ቅዳሜ 3 ሜይ 2014

በጎንደር ተኩሱ ቀጥሏል፣ በግጭቱ 6 ሰው ሞቷል

May 1, 2014

Update:

ፖሊስ በነዋሪዎቹ ላይ የወሰደው እርምጃ ያስቆጣው የጎንደር ህዝብ በቁጣ የአጸፋ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ከጎንደር የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በፖሊስ እርምጃ የተቆጡ ወጣቶች የፖሊስ መኪና በመሰባበር ላይ ናቸው ተብሏል፡፡ ህዝቡ በነቂስ እየወጣ ግጭቱ እየተባባሰ መሆኑንም ምንጫችን ጠቅሷል (ነገር-ኢትዮጵያ)

——————————
ነገረ-ኢትዮጵያ – ጎንደር ከተማ ውስጥ ቀበሌ 18 ልዩ ቦታ አርምጭሆ ሰፈር፣ ገንፎ ቁጭና ህዳሴ የተባሉ ሰፈሮች የከተማው አስተዳደር ‹‹ህገ ወጥ ሰፈራ ነው፡፡›› በሚል ቤቶችን ለማፍረስ መዘጋጀቱን ተከትሎ አፍራሾቹ ከህዝብ ጋር በፈጠሩት ግጭት ከ6 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸውንና መታሰራቸውን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ግጭቱ ከሶስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ የነበር ሲሆን ምንጫችን ደውሎ በሚነግረን ወቅት (ከቀኑ 6፡ 43) ተኩስ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎቹ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ትዕዛዝ በተላለፈበት ወቅት ህገ ወጥ አለመሆናቸውን፣ ካልሆነም መንግስት ቅያሬ ቦታና ጊዜ መስጠት እንዳለበት በመግለጽ አንለቅም ብለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዛሬው ቀን ግጭቱ የተነሳውም አፍራሾቹ እንዲፈርሱ የተወሰነባቸውን ቤቶች ቀለም በመቀባታቸውና ህዝቡም እንዳይቀቡ በመከልከሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በግጭቱ ፖሊስ፣ ፌደራልና ልዩ ኃይል የተሳተፈበት ሲሆን ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ የአካባቢው ወጣቶች ላይ ድብደባና እስራት እየፈጸሙባቸው እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ‹‹ወጣቶችን እንደ እንሰሳ በአንድ ገመድ አስረው እየደበደቧቸው ነው፡፡ ህዝብ በጅምላ እየታሰረ ይገኛል፡፡ ግጭቱ ቢያቆምም በአሁኑ ወቅት በሶስቱም ሰፈሮች ጥይት እየተተኮሰ ነው›› ያሉት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች የተወሰደው እርምጃ የጎንደርን ህዝብ በማስቆጣቱ ከዚህ የባሰ ግጭት እንዳይፈጠር ያሰጋል ሲሉም ገልጸውልናል፡፡ በግጭቱ ወቅት የመጀመሪያዋ የሞት ሰለባ የሆነችው ልዩ ኃይል ቤቷ እንዲፈርስ ቀለም ሲቀባ የተቃወመች የልጆች እናት እንደሆነችም ታውቋ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ