ይገረም ዓለሙ
የላቀ የኳሽ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች በሀገራቸውም ሆነ ከሀገራቸው ውጪ በከፍተኛ ገንዘብ እየተሸጡ ይጫወታሉ፡፡
እነዚህ ዘር፣ቀለም ፤ኃይማኖትም ሆነ ቋንቋ ሳይገድባቸው በችሎታቸው ተመርጠው በየትኛውም የአለም ክፍል የሚጫወቱ
ተጨዋቾች ገንዘብ የሚከፍላቸውን ቡድን የዋንጫ ባለድል ለማድረግ ለራሳቸውም ተዋቂነት ለማትረፍ በቁርጠኝነት
ይጫወታሉ፡፡ የአንድ ሀገር ልጆች የተለያየ ማሊያ ለብሰው ለተለያዩ ቡድኖች ተሰልፈው ሲጫወቱ የተሰለፉለትን ቡድን
ለአሸናፊነት ለማብቃት ይሻኮታሉ ይጎሻሸማሉ፡
አህጉራዊ ወይንም ዓለም አቀፋዊ ጨዋታ ሲኖር ግን ከየሄዱበት ተመልሰው ከተበታተኑበት ተሰባስበው በአንድ ማሊያ
ለሀገራቸው ይሰለፋሉ፡፡ ለሀገራቸው ቡድን የመሰለፍ ምክንያታቸው በአሰልጣኙ መመረጣቸውና ሀገራቸው ችሎታቸውን መፈለጉ
ብቻ ሳይሆን የእነርሱም ሀገራቸው አሸንፎ ባለ ድል አንዲሆን ከምር መፈለጋቸው ጭምር ነው፡፡ ባለፈው የዓለም ዋንጫ
የእግር ኳስ ውድድር ላይ ከአሸናፊነት ክብር ብር በልጦባቸው ከሀገራቸው አልፎ አፍሪቃን መሳቂያ ያደረጉትን
ተጨዋቾች ሳንጨምር ነው ታዲያ፡፡
በዚህ ተምሳሌት የሀገራችንን ፖለቲካ ብንመለከተው ወያኔ በዚህ መንገድ በሚገባ እየተጠቀመበት መሆኑን
እናያለን፡፡ ተቀዋሚው ግን….. ፡፡ ወያኔ አባል አጋር ሌላም በውል ስም ያልወጣላቸው ቡድኖችን አቋቁሞ በተለያየ
ማሊያ የክልል ጨዋታውን ያካሄዳል፤ አምስት ዓመት ጠብቆ ሀገራዊው ጨዋታ ሲካሄድ ደግሞ ሁሉንም በአንድ ማሊያ
በኢህአዴግ ስም ያሰልፋል፡፡
ወያኔ ማሊያ እየቀያየረ መጫወት የጀመረው በህውኃት ማሊያ ወደ ጎነደርና ወሎ መሸጋገር እንደማይቻል በተረዳበት
ግዜ ነው፡፡እናም የአማራ ክልል የሚል ስያሜ በሰጠው የኢትዮጵያ ክፍል ለመረማመድ እንዲቻለው ኢህዴን ይባል
የነበረውን ሕብረ- ብሔራዊ ድርጅት ስሙንም ዓላማውን አስለውጦ ብአዴን በሚል መጠሪያ የአማራነት ማሊያ
አለበሰው፡፡ወያኔ ይህን ሲያደርግ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው የመታው፡፡ አንዱ በአማራ ክልል ለመረማመድ
የሚያስችለው ቡድን መፍጠር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የማይፈልገውንና ለእቅዱ አንቅፋት አድርጎ የሚያየውን ሕብረ ብሄር
ፓርቲ ማክሰም፤ ሀገራዊ አስተሳሰብን ማጥፋትና ዘረኝነትን ማስፋፋት ነው፡፡ ወደ ሸዋ ሲጠጋ ደግሞ እሱም ጋር
ሻዕቢያም ዘንድ የነበሩ ኦሮምኛ ተናጋሪ ምርኮኞችን ሰብስቦ በኦሮምያ ውስጥ ለመረማመድ የሚያስችለውን የኦሮሚያ ማሊያ
ለብሶ የሚጫወት ቡድን ( ኦህዴድን) ፈጠረ፡፡አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ የሱን ሥልጣን የሚያረጋጉና
የሚያስጠብቁ ደኢህዴንና እና አጋር የሚባሉትን ቡድኖችን መፍጠሩን ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡
እነዚህ የተለያያ ማሊያ ለብሰው የተለያየ ቡድን ተመስለው የሚጫወቱ ቡድኖች የቡድን መሪያቸው አሰልጣኛቸው
አስተዳዳሪያቸው ህወኃውት መሆኑን አሌ የሚል አይኖርም፡፡እናም ለዘወትሩ ጨዋታ በክልል ማሊያ እያሰለፈ በየአምስት
ዓመት ለሚካሄደው ጨዋታ ደግሞ የኢህአዴግን ማሊያ እያሰለፈ ሀያ አራት አመት ሙሉ የዋንጫው ባለቤት እንደሆነ አለ፡፡
ይህን ጨዋታ ቅንጅትም ሞክሮት ውጤታማነቱን አሳይቷል፤ምርጫ 97 በአጃቢነት የምንገባበት፣ ለአድማቂነት
የምንሰለፍበት ሳይሆን ከምር ተወዳድረን የምናሸንፍበት መሆን አለበት ያሉ ወገኖች ለማሸነፍ ደግሞ በተለያየ ስም ሆኖ
የተለያያ ማሊያ ለብሶ ሳይሆን በአንድ ቡድን መደራጀት በአንድ ማሊያ መሰለፍ እንደሚስፈልግ ተናገሩ-ሰሩ፡፡ በዚህ
ጥረትም አደረጃጀታው ሀገራዊ መገኛቸው ሀገር ቤት የሆኑ አራት ድርጅቶች ስማቸውን ቅንጅት ብለው ምልክታቸውን ሁለት
ጣት አድርገው በአንድ ማሊያ ተሰልፈው መጫወት በመቻላቸው መቼም የማይረሳውንና መቼ ሊደገም እንደሚችል መተንበይ
የማይቻለውን ውጤት አስገኙ፡፡
ይህ ከሆነ በኋላ ሁለት ምርጫዎች ተደርገው ተቀዋሚው እንደለመደው ጨዋታውን በተለያየ ማሊያ ማድረጉን በመቀጠሉ
በአንዱ አንድ ወንበር ሲያገኝ በሁለተኛው ፓርላማውን ጨርሶ አስረክቧል፡፡ ሀገራዊ ውድድርን በአሸናፊነት ለመወጣት
ካልሆነም ትንሽ ወንር ከፓርላማ ለማግኘት አንድ ቡድን መስርቶ በአንድ ማሊያ መጫወት ያለውን ጠቀሜታ ከወያኔ መማር
ባይቻል ወይንም ባይፈለግ እንደምን ከቅንጅት መማር ይቸግራል፡፡
ለውጤታማነት በአንድ ማሊያ መጫወት የሚያስፈልገውና የሚጠቅመው በሀገር ቤት ለሚደረገው ትግል ብቻ
አይደለም፡፡የትግሉ መነሻ ቦታ ኢትዮጵያም ይሁን አሜሪካ፣ ኤርትራም ይሁን በርበራ፣አሰብም ይሁን ሱዳን በሁሉም
የሚፈለገው ውጤት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ከሆነ በአንድ ቡድን ተሰባስቦ አንድ ማሊያ ለብሶ አንድ ሀገራዊ
ገዢ መርህ አንግቦ መጫወት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ እስካሁን በተመጣበት ሁኔታ የሚካሄድ ውድድር(ትግል)
ይህን ያህል ቡድን እዛና እዚህ አለ ከመባል ባለፈ ብሎም አንድ ቡድን ብቻውን ለጨዋታ ሜዳ አይገባምና የወያኔ
አጨዋች ከመሆን የዘለለ የሚፈይደው ነገር የለም፣ አለ ከተባለ እገሌ የዚህ ቡድን መሪ እገሌ የዛኛው ቡድን
ሊቀመንበር እየተባሉ መኖርን ትግልም ድልም ላደረጉ ሰዎች የሥልጣን ጥም ርካታ ማስገኘቱ ብቻ ነው፡፡ የፓርቲ መሪነት
ሥልጣን ሆኖ፡፡
ሀያ አራት አመት እጅግ ብዙ ነው፡፡ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሊመረን ይገባል፡፡በርግጥ ለውጥን ዓላማቸው አድርገው
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሥረታ ከልብ አምነው ለዚህም ከምር ቆርጠው ለመታገል የወሰኑትና የፓርቲ ሊቀመንበር እየተባሉ
መኖርን መነሻ ዓላማቸው መድረሻ ግባቸውም አድርገው የሚኖሩት ይለዩ፡፡ አንድ ቡድን መስርቶ በአንድ ማሊያ ተወዳደሮ
የዋንጫ ባለቤት ላለመሆን ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው ቡድኖች ያላቸው የአደረጃጀት ፣ የጨዋት ስልት ፣የሚገኙበት
ቦታ ወዘተ ልዩነት አሳማኝ አይደለም፡፡ ዋናው ምክንያት ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ያለመፈለግ ወይንም ቁርጠኝት ማጣት
ነው፡፡ ለለውጥ በቁርጠኝነት የተሰለፈ ለለውጥ እንቅፋት ለሆኑ ችግሮች መፍትሄ ይፈልጋል እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ
ሰበቦችን ያስወግዳል እንጂ ልዩነትን ለማስፋት ሲማስን አያድርም፣በእያንዳንዱ ርምጃ ሰበብ እየፈለገ እንቅፋት
አይፈጥርም፣ስለ ሀገራዊው ድል እንጂ ስለ እርሱ ቦታ አይጨነቅም፡፡
አንድ በግልጽ የሚታይ ነገር ላንሳ ጀነራል ከማል ገልቹና ጀነራል ሀይሉ ጎንፋ ሁለቱም ከወያኔ ከድተው አስመራ
የገቡ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፡፡እዛ ደርሰው ግን በአንድ ቡድን ተሰልፈው አንድ ማሊያ (ኢትዮጵያዊ ቢቀር
ኦሮሚያዊ)ለብሰው መጫወት ተስኖአቸው ተለያይተው በኦሮሞ ስም የተለያየ ቡድን መስርተው እንደሚገኙ ነው የሚሰማው፡፡
ለያዙት ማእረግ የበቁት ውትድርናውን መቼ ጀምረውት እንደሆነ ማስረጃ ባይኖረኝም እዚህ ማዕረግ እስኪደርሱ በቃልም
በተግባርም፤ በክፍልም በመስክም ወዘተ ሰፊ ወታደራዊ እውቀት እንደቀሰሙና ልምድ እንዳካበቱ እሙን ነው፡፡ ታዲያ
በዚህ ወቅት ከሀገር ቤት ብቻ አይደለም ከአውሮፓና አሜሪካ ጭምር ከፕሮፌሰር እስከ ጳጳስ ከምር ቆርጠው ትግሉ ቦታ
ሲወርዱ ጀነራሎቹ አሥመራ ተቀምጠው እንኳን ከሌላው መተባበር ርስ በርሳቸውም መነጋገር አቁመው አመታት መቁጠራቸውን
መስማት እንቆቅልሽ አይሆንም!
ከምር ራሳቸውን ለትግሉ የሰጡና ለሥልጣን ሳይሆን ለነጻነት የሚታገሉ ስራቸው ምስክር ነውና በተግባራቸው
እንለያቸው በምንችለውም አንደግፋቸው ይጠናከሩ፡ከውጤት አልባው የአመታት ጉዞአቸው ተምረው ለመለወጥ ያልፈቀዱትና
ትግሉን ለስማቸው መጠሪያ ብቻ አድርገውት የሚኖሩት እንደዚሁ በተግባራቸው ይለዩ ፡፡ የእነዚህ መኖር ለሀገራዊው
ትግል ከሚጠቅም ይልቅ ጉዳት ናቸውና ድጋፍ እንነሳቸው፤ከመኖራችሁ አለመኖራችሁ ይሻላል ብለን በግልጽ እንንገራቸው፡፡
ለነገሩ ሀገር ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ፓርቲዎች በወያኔ ዘንድ ነው እንጂ አሉ የሚባሉት ቆሞ ያልጠቀመ ሞቶ ምን
ሊጎዳ ብሎ ሕዝቡ ከሸኛቸው አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በውጪም በሚገኙት ላይ ይሄው መደገም አለበት፡፡ ሀገራዊውን ጨዋታ
በአሸናፊነት ለመወጣት በአንድ ማሊያ መጫወት በምንልበት በዚህ ሰዐት እንወክለዋለን በሚሉት የአንድ አካባቢ ሕዝብ
ስም የተደራጁ ሁለትም ስድስትም ድርጅቶች ስም እንሰማለን፡፡ የድርጅቶቹ መስራቾች ሁሉም ሊቀመንበር መባል
በመፈለጋቸው ነው፡፡ ብዙም አባል አንደሌላቸው ይታወቃል፤ደጋፊው ግን ምን ይባላል፡፡ ትግሉን ከምር ያዙት አለያም
ተዉት ማለት አያስፈልግም ትላላችሁ፡፡
በመጨረሻም ሎሬትን እንጋራ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ