ረቡዕ 11 ኖቬምበር 2015

ረሃቡና እድገታችን፡ ተጠያቂው ማን ነው? (በአብዱረዛቅ ሑሴን)

ክፍል አንድ፡ እድገቱን የጎሪጥ!
ምስራቅ አፍሪካ ላይ በዚህ አመት 22 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ እንደሚጠቁና ከዚያም ውስጥ 68% (15 ሚሊየኑ) ከኢትዮጵያ እንደሚሆን የተባበሩት መንግስታት እየተናገረ ይገኛል፡፡ መጀመሪያ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ፣ ከዚያም 4 ሚሊየን ቆየት ብሎ ደግሞ 8 ሚሊየን ህዝብ ተጠቂ እንደሆነ ዘግይተው ላመኑት ሹማምንቶቻችን ከፍተኛ ዱብ እዳ እንደሚሆንባቸው አያጠያይቅም፡፡ የሀገርም ውስጥ ይሆን አለም አቀፉ ህብረተሰብ አንድ ተመሳሳይ ጥያቄ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል፡- ‪ላለፉት‬ አስር አመታት በሁለት ዲጅት ያደገ ኢኮኖሚ እንዴት የህዝቡ 15% በረገብ ሊጠቃ ቻለ?15 million people in need of food aid
ለዚህ ጥያቄ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትራችን ያላቸውን የኢኮኖሚክስ እውቀት ተጠቅመው ቢያንስ መልስ ሚመስል ነገር ይሰጡን እንደነበረ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ እሳቸው ከነጎዱ ወዲህ ግን ‪‎ወይ‬ አያውቁ፣ ወይ የሚያውቁትን አያመጡ፣ ወይ አይወጡ; ሆኖብን እንጨት እንጨት የሚል የወረዱ ትንታኔዎቻችን የሚሰጡን ከጠቅላይ ሚንስተሩ እስከ ኮሚኒኬሽን ሚንስትሮቻቸው ድረስ ያሉ ባለስልጣናት ግራ አጋብተውናል፡፡ የዋጋ ግሽበት ፣የኑሮ ውድነቶችን እና የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት እጥረትን የመሳሰሉ ችግሮች ሲነሱ አቶ መለስ በተደጋጋሚ የእድገታችን ውጤት እንደሆነ ለኛም ለተተኪዎቻቸውም ሲነግሩን ነበር፡፡ ይህ ምላሽ መንግስትን ከተጠያቂነት ባያስመልጥም በከፊልም ቢሆን ኢኮኖሚክሲያዊ መሰረት ያለው ምሁራዊ ትንተና ሊባል የሚችል ነው፡፡ ከሳቸው መሞት በኋላ የመጡ መሪዎቻችን ለተመሳሳይ ጥያቄዎች ተመሳሳይ መልስን ሲሰጡን ቆይተዋል፡፡ ራእያቸውንም ብቻ ሳይሆን ለጥያቄዎች የሰጡትንም መልሶቻቸውን እያስቀጠሉም ይገኛሉ፡፡ ረሃብ ሀገራችንን ተለይቷት ባያውቅም በዚህ መጠን ግን የሁለት ዲጅት እድገት ትርክት ከተጀመረ ወዲህ ስላልተከሰተ የቀድሞውም ጠቅላይ ሚንስትር አልተጠየቁምም ለወራሾቻቸውም መልሱን አላስቀመጡም፡፡ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ሚዲያ ብቅ ያሉትም ባለስልጣናት ችግሩን ከመካድ፣ መጠኑን ከማስተባበልም አልፎ የወረዱ ምክንያቶችን ሲደረድሩ ታዝበናቸዋል፡፡ መልሽ ያጣውን ጥያቄ ዛሬ በከፊልም ቢሆን ለመመለስ እንሞክር፡፡
ረሃብ! ድሮና ዘንድሮ
የሰባ ሰባቱ ድርቅና ረሃብ ሀገራችንን አለም ፊት አንገት ያስደፋ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ የሆነን ረሃብና እልቂት አስከትሎ ነበር፡፡ ዶክተር እሌኒን የመሰሉ ምሁራን እንደሚሞግቱት በወቅቱ የሰሜኑ ክፍል በድርቅ ቢጠቃም በሌላው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ግን በቂ ምርት እንደነበረ ይገልፃሉ፡፡ ሀገሪቱ በዛ ወቅት ምርት ከተትረፈረፈበት ደቡብ እጥረት ወደተከሰተበት ሰሜን እንዲሄድ የሚያስችል በቂ የኢንፍራስትራክቸርና በተለይም የገበያ ተቅዋም አለመኖሩን ለችግሩ መባባስ እንደ ዋና ምክንያትም ያቀርባሉ፡፡ በሌላ አባባል በቂ የኢንፍራስትራክቸር ዝርጋታ ኖሮ በነበረና ምርትን ከፍላጎት ጋር ለማገናኘት የሚያስችል የገበያ መረብ ኖሮ በነበረ ድርቁ ያስከተለውን እልቂት መቀነስ ይቻል ነበር፡፡ ይህ ምልከታም በዶክተር እሌኒ መሪነት የተቋቋመውን የEthiopia Commodity Exchangeን ለመመስረት እንደ ዋነኛ መከራከሪያ ሆኖ በተለያዩ የጥናት ፅሁፎቻቸው ውስጥ ተካቶ እናየዋለን፡፡
አስከፊው የሰባ ሰባቱ እልቂት ከተከሰተ ከሰላሳ አመት በኋላም ይኸው ድርቅ አገሪቱን እያሳሰበ ይገኛል፡፡ እነ ዶክተር እሌኒ የሞገቱለት የኢንፍራስትራክቸርና የገበያ ተቋማት አለመኖር በፊት ከነበረው በእጅጉ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጥርጥር የለውም፡፡ የመንገዶችም ሆነ የኮሚኒኬሽን ኢንፍራስትራችቸሩ ከድሮው ጋር ሊወዳደር በማይችል መልኩ አድጓል፡፡ በሀገሪቱ በየትኛውም ቦታ የአቅርቦት እጥረት እናዳለና ተመጣጣኝ ትርፍ ሊገኝ እንደሚችል የሚያውቅ ነጋዴ ወሬውን ሰምቶ ተኝቶ ያድራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ወሬውን ለመስማት የሚያስችለው የኮሚኒኬሽን ኢንፍራስትራችቸርም ይሁን ምርቱን እጥረት ወደ አለበት ቦታ ወስዶ ለማትረፍ የሚያስችለው የትራስፖርት አማራጮች በብዙ እጥፍ ተሻሽለውለታል፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ረሃቡ በድጋሚ መከሰቱ እነ ዶክተር እሌኒ የዘነጉት ወይም ትኩረት ያልሰጡት ሌላ ተጨማሪ የረሃብ መንስኤ እንዳለ ያሳየናል፡፡ ይህም የህዝብ ወይም የመንግስት የመግዛት አቅምን ይመለከታል፡፡
ነጋዴው ያማሩ መንገዶችን ተጠቅሞ ትርፍ ምርት ካለበት ወደ እጥረት ወደተከሰተበት የሀገሪቱ ክፍል ምርቱን ቢያቀርብ ለረሃቡ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ በችግሩ የተጠቃው የህብረተሰብ ክፍል የምርት አቅርቦት ብቻም ሳይሆን የመግዛት አቅሙም ሊኖረው ይገባል፡፡ ምርቱ በድርቅ የረገፈበት ገበሬ በደህናው ጊዜ ተቀማጭ ሀብት እስካላፈራ ድረስ የምርት አቅርቦትን ማሻሻልና ማቀላጠፍ ብቻ በራሱ ችግሩን አይፈታውም፡፡ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ስለሆነና የመግዛት አቅሙም ስለማይኖረው ከመንግስት እርዳታን መከጀል ብቸኛ ምርጫው ይሆናል፡፡ መንግስት ፈርጣማ አቅሙን በመጠቀም ትርፍ ምርት ካለባቸው አካባቢዎችም ካልሆነም የውጭ ሀገራት ገዝቶ ተጠቂውን ህዝብ የመድረስ ግዴታ ይወድቅበታል፡፡ አሁን እንደሚታየው ከሆነ ግን ገበሬውም ለነገዬ ብሉ ያስቀመጠው ቅሪት ሳይኖረው በረሃብ አለንጋ እየተጠበሰ፤ መንግስትም ሲፎክርበት የነበረው ፈርጣማ አቅሙ በሞት አፋፍ ላይ ላሉት 15% ህዝቡ የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆን ያዳገተው ይመስላል፡፡ ላለፉት አስርት አመታት ተኣምራዊ እድገትን ስታድግ የነበረችው ኢትዮጵያ፤‪‎ግብርናን‬ መሰረት ያደረገ; የእድገት ስትራቴጂ እየተከተለች እንዳለች የምትነግረን ኢትዮጵያ፤ ገበሬዋ እራሱን መመገብ ሲያቅተውና መንግስቷም የክፉ ቀን ደራሽ መሆን ሲሳነው እድገቱን የጎሪጥ ብናየው ይፈረድብን ይሆን?

ቅዳሜ 7 ኖቬምበር 2015

ድል ለመቀዳጀት በአንድ ማሊያ መጫወት (ይገረም ዓለሙ)

ይገረም ዓለሙ

የላቀ የኳሽ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች በሀገራቸውም ሆነ ከሀገራቸው ውጪ በከፍተኛ ገንዘብ እየተሸጡ ይጫወታሉ፡፡ እነዚህ ዘር፣ቀለም ፤ኃይማኖትም ሆነ ቋንቋ ሳይገድባቸው በችሎታቸው ተመርጠው በየትኛውም የአለም ክፍል የሚጫወቱ ተጨዋቾች ገንዘብ የሚከፍላቸውን ቡድን የዋንጫ ባለድል ለማድረግ ለራሳቸውም ተዋቂነት ለማትረፍ በቁርጠኝነት ይጫወታሉ፡፡ የአንድ ሀገር ልጆች የተለያየ ማሊያ ለብሰው ለተለያዩ ቡድኖች ተሰልፈው ሲጫወቱ የተሰለፉለትን ቡድን ለአሸናፊነት ለማብቃት ይሻኮታሉ ይጎሻሸማሉ፡
አህጉራዊ ወይንም ዓለም አቀፋዊ ጨዋታ ሲኖር ግን ከየሄዱበት ተመልሰው ከተበታተኑበት ተሰባስበው በአንድ ማሊያ ለሀገራቸው ይሰለፋሉ፡፡ ለሀገራቸው ቡድን የመሰለፍ ምክንያታቸው በአሰልጣኙ መመረጣቸውና ሀገራቸው ችሎታቸውን መፈለጉ ብቻ ሳይሆን የእነርሱም ሀገራቸው አሸንፎ ባለ ድል አንዲሆን ከምር መፈለጋቸው ጭምር ነው፡፡ ባለፈው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ከአሸናፊነት ክብር ብር በልጦባቸው ከሀገራቸው አልፎ አፍሪቃን መሳቂያ ያደረጉትን ተጨዋቾች ሳንጨምር ነው ታዲያ፡፡
በዚህ ተምሳሌት የሀገራችንን ፖለቲካ ብንመለከተው ወያኔ በዚህ መንገድ በሚገባ እየተጠቀመበት መሆኑን እናያለን፡፡ ተቀዋሚው ግን….. ፡፡ ወያኔ አባል አጋር ሌላም በውል ስም ያልወጣላቸው ቡድኖችን አቋቁሞ በተለያየ ማሊያ የክልል ጨዋታውን ያካሄዳል፤ አምስት ዓመት ጠብቆ ሀገራዊው ጨዋታ ሲካሄድ ደግሞ ሁሉንም በአንድ ማሊያ በኢህአዴግ ስም ያሰልፋል፡፡
ወያኔ ማሊያ እየቀያየረ መጫወት የጀመረው በህውኃት ማሊያ ወደ ጎነደርና ወሎ መሸጋገር እንደማይቻል በተረዳበት ግዜ ነው፡፡እናም የአማራ ክልል የሚል ስያሜ በሰጠው የኢትዮጵያ ክፍል ለመረማመድ እንዲቻለው ኢህዴን ይባል የነበረውን ሕብረ- ብሔራዊ ድርጅት ስሙንም ዓላማውን አስለውጦ ብአዴን በሚል መጠሪያ የአማራነት ማሊያ አለበሰው፡፡ወያኔ ይህን ሲያደርግ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው የመታው፡፡ አንዱ በአማራ ክልል ለመረማመድ የሚያስችለው ቡድን መፍጠር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የማይፈልገውንና ለእቅዱ አንቅፋት አድርጎ የሚያየውን ሕብረ ብሄር ፓርቲ ማክሰም፤ ሀገራዊ አስተሳሰብን ማጥፋትና ዘረኝነትን ማስፋፋት ነው፡፡ ወደ ሸዋ ሲጠጋ ደግሞ እሱም ጋር ሻዕቢያም ዘንድ የነበሩ ኦሮምኛ ተናጋሪ ምርኮኞችን ሰብስቦ በኦሮምያ ውስጥ ለመረማመድ የሚያስችለውን የኦሮሚያ ማሊያ ለብሶ የሚጫወት ቡድን ( ኦህዴድን) ፈጠረ፡፡አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ የሱን ሥልጣን የሚያረጋጉና የሚያስጠብቁ ደኢህዴንና እና አጋር የሚባሉትን ቡድኖችን መፍጠሩን ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡
እነዚህ የተለያያ ማሊያ ለብሰው የተለያየ ቡድን ተመስለው የሚጫወቱ ቡድኖች የቡድን መሪያቸው አሰልጣኛቸው አስተዳዳሪያቸው ህወኃውት መሆኑን አሌ የሚል አይኖርም፡፡እናም ለዘወትሩ ጨዋታ በክልል ማሊያ እያሰለፈ በየአምስት ዓመት ለሚካሄደው ጨዋታ ደግሞ የኢህአዴግን ማሊያ እያሰለፈ ሀያ አራት አመት ሙሉ የዋንጫው ባለቤት እንደሆነ አለ፡፡
ይህን ጨዋታ ቅንጅትም ሞክሮት ውጤታማነቱን አሳይቷል፤ምርጫ 97 በአጃቢነት የምንገባበት፣ ለአድማቂነት የምንሰለፍበት ሳይሆን ከምር ተወዳድረን የምናሸንፍበት መሆን አለበት ያሉ ወገኖች ለማሸነፍ ደግሞ በተለያየ ስም ሆኖ የተለያያ ማሊያ ለብሶ ሳይሆን በአንድ ቡድን መደራጀት በአንድ ማሊያ መሰለፍ እንደሚስፈልግ ተናገሩ-ሰሩ፡፡ በዚህ ጥረትም አደረጃጀታው ሀገራዊ መገኛቸው ሀገር ቤት የሆኑ አራት ድርጅቶች ስማቸውን ቅንጅት ብለው ምልክታቸውን ሁለት ጣት አድርገው በአንድ ማሊያ ተሰልፈው መጫወት በመቻላቸው መቼም የማይረሳውንና መቼ ሊደገም እንደሚችል መተንበይ የማይቻለውን ውጤት አስገኙ፡፡
ይህ ከሆነ በኋላ ሁለት ምርጫዎች ተደርገው ተቀዋሚው እንደለመደው ጨዋታውን በተለያየ ማሊያ ማድረጉን በመቀጠሉ በአንዱ አንድ ወንበር ሲያገኝ በሁለተኛው ፓርላማውን ጨርሶ አስረክቧል፡፡ ሀገራዊ ውድድርን በአሸናፊነት ለመወጣት ካልሆነም ትንሽ ወንር ከፓርላማ ለማግኘት አንድ ቡድን መስርቶ በአንድ ማሊያ መጫወት ያለውን ጠቀሜታ ከወያኔ መማር ባይቻል ወይንም ባይፈለግ እንደምን ከቅንጅት መማር ይቸግራል፡፡
ለውጤታማነት በአንድ ማሊያ መጫወት የሚያስፈልገውና የሚጠቅመው በሀገር ቤት ለሚደረገው ትግል ብቻ አይደለም፡፡የትግሉ መነሻ ቦታ ኢትዮጵያም ይሁን አሜሪካ፣ ኤርትራም ይሁን በርበራ፣አሰብም ይሁን ሱዳን በሁሉም የሚፈለገው ውጤት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ከሆነ በአንድ ቡድን ተሰባስቦ አንድ ማሊያ ለብሶ አንድ ሀገራዊ ገዢ መርህ አንግቦ መጫወት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ እስካሁን በተመጣበት ሁኔታ የሚካሄድ ውድድር(ትግል) ይህን ያህል ቡድን እዛና እዚህ አለ ከመባል ባለፈ ብሎም አንድ ቡድን ብቻውን ለጨዋታ ሜዳ አይገባምና የወያኔ አጨዋች ከመሆን የዘለለ የሚፈይደው ነገር የለም፣ አለ ከተባለ እገሌ የዚህ ቡድን መሪ እገሌ የዛኛው ቡድን ሊቀመንበር እየተባሉ መኖርን ትግልም ድልም ላደረጉ ሰዎች የሥልጣን ጥም ርካታ ማስገኘቱ ብቻ ነው፡፡ የፓርቲ መሪነት ሥልጣን ሆኖ፡፡
ሀያ አራት አመት እጅግ ብዙ ነው፡፡ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሊመረን ይገባል፡፡በርግጥ ለውጥን ዓላማቸው አድርገው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሥረታ ከልብ አምነው ለዚህም ከምር ቆርጠው ለመታገል የወሰኑትና የፓርቲ ሊቀመንበር እየተባሉ መኖርን መነሻ ዓላማቸው መድረሻ ግባቸውም አድርገው የሚኖሩት ይለዩ፡፡ አንድ ቡድን መስርቶ በአንድ ማሊያ ተወዳደሮ የዋንጫ ባለቤት ላለመሆን ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው ቡድኖች ያላቸው የአደረጃጀት ፣ የጨዋት ስልት ፣የሚገኙበት ቦታ ወዘተ ልዩነት አሳማኝ አይደለም፡፡ ዋናው ምክንያት ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ያለመፈለግ ወይንም ቁርጠኝት ማጣት ነው፡፡ ለለውጥ በቁርጠኝነት የተሰለፈ ለለውጥ እንቅፋት ለሆኑ ችግሮች መፍትሄ ይፈልጋል እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ሰበቦችን ያስወግዳል እንጂ ልዩነትን ለማስፋት ሲማስን አያድርም፣በእያንዳንዱ ርምጃ ሰበብ እየፈለገ እንቅፋት አይፈጥርም፣ስለ ሀገራዊው ድል እንጂ ስለ እርሱ ቦታ አይጨነቅም፡፡
አንድ በግልጽ የሚታይ ነገር ላንሳ ጀነራል ከማል ገልቹና ጀነራል ሀይሉ ጎንፋ ሁለቱም ከወያኔ ከድተው አስመራ የገቡ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፡፡እዛ ደርሰው ግን በአንድ ቡድን ተሰልፈው አንድ ማሊያ (ኢትዮጵያዊ ቢቀር ኦሮሚያዊ)ለብሰው መጫወት ተስኖአቸው ተለያይተው በኦሮሞ ስም የተለያየ ቡድን መስርተው እንደሚገኙ ነው የሚሰማው፡፡ ለያዙት ማእረግ የበቁት ውትድርናውን መቼ ጀምረውት እንደሆነ ማስረጃ ባይኖረኝም እዚህ ማዕረግ እስኪደርሱ በቃልም በተግባርም፤ በክፍልም በመስክም ወዘተ ሰፊ ወታደራዊ እውቀት እንደቀሰሙና ልምድ እንዳካበቱ እሙን ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ከሀገር ቤት ብቻ አይደለም ከአውሮፓና አሜሪካ ጭምር ከፕሮፌሰር እስከ ጳጳስ ከምር ቆርጠው ትግሉ ቦታ ሲወርዱ ጀነራሎቹ አሥመራ ተቀምጠው እንኳን ከሌላው መተባበር ርስ በርሳቸውም መነጋገር አቁመው አመታት መቁጠራቸውን መስማት እንቆቅልሽ አይሆንም!
ከምር ራሳቸውን ለትግሉ የሰጡና ለሥልጣን ሳይሆን ለነጻነት የሚታገሉ ስራቸው ምስክር ነውና በተግባራቸው እንለያቸው በምንችለውም አንደግፋቸው ይጠናከሩ፡ከውጤት አልባው የአመታት ጉዞአቸው ተምረው ለመለወጥ ያልፈቀዱትና ትግሉን ለስማቸው መጠሪያ ብቻ አድርገውት የሚኖሩት እንደዚሁ በተግባራቸው ይለዩ ፡፡ የእነዚህ መኖር ለሀገራዊው ትግል ከሚጠቅም ይልቅ ጉዳት ናቸውና ድጋፍ እንነሳቸው፤ከመኖራችሁ አለመኖራችሁ ይሻላል ብለን በግልጽ እንንገራቸው፡፡
ለነገሩ ሀገር ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ፓርቲዎች በወያኔ ዘንድ ነው እንጂ አሉ የሚባሉት ቆሞ ያልጠቀመ ሞቶ ምን ሊጎዳ ብሎ ሕዝቡ ከሸኛቸው አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በውጪም በሚገኙት ላይ ይሄው መደገም አለበት፡፡ ሀገራዊውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለመወጣት በአንድ ማሊያ መጫወት በምንልበት በዚህ ሰዐት እንወክለዋለን በሚሉት የአንድ አካባቢ ሕዝብ ስም የተደራጁ ሁለትም ስድስትም ድርጅቶች ስም እንሰማለን፡፡ የድርጅቶቹ መስራቾች ሁሉም ሊቀመንበር መባል በመፈለጋቸው ነው፡፡ ብዙም አባል አንደሌላቸው ይታወቃል፤ደጋፊው ግን ምን ይባላል፡፡ ትግሉን ከምር ያዙት አለያም ተዉት ማለት አያስፈልግም ትላላችሁ፡፡
በመጨረሻም ሎሬትን እንጋራ
Loret Tsegaye Gabre-Medhin

የፓርላማው ድራማ (ይገረም ዓለሙ)

ይገረም ዓለሙ
ሙሉ በሙሉ በአብዮታዊ ዴሞክራቶች በመያዙ የተለየ ሀሳብ የማይሰማበት ሙት የሆነውን ፓርላማ ህይወት ያለው ለማስመሰል የተዘጋጀው ድራማ ማክሰኞ ጥቅምት 16/2008 መታየት ጀምሯል፡፡ ይህ የፓርላማ ድራማ ቤቴሌቭዥን እንደምናያቸው ድራማዎች ሰሞነኛውን ትኩሳት እየተከተለ በየሳምንቱ የሚጻፍና የሚዘጋጅ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ቀን ትዕይንት መሪ ተዋናይ ሆነው የቀረቡት ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከፓርላማው አባላት መካከል በተመረጡት ተዋንያን እየተጠየቁ በመመለስ ሲተውኑ ታይተዋል፡፡Hailemariam Desalegn in the TPLF parliament
ከቀደሙት ጠቅላይ ምኒስትር ጀምሮ ሲነገር እንጂ ሲተገበር የማይታየው ከተቀዋሚዎች ጋር አብሮ የመስራት ጉዳይ ለመጀመሪያው ቀን ድራማ ማድመቂያነት ከተመረጡት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ተባብሮ መስራት ማለት እንደ ተቀዋሚዎች በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ሀገራዊ መግባባት ከመፍጠር የሚጀምር እንደ ወያኔ ደግሞ እሱ በሚፈልገው ጉዳይ ሲፈልጋቸው ብቻ በመጥራት የሚገለጽ ነው፡፡ እንዲ ሆነናም በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ላይ ለማወያየት ምርጫ ቦርድ መዝግቦ ለሚያውቃቸው ፓርቲዎች በሙሉ መንግጨሥታቸው ሰነድና ደብዳቤ መላኩን የገለጹት አቶ ኃይለማሪያም ብዙዎቹ በስብሰባው ላይ ሲገኙ ጥቂቶች ውኃ የማይቋጥር ምክንያት በመስጠት አልተገኙም አሉ፡፡ ያልተገኙት ፓርቲዎች ያቀረቡት ምክንያት ውኃ የማይቋጥር ነው ያሉበትን ምክንያትም ሲያረዱ በሕጋዊ መንግድ የተመረጠ መንግሥት ስላልሆነ ከእርሱ ጋር አንነጋርም ማለታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለመሆኑ ጥሪያችንን ተቀብለው ብዙዎቹ ተገኝተዋል የተባሉት ፓርቲዎች የትኞቹና እነማን ናቸው፡፡ዝቅ ብለን እናያቸዋለን፡፡
የመሳሪያ ትግል የሚያካሂዱትን ድርጅቶች አስመልክቶም ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ለራሱም መሆን ካልቻለው ሻዕቢያ ጋር ሆነው የሚያመጡት ውጤት ስለማይኖር ጊዜያቸውን በከንቱ ባያባክኑ በማለት ምክር ለመስጠት የዳዳቸው አቶ ኃይለማሪያም አንዳንዶቹ እኮ ጭራሽ የሌሉ ናቸው በማለት ኦነግን ኦብነግንና የጋምቤላ ህዝቦች ንቅናቄን ጠቀሱ፡፡ ይቺ ገለጻ የቀረበችው በደራሲውና አዘጋጁ ስህተት ይሁን ወይንም በርሳቸው የጥናት ጉደለት ባይታወቅም ሁለት መልእክት ታስተላልፋለች፡፡ አንደኛ እነዚህ የተጠቀሱት ድርጅቶች ሰሞኑን ተባብረው ለመስራት የደረሱበት ስምምነት እነ አቶ ኃይለማያም ሰፈር የፈጠረው ነገር መኖሩን እንድንጠረጥር ያሚያደርግ ፣ ሁለተኛ ደግሞ በሰሜን በኩል ድምጻቸው የሚሰማው ድርጅቶች እነዚህ ብቻ አይደሉምና ለሌሎቹ መኖሮና ጠንካራ መሆን በዘወርዋራ እውቅና የሰጠ ነው፡፡
አቶ ኃይለማሪያም የአቶ መለስ ሌጋስ አስቀጣይ እንደመሆናቸው ስለ ድርጅቶቹ የተናገሩት ከርሳቸው የወሰዱትን ነው፡፡ አቶ መለስ ብረት አንስተው መንግሥታቸውን የሚታገሉ ድርጅቶችን አስመልክቶ ሲላቸው አጥፍተናቸዋል የሉም ሲሉ ሌላ ግዜ ደግሞ በግላቸው ብዙ ርቀት ሄደው ከድርጅቶቹ መሪዎች ጋር ለመገናኘትና ለመደራደር እንደጣሩ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ ወድመዋል ተደምስሰዋል የተባሉት ደርጅቶች በዚህ ቦታ እንዲህ አደረጉ ጥፋት አደረሱ የሚል ዜና ስንሰማ ኖረናል፡፡ የሉም በተባሉ ድርጅቶች ስምም ዜጎች እየተወነጀሉ ታስረዋል እየታሰሩም ነው፡፡ አቶ መለስ አይደለም የሀገር ውስጥ ተፋላሚዎችን ሶማሌ ተሻግረው አልሻባብን ድምጥማጡን አጥፍተነዋል ብለውንም ነበር፡፡
አቶ ኃይለማሪያም ባያስታውሱም እኛ አንረሳውም፡፡ አቶ መለስ ከርሳቸው ፍላጎት ውጪ ስንዝር መሄድ የማይችለውን ፓርላማ አስፍቅደው(ነግረው) እንዲህ አስታዋሽ አጥቶ የቀረውን ሰራዊት ሶማሊያ በላኩበት ወቅት የገጠማቸውን ተቃውሞ ዝም ለማሰኘት ሰራዊታችን አልሻባብን ደምስሶ አሁን የቀረው ቃርሚያ ብቻ ነው፣ ያንን አጠናቆ በቅርብ ቀን ይመለሳል ብለውን ነበር፡፡ ነገር ግን ይኸው እስካሁን አልሻባብም አልጠፋ ሰራዊቱም አልተመለሰ፡፡ እንደውም በተቃራኒው ወንድሞቻችን የአልሻባብ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ አቶ ኃለማሪያም እኔም አንደ መለስ ብለው በንቀት ስሜት የሉም ጠፍተዋል ስላሉዋቸው ድርጅቶች መረጃ ስለሌለኝ የምለው አይኖርም፤ የላችሁም የተባላችሁ መኖራችሁን አሳይዋቸውና አቶ ኃይለማሪም በዚህ አፋቸው ምን እንደሚሉ ለመስማት አብቁን የሚለው ግን መልእክቴ ነው፡፡
አቶ መለስ የሻዕቢያና ወያኔ ጸብና ፍቅር ለወላይታው ምኑ ነው ብለው ለአቶ ኃይለማሪያም አለነገሯቸው እንደሁ እንጂ ወያኔን አዲስ አበባ ያደረሰው ለራሱም የማይሆን ያሉት ሻዕቢያ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሌላው ኢትዮጵያዊ (የወያኔ ታጋይ ጭምር ) የማይታመን ሆኖ እስከ ተጣሉበት ግዜ ድረስ ቤተ መንግሥቱ ይጠበቅ የነበረው በሻዕቢያ ሰራዊት እንደነበረ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ስለሆነም አቶ ኃይለማሪያም ወያኔዎች ስለ ሻዕቢያ ዛሬ የሚሉትን ብቻ እየተቀበሉ መናገር ሳይሆን ትናንት ምን ይሉ ምንስ ያደርጉ እንደነበር የተጻፈ አንብበው የነበረ ጠይቀው ቢናገሩ ቢያንስ ጠቅላይ ምኒስትር ለሚለው ማዕረጋቸው( ይስሙላም ቢሆን) የሚመጥን ይሆናል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው አቶ ኃይለማሪያም ስለ አብሮ መስራት ሲናገሩ ምርጫ ቦርድ የመዘገባቸውን ፓርቲዎች በሙሉ ጠርተን አብዛኛዎቹ ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡ አብዛኛው የሚለው የጥቅል መጠሪያ ለወያኔም ለፓርቲዎቹም ለምርጫ ቦርድም እያገለገለ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በቁጥር ሲገለጹ እንጂ በስም ሲጠሩ አይሰማም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርጫ ቦርድ መዝገብ ላይ ሰፍረው የሚገኙት አንዳንዶቹ የሌሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ምርጫ ሲመጣ ብቻ ብቅ የሚሉና ለምርጫ የሚሰጣቸውን ገንዘብ ተቀብለው የአጃቢነት ሚናቸውን ተወጥተው ለአራት ዓመት የሚጠፉ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹም ፓርቲ ለመባል የሚያበቃ ቁመና የሌላቸው አቶ በረከት የፓርቲዎቹ ጥቅማቸው አልታይ ብሉአቸው ይሁን ስሜት ገፋፍቶአቸው ወይንም እውነት ተናንቆአቸው ባይታወቅም በመጽሀፋቸው የቤተሰብ ፓርቲ ሲሉ የገለጹዋቸው ናቸው ፡፡ በርግጥ ለመናገር አንዳንዶቹ ሊቀመንበር ተብሎ ከሚጠራው ሰው ቀጥሎ የሚጠራ ሶስትና አራት ሰው የሌላቸው በመሆኑ የቤተሰብ ፓርቲ የሚለውንም አያሟሉም፡፡ ብዙዎቹ ከተባሉት ከእነዚህ ስመ ፓርቲዎች ውስጥ ብዙዎቹን እንኳን ህብረተሰቡ ምርጫ ቦርድም አያውቃቸው፡፡ ድረ ገጹን ብትጎበኙ ቦርዱ ስለማያውቃቸው የተመዘገቡበትን ቀን መሙላት አቅቶት ቦታው ክፍት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ፤ብቻ ብዙዎች እየተባሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ይውላሉ፡፡እነዚህን በስም እየጠቀሱ መሪ የሚባሉትን ሰዎች ምንነትና ማንነት እያሳዩ መግለጽ የሚቻል ቢሆንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ የምርጫ ቦርድን ድረ ገጽ ከጎበኙ ሌላም ነገር ይታዘባሉ፣ ምርጫ የማስፈጸም ብቃት አለው ተብሎ ምስጋና የተዥጎደጎደለት ይህ ተቋም ድረ- ገጹን ወቅታዊ ማድረግ ተስኖት ከአስር ዓመት በፊት የነበረ መረጃ ነው የሚያገኙት፡፡
ፓርቲ ማለት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የህጋዊነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጠው ነው ካልተባለ በስተቀር ብዙዎች የሚባሉት ከወያኔ ዳረጎት እየተቀበሉ፤ በምርጫ ቦርድ መልካም ፈቃድ ፓርቲ እየተባሉ፤ በአዳማቂነትና በአጃቢነት የሚያገለግሉ፣ እንኳን አባል የተሟላ አመራር የሌላቸው ናቸውና ፓርቲ ሊባሉ የሚበቁ አይደሉም፡፡ መሪ ለሚባሉት ሰዎች ግን የእለት እንጀራም የሕይወት መንገድም ሆኖ እየጠቀማቸው ነው፡፡ በአንጻሩ ብዙም ባይሆን ለወያኔ ዕድሜ መርዘምም እየረዱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ኖሩም አልኖሩ “ተለበሰ ቀረ የደበሎ ቅዳጅ ”እንደሚባለው ናቸውና ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ እንደውም የማይቻል ሆኖ እንጂ አለመኖራቸው ይሻል ነበር፡፡
ሙቱን ፓርላማ ህይወት ያለው ለማስመሰል የተጀመረው ድራማ ደራሲና አዘጋጁ ሰልችቶአቸው እስካላቆሙት ድረስ በጀመረው መልኩ ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን እየተከተለ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የእኛም ማየትና መስማት ብሎም ከምናይ ከምንሰማው ተነስተን ብዕር ከወረቀት ማገናኘት እንዲሁ ይቀጥላል፡፡እስካላቆሙት ድረስ ያልኩት አቅጣጫ ለማስቀየሻ እየተባሉ በዚህ መልኩ የሚጀመሩ ጉዳዮች ሲዘልቁ ስለማይታይ ነው፡፡ደግሞስ የማስመሰል ስራ መች ብዙ መንገድ ያስኬዳል፡፡ይህ የፓርላማ ድራማ ቀልቡን የሚስበው ሰው ኖር ይሆን!!

ለጥቅምት 22 ሰማዕታት የመታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ (ነገረ ኢትዮጵያ) ለጥቅምት 22 ሰማዕታት የመታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ (ነገረ ኢትዮጵያ)

http://ecadforum.com/Amharic/wp-content/uploads/2015/11/semayawi-party-remembering.jpg?bd378dምርጫ 1997 ዓ.ምን ተከትሎ ጥቅምት 22/1998 ዓ.ም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀጥታ ትዕዛዝ በ‹‹ፀጥታ ሀይሎች›› በጭቃኔ ለተገደሉት ሰማዕታት እና ለቆሰሉት ኢትዮጵያውያን በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት መታሰቢያ ተደረገ፡፡ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ጥቅምት 22/1998 ዓ.ም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የገጠማቸውን በተለይም ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ያዩትንና የራሳቸውን ገጠመኝም አካፍለዋል፡፡
የፕሮግራሙ ተሳታፊዎቹ የተገደሉትን በክብር መቅበር እንዳልቻሉ እና ታፍሰው በተለያዩ እስር ቤቶች መታሰራቸውን አስታውሰዋል፡፡ አዛውንቶችንና ህፃናትን በጭካኔ ተገድለው ባንክ ሊዘርፉ ነው የተባለበትና የሥርዓቱን የህግና ሞራል የማይገድበው መሆኑን ያሳየበት ነውም ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ካለፈው ስህተቱ ሳይማር ዛሬም ለመግደል ዝግጁ እንደሆነ መቀጠሉንም ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥርዓቱ ወደ ባሰ አምባገነንነት በመግባቱም ትግሉን መቀላቀላቸውን ገልፀው፣ ዘላቂው አማራጭ የሰማዕታቱን የትግል መንፈስ ፅናት ይዞ መታገል ነው ብለዋል፡፡ እነሱ አላማ ያደረጉትን ተጉዘው በአንድነት የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ መወሰን እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በ1997 ዓ.ም በኋላ የሥርዓቱ ሁኔታ እየተባባሰ እንደመጣና ለዚህም ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ሥርዓቱ የሚያደርስብንን በደል ችለን ወደ ውስጥ የምናለቅስ መሆናችን ነው ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ይቅር የማይደረግለት ሆኖ፣ ፖለቲካው በመነታረክ መቀጠሉን ትክክል እንዳልሆነም ገልፀዋል፡፡
‹‹ሥርዓቱ ታሪክና የጋራ ነገር የላችሁም ብሎናል፡፡ መናናቅንና ሀይማኖትን ማቃለልን በተግባር አሳይቶናል፡፡ የወደፊት ኢትዮጵያ በእኛ እጅ እንድትሆን ከፈለግን የነበረውን የሀገራችን እሴት ማናናቅ የለብንም፡፡›› ያሉት ኢ/ር ይልቃል ኢትዮጵያውያን የገነቧቸው እሴቶች ሁሉ በወጣቱ ልብ ውስጥ ማደር እንዳለባቸው፣ ሰማዕታቱ የሞቱለት አላማና ኢትዮጵያውያን የገነቡት እሴት መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡