ቅዳሜ 28 ፌብሩዋሪ 2015

በደህንነቶች የታፈነው አቶ ዘሪሁን ገሰሰ እስካሁን የት እንዳለ አልታወቀም

በደህንነቶች የታፈነው አቶ ዘሪሁን ገሰሰ እስካሁን የት እንዳለ አልታወቀም

February 23, 2015
(ነገረ-ኢትዮጵያ) የቀድሞው አንድነት የኮምቦልቻ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪና የአካባቢው የምርጫ እጩ አቶ ዘሪሁን ገሰሰ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 14/2007 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ኮምቦልቻ በማምራት ላይ እንዳለ ሸዋሮቢት ላይ በደህንነቶች መታፈኑ የታወቀ ሲሆን እስካሁንም የት እንዳለ አለመታወቁን ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አቶ ዘሪሁን ቀደም ሲል ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን አትችሉም፡፡ ለትግስቱ አወሉ እውቅና ካልሰጣችሁ እናስገርፋችኋለን›› እየተባሉ ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ያለህን ግንኙነት አቁም፡፡ በዚህ ሶስት ቀን ውስጥ ለቅቀህ ውጣ፡፡ በስልክ ከማንም ጋር እንዳታወራ፡፡ የነገርንህንም ለማንም መንገር የለብህም›› ተብያለሁ ሲል አቶ ዘሪሁን ጫና ይደረግበት እንደነበር ለነገረ ኢትዮጵያ መግለጹ ይታወሳል፡፡
አቶ ዘሪሁን በትራንስፖርት ውስጥ ከአዲስ አበባ አብረውት በተሳፈሩ የደህንነት ሰዎች ሸዋሮቢት ላይ ታፍኖ ለጊዜው በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ቆይታ አድርጎ የነበር ቢሆንም ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን ቤተሰቦቹ ከፖሊስ ጣቢያ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ሸዋሮቢት ሄደን ዘሪሁንን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ፖሊሶች እንደነገሩን ከሆነ ዘሪሁን ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል፡፡ አዲስ አበባ የት ቦታ እንደወሰዱት ግን አላወቅንም፡፡ ፖሊስን ለምን ለሲቪል ሰዎች አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ስንላቸው ‹እኛ ምን እናድርግ የበላይ ትዕዛዝ ነው፡፡ የደህንነት ሰዎች መሆናቸውን መታወቂያ አሳይተውናል› አሉን፡፡ አሁን እኛ ወደ አዲስ አበባ ሄደን ለማጣራት ጉዞ ላይ ነን›› ስትል ባለቤቱ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግራለች፡

ሰበር ዜና – የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ


‹‹ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል›› በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ‹‹የሚያልፉት በዕጣ ነው›› የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ‹‹ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡›› ተብሏል፡፡Blue Party
ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡›› ብለዋል
ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የመኢአድ ከፍተኛ አመራር ራሳቸዉን ከፎርጅድ ምርጫ ማግለላቸዉን አሳወቁ::


አቶ አዳነ ጥላሁን የሰሜን ወሎ ዞን ሰብሳቢ እና የማዕከላዊ ስራ
አስፈጣሚ የሆኑት ሁሉን ነገር ወያኔ በግፍ በጠበጃ አፈሙዝ
በተቆጣጠረበት እና ርካሽ ፕሮፓጋንዳዉን በሴራ እያጀበ
በሚያከናዉንበት ሰአት በምርጫ መሳተፍ ለሕገ ወጥ እና
ለመግስታዊ ዉንብድናዉ እዉቅና ከመስጠት ባሻገር ለሕዝባዊ
እቢተኝነት የተዘጋጀዉን ሕዝብ ማዘናጋት ነዉ የሚሆነዉ ብለዋል::
በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ምርጫ ለመግባት የወያኔ ምርጫ ቦርድ
በትግላችን አወንታዊ በሆነ መልኩ መቀየር አለበት ሲሉ
ሃሳባቸዉን ገልፀዋል::
አቶ አዳነ መኢአድ በጠላቶቹ ዉርጅብኝ የያዘዉን ፅኑ አላማ
ከግብ ሳያደርስ ከትግል ሜዳ ይወጣል ማለት ዘበት ነዉ:: አሁን
ምንም እንኳን ሐቁ ሳይጠፋቸዉ ለማደኖቆር የሚጥሩ
ፀረ መኢአድ መሆን ፀረ ኢትዮጵያ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል
ብለዋል::

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተቃውሞ ሰልፉን አራዘመ

የካቲት ፲፰(አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲዎቹ ምርጫ ቦርድ የአባል ፓርቲዎችን ዕጩዎች ያለ አግባብ በመሰረዙና እስከዛሬ ድረስ ዕጩዎቻቸውን በዝርዝር ባለማሳወቁ ምክንያት ለየካቲት 22/2007 ዓ.ም በ15 ከተሞች ሊያደርጉ አስበው የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፋቸውን የትብብሩን ጸሃፊ አቶ አቶ ግርማ በቀለን ጠቅሶ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
አቶ ግርማ በቀለ ‹‹ምርጫ ቦርድ ዕጩዎችን እመዘግብበታለሁ ባለበት የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ዕጩዎቻችን በዝርዝር ሊያሳውቀን አልቻለም፡፡ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆንም፡፡ ከምንም በላይ ግን በዕጩዎች ስረዛና ወከባ በርካታ ጊዜ አጥፍቶብናል፡፡›› በማለት ሰልፉ የተሰረዘበትን ምክንያት ገልጸዋል።
ትብብሩ ሰልፉ የሚደረግበትን ቀን ወደፊት ለህዝብ እንደሚያሳውቅ ዋና ጸሃፊው ገልጸዋል፡፡

ዓርብ 6 ፌብሩዋሪ 2015

በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መከረ



ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም :-ህብረቱ ጥር 27፣2007 ዓም በብራሰልስ ቤልጂየም የአውሮፓ ህብረት ጽ/ቤት ውስጥ ለ3 ሰአታት ባደረገው የኢትዮጵያ የሰአብአዊ መብት ግምገማ በኦጋዴን ክልል እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃ የአውሮፓ ህብረትና አባል መንግስታት በዝምታ መመልከታቸውን ማብቃት አለበት የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ስብሰባውን ያዘጋጁት የህብረቱ የሶሻሊስትና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ጥምር ህብረት ፣ ውክልና አልባ ህዝቦች ተቆርቋሪ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
በስብሰባው ላይ የኦጋዴን ክልል ፕ/ት አማካሪ የነበረና በክልሉ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመረጃ በማጋለጥ ላይ የሚገኘው ወጣት አብዱላሂ ሃሰን፣ ተቀማጭነቱ በጄኔቫ የሆነ የአፍሪካ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባልደረባ፣ አቶ አብዱላሂ ሙሃመድ፣ የኦጋዴን ሴቶች ተወካይ ፣ ጋዜጠኛና የክሬት ትረስ ዳይሬክተር ግርሃም ፌብልስ፣ እንዲሁም በኦሮሞ ሴቶች ላይ የሚደረሰውን ሰቆቃ በማስመልከት ጥናት ያካሄዱት፣ ዶ/ርባሮ ቀኖ በቪዲዮ የተደገፈ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
እንግሊዛዊው ግራሃም ፌብልስ በኢትዮጵያ 2 አመታት ቆይታቸው የታዘቡትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተለይም በኦጋዴን ክልል በሴቶች ላይ ተፈጽሟል ያሉትን አስገድዶ መድፈር ወንጀል የታዳሚውን ስሜት በነካ መልኩ አቅርበዋል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዜጎች ላይ ሽብርን እያኬደ ነው ያሉት ሚ/ር ፌብልስ የዚህ ሶቆቃ ፈጻሚዎች፣ ከአውሮፓ ህበረትና መንግስታት በእያመቱ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙ መሆናቸው እጅግ የሚያሳዝነው ነው ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ተወካይ ዶ/ር ባዳል አህመድ እና አርበኞች ግንቦት7 ተወካይ አቶ አበበ ቦጋለ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው የሚሉትን የሰብአዊና የፖለቲካ መብቶች እረገጣና አስከፊ ሰቆቃ በእየተራ አቅርበዋል።
የአውሮፓ ህብረትን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና ጎሜዝና የእንግሊዝ የፓርላማ ተወካይ ወ/ሮ ጁሊ ዋርድ በየተራ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ከ60 በመቶ በላይ በጀቱን ከአውሮፓ ህበረት እየተቀበለ ዜጎች ላይ እየፈጸማቸው ያለው አስከፊ ሰቆቃዎችን አውሮፓ ካሁን በሁዋላ በዝምታ ማየት የለባትም ካሉ በሁዋላ፣ ኢትዮጵያኖች በአገራቸው እየተፈጸመ ያለውን አፈናና ጭቆና የውች ማህበረሰብ ያስቆምልናል ብለው ከመጠባበቅ ለራሳቸው ነጻነት ልዩነቶቻቸውን በማቻቻልና መለስተኛ ፕሮግራም በማዘጋጀት ህብረት ፈጥረው በአንድነት መታገልና ለለውጥ መነሳት አለባቸው ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው ምርጫ ላይ ታዛቢዎችን እንዳይልክ የወሰነው የኢህአዴግ መንግስት በየ5 አመቱ የሚያደርገውን የተሳሳተ ምርጫ በማጀብ ህጋዊነት ለማሰጠት እንደከዚህ በፊቱ ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆኑን ለመግለጽ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ህበረቱ በገጠመው የበጀት ችግር ምክንያት ታዛቢ አልክም ብሎአል ብሎ የጀመረው ቅስቀሳ መሰረተ ቢስና የተለመደ ህዝብን የማዘናጊያ ወሬ እንደሆነ ገልጸዋል። የአመቱን 60 በመቶ የሚሸፍን በጀት የሚሰጠው ህብረቱ፣ ኢትዮጵያን የመሰለ ስትራቴጂክ አገር፣ ህብረቱ የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል ብሎ ማሰብ ራስን እንደማታለል ይቆጠራል ብለዋል።
ህብረቱ ምርጫው ከመደረጉ ከሚቀጥለው ወር በፊት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችንና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በስፋት የሚያሳትፍ ትልቅ ጉባኤ በሚያዚያ ወር ላይ ለመጥራት በዝግጅት ላይ እንዳለ በዚህ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።
አንዳንድ የፓርላማ አባላት በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደግብጽ ህዝብ ሆ ብሎ በመነሳት ከመዒው ግንቦት ምርጫ በፊት አምባገነንነትን ከራሱ ትከሻ ላይ ለማውረድ መነሳት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀርብበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አቋሙን እንዲገልጽ ቢጋበዝም ፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነ ቤልጂየማዊ ዜጋ የሆነ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኛ  የተገኘ ሲሆን ስራውም መረጃ መሰብሰብ እንጅ አስተያየት መስጠት አለመሆኑን ገልጾ፣ ምንም ንግግር ሳያደርግ ወጥቷል።

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ በደረሰባቸው ድብደባና መድሀኒት ክልከላ ህይወታቸው አለፈ

ጥር ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም  :-የ9ኙ ፓርቲዎች በጠራው የአዳር ሰልፍ ታስረው የነበሩት  የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በእስር ቤት ሳሉ በደረሰባቸው ድብደባና መድሀኒት ክልከላ ህይወታቸው ማለፉን ነገረ-ኢትዮጰያ ዘገበ
የመላው አማራ አንድነት ድርጅት ምክትል ጸሀፊ የሆኑት መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የህዳር 27/28 የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በጠራው የአዳር ሰልፍ ላይ  ነው ክፉኛ  የተደበደቡት።
የስኳር ህመምተኛ የሆኑት  የመአህድ ምክትል ጸሀፊ ከደረሰባቸው የከፋ ድብደባ ባሻገርም   ወደ እስር ቤት ተወስደው  ለሶስት ተከታታይ ቀናት  መድሃኒት እንዳይገባላቸው መከልከላቸው  ለከፋ ህመም እንደዳረጋቸው ተገልጿል።
በድብዳባና  በእስር ቤት  መድሀኒት በመከልከላቸው ክፉኛ የታመሙት መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ፤ ከእስር ከተፈቱበት እለት  ጀምሮ ለሁለት ወር  በዘውዲቱ ሆስፒታል  ከቆዩ በኋላ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የስኳር ህመምተኛው መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ከደረሰባቸው ድብደባ ባሻገር ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡
የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ጥር 27/2007 ዓ.ም በቦሌ ሚካኤል እንደሚፈጸም ለማወቅ ተችሏል፡

Documentary:U.S Policy:ETHIOPIA A FAILED STATE!