦች ውስጥ የተፈጠረውን ትርምስ ተከትሎ ኮሎኔል አበበ ተካና በብርጋዴር ጄኔራል ማሾ ሃጎስ እርስ በርስ መወነጃጀል ጀምረዋል።
ኮሎኔል አበባ ተካ በህወሃት መሪዎች ዘንድ የሚወደዱ በመሆናቸው አየር ሃይልን ከጀርባ ሆነው እስካሁን ሲመሩት ቆይተዋል። አለቃቸው ብርጋዴር ጄኔራል ማሾ ሃጎስ ደግሞ ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር በሚፈጥሩት አለመግባባት የተነሳ  ስልጣን ሳይኖራቸው  በስም ብቻ ተንሳፈው የሚኖሩ ናቸው። ብርጋዴር ጄኔራል ማሾ ቀደም ብሎ ከአየር ሃይል አዛዡ ሞላ ሃይለማርያም ጋር ከፍተኛ ጸብ ውስጥ ገብተው የነበር ሲሆን፣ ከኢታማጆር ሹሙ ሳሞራ የኑስ ጋርም ያላቸው ልዩነት እየሰፋ ሄዶ እርስ በርስ ማውራት ማቆማቸው ይነጋራል። ከጄ/ል ማሾ ጋር በእኩል ደረጃ የነበሩ ወታደራዊ  አዛዦች ቀድመዋቸው የጄኔራልነት ማእረግ ሲሰጣቸው እርሳቸው ግን ከሁለት ጊዜ በላይ እንደታለፉና  በቅርቡ በተደጋጋሚ ባሰሙት ቅሬታና ህወሃትን ከመከፋፈል ለማዳን በሚል ምክንያት የብርጋዴር ጄኔራልነት ማእረግ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።
ጄ/ል ማሾ በሲነየርቲ ከፍተኛ የማእረግ ደረጃ ላይ መድረስ የነበረብኝ ቢሆንም፣ ከጓደኞቹ እንዳንስ ያደረገኝ ጄ/ል ሳሞራ በሚያደርስብኝ በደል ነው በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያሰሙና ከስራቸው እየቀሩ በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው እንደሚውሉ የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። ጄ/ል ማሾ ቦታውን በስም ብቻ እንዲይዙ ተደርጎ ዋናውን የበረራ ስምሪት የሚያካሂዱት ኮ/ል አበበ መሆናቸው ፣ ኮሎኔል አበበን በሚደግፉት በእነ ሳሞራ እና በጄ/ል ማሾ መካከል ያለው ውዝግብ እንዲሰፋ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
ኮ/ል አበባ ተካ አየር ሃይልን በተለይም የድሬዳዋን አየር ምድብ ማዘዝ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አየር ሃይሉን ጥለው የሚጠፉ አብራሪዎች ተበራክተዋል። ባለፉት 6 ወራት ብቻ 11  አብራሪዎች አየር ሃይልን ጥለው በመጥፋት ግንቦት7ትና አርበኞች ግንባርን  ተቀላቅለዋል። አብዛኞቹ ለመጥፋታቸው ከሚሰጡዋቸው ምክንያቶች መካከል ዘረኝነት፣  የተበላሸ አስተዳደራዊ አሰራር መኖርና በአገሪቱ የሚታየው የመብት አፈና  የሚሉት ናቸው።
የአየር ሃይል ምንጮች እንደሚሉት ኮ/ል አበበ ተካ የውቅሮ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በድሬዳዋ ምድብ ውስጥ ያሉ የሃላፊነት ቦታዎችን በውቅሮ ልጆች ብቻ እንዲሞሉ አድርገዋል። ቀደም ብሎ የአየር ሃይል አዛዥ የነበሩት አበበ ተክለሃይማኖት በተመሳሳይ የውቅሮ ልጅ ሲሆኑ፣ ኮ/ል አበበን አሁን ላሉበት ደረጃ ያደረሱዋቸው እርሳቸው መሆናቸውንም ምንጮች ይገልጻሉ። ኮ/ል አበበ አየር ሃይል እንዲዳከም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የተለያዩ አብራሪዎች ቢናገሩም፣ እስካሁን ድረስ ማንም ደፍሮ እርምጃ አልወሰደባቸውም። እርሳቸው ሃላፊ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ በ2001 ዓም ሃምሌ ወር ላይ 2 ኤፍ ኤፍ 260 የመሰረታዊ በረራ ማስተማሪያ ሄሊኮፕተሮች ተጋጭተዋል። እርሳቸው በሰጡት የተሳሳተ አመራር  2 ኤም አይ 35 ሄሊኮፕተሮች በአየር ላይ ተጋጭተው 6 አብራሪዎች አልቀዋል። አንድ ኤፍ ኤፍ ሄሊኮፕተር ደግሞ ሁርሶ ላይ ሞተር ጦፍቶበት የወደቀ ሲሆን፣ አብረራዎቹ እንደ እድል ተርፈዋል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች የኮ/ል አበበ የአመራር አሰጣጥ ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸው ቢታመንም፣ ለረጅም ጊዜ ጄ/ል ሞላ እንዳይገመገሙ አድርገዋቸው እንደቆዩ ጄ/ል ሞላ ሃላፊነቱን ከለቀቁ በሁዋላ ደግሞ ጄ/ል ሳሞራ እየተከላከሉላቸው ይገኛሉ።
ኮሎኔሉ አበበ በጦር ሄሊኮፕተሮች የኮንትሮባንድ እቃዎችን ወደ ድሬዳዋ እየጫኑ ከጄ/ል ሞላ ሃይለማርያም ጋር በመሆን ሲነግዱ እንደቆዩና ከፍተኛ የሆነ ሃብት እንዳከማቹ የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። በድሬዳዋ፣ አዲስ አበባና መቀሌ ሰፋፊ ቦታዎችና በአዲስ አበባም አንድ ትልቅ ፎቅ አሰርተዋል በማከራየት ላይ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ቸግሮች ጄ/ል ማሾ ኮሎኔል አበበን ለመክሰስ በቂ ምክንያቶች ቢሆኑላቸውም፣ ከላይ ባሉ ባለስልጣናት ድጋፍ በማጣታቸው እስካሁን ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም። ሰሞኑን የጠፉትን አብራሪዎች ከጄ/ል ማሾ ጋር ለማያያዝ የእነ ኮ/ል አበበ ደጋፊዎች ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ከጄ/ል ማሾ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም አላማቸውን ይደግፋሉ ያሉዋቸውን ሁሉ ለመምታት እየተንቀሳቀሱ ነው።
ኮ/ል አበበ ኢሳት ሊያነጋግራቸው ቢሞክርም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ይታወቃል። ብርጋዴር ጄነራል ማሾን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።f