በ11ሺ 149 ስኩዌር ኪሎሜትር ላይ ሰፈረውና 413ሺ564 ሕዝብ እንዳለው የሚነገርለት የወልቃይት ማህበረሰብ ባለፉት 24 ዓመታት የአማራ ብሄር ነን በሚል በአማራ ክልል ለመካለል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርብ ቢቆይም ጥያቄው በትግራይ ክልል በአዎንታ መልኩ ባለመታየቱ ለእስር፣ ለሞትና ለስደት መዳረጉን ከሕዝቡ የተወከሉ የኮምቴ አባላት ያስረዳሉ። ባለፉት 24 ኣመታት አማራ ነን የሚል የብሄርተኝነት ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ 116 ያህል ሰዎች ታስረው የገቡበት እንዳልታወቀ የኮምቴ አባላቱ በስም ዝርዝር አሳውቀዋል። በተጨማሪም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ንብረታቸው በጠራራ ጸሀይ የተነጠቁ ሰዎችንም ዝርዝር እንዲሁ በማስፈር አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ም/ቤት እና ለሰብዓዊ መብት ኮምሽን ሰሞኑን በጹሑፍ አሳውቀዋል።
የወልቃይት ሕዝብ አቤቱታ እንደሚከተለው ቀርቧል።
……………
የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ መነሻ፣
በመሰረቱ የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አሁን የተነሳ ጥያቄ ሳይሆን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የተነሳና በሕገ-መንግስቱ የሰፈሩትን ሃሳቦች ታይተው ምላሽ ያልተሰጠው በየጊዜው እየተንከባለለ የመጣ ነው። ጥያቄው እንደ ጥያቄ ማንሳት በሕግ እንደሚያስቀጣ ሕገመንግስታዊ መብት ነው ብሎ እንደመብት ተደርጎ ባለመወሰዱ የተነሳ ሲንከባለል የቆየ ጥያቄ እንጂ አዲስ ጥያቄ አይደለም።
የወልቃይት የአማራ ብሔተኝነት ጥያቄ እንደ ጥያቄ ሲነሳ ዋናው መነሻው ሕገ-መንግስቱን መሠረት ያደረገ ነው። በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39 ተራ ቁጥር 2 ተራ ቁጥር 5 እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል።
ተራ ቁጥር 2 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ በቋንቋው የመናገር የመፃፍ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ የማዳበር የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው” ይላል። ከዚህ በተጨማሪም በተራ ቁጥር 5 በዚህ ሕገ-,መንግስት ውስጥ “ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለፀውን ባህሪይ የሚያሳይ ማህበረሰብ ነው። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚንፀባርቅ ባህል ወይንም ተመሳሳይ ልምድ ያላቸው ሊግባቡ የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው የጋራ ወይም የተዛመድ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ የሥነ-ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ በመልክዓምድር የሚኖሩ ናቸው።
በሕገመንግስቱ አንቀፅ 39 ተራ ቁጥር 2 እና 5 በተቀመጠው መሰረት እኛ የወልቃይት ሕዝቦች የራሳችን አማራዊ ባህል ያለን ሲሆን ይህ ባህል ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ የተረከብነው እና ከዘመን ዘመን እያደገ የመጣ የነበረ ነው። ሆኖም ግን በዚህ 24 ዓመታት ውስጥ ይቅር የራሳችን ባህል ማሳደግ፣ ማስፋፋት፣ መከባከብ ይቅርና እነሆ የማንነታችን መገለጫ የሆነው ባህላችን እየጠፋ በሌላ ባህል እየተተካ የእኛ ባህል እየከሰመ በምትኩ የሌላ ባህል የሚያድግበት የሚስፋፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ህገመንግስቱ ያስቀመጠው መብቶቻችን ተረግጦ በምትኩ አዲሱ ትውልድ የሌላ ብሔር ባህል እንዲቀበል በመደረጉ የአንድ ብሔር ባህል ጠፍቶ በሌላ ባህል መተካት ሕገመንግስታው ጥሰት መሆኑ እየታወቀ በእኛ ላይ ይህ መሰል ሕገ-መንግስታዊ የመብት ጥሰት የተካሄደብን ስለሆነ ይህን ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ቆሞ ታሪካችን ወጋችን ባህላችን በአጠቃላይ ማንነታችን ወደሚከበርበት አማራ እንድንከለል የተነሳ ጥያቄ ነው።
በሌላ በኩል ከደርግ ውድቀት በፊት ሃገራችን በተማከለ አስተዳደራዊ ስርዓት ስትመራ በነበረበት ወቅት እኛ የወልቃይት ህዝቦች በጎንደር ክ/ሃገር በወገራ አውራጃ ውስጥ ስንተዳደር የነበርን ከአማራ ህዝብ ጋር ተፋቅረን ተመሳሳይ ሳይሆን አንድ አይነት ባህል ወግ ታሪክ ያለን የስነ ልቦና ትስስር ያለን በተያያዘ መልክአምድር ጋር የምንኖር ህዝቦች ሁነን እያለን ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ እነዚህ እላይ የተገለፁትን የብሔር ብሔረሰብ መገለጫ ተጠቃሚ ሳንሆን ቀርተናል። ያለ ህዝቡ ፍላጎትና ምርጫ ተከለልን እንጂ በራሳችን ፍቃድና ሕገ-መንግስቱ ባረጋገጠልን መስፈርት ተመስርቶ ባለመካለላችን ማንነታችን እንዲጠፋ አድርጓል።
ስለሆነም ዛሬ በዓለማችን ሆነ በሃገራችን ዴሞክራሲ በማደግ ላይ ነው። ምንጊዜም ቢሆን ዴሞክራሲ የሚያድገው በሂደት ስለሆነ ትላንትና እንደነውር ወይንም እንደወንጀል የሚታዩ የነበሩ፣ ነገር ግን የዴሞክራሲ መብቶች የሆኑ ጊዜአቸው ሲደርስ መብት ሁነው ሲገኙ በዴሞክራሲ ስርዓት መልስ ያገኛሉ። ስለዚህ በሀገራችን ሁሉን ያካተተ ህገመንግስት አለን። ስለዚህ ሕገመንግስት ሲባል ክብረ መስዋትነት ተከፍሎበታል። በመሆኑም በሕገ መንግስቱ አማካኝነት የሚመለስ ጥያቄ እስከአለን ድረስና ይህን ጥያቄ የሚመልስ ሥርዓት እስካለን ድረስ የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት ጥያቄ ማነሳታችን ወንጀል ሳይሆን ሕገመንግስታዊ መብታችን መሆኑ አሁንም ሊታወቅልን ይገባል።
በወልቃይት ሕዝብ የደረሱ የፖለቲካ ተፅዕኖዎች
- ልጆቻችን በቋንቋቸው እንዳይማሩ በግድ ትግርኛ እንዲማሩ ተደርገዋል፣
- በየትኛው መ/ቤት የስራ ቋንቋ በግድ በትግርኛ እንድንናገር ተገደናል፤
- የአማርኛ ባህል ቀይራችሁ የትግርኛ ባህል በግድ ተቀበሉ እየተባልን ነው
- የአካባቢያችን ጥንታዊ ያሀገር፣ የወል እና የጋራ ስሞች ማትም የወረዳ፣ ከተማ መንደር፣ ወንዝ ጋራ ሸንተረር ምንጭ በትግራይ ስም ተሰይመዋል።
- በትግራይ ባሉ መስሪያ ቤቶች የወልቃይት ተወላጆች 5 በመቶ የትግራይ ተወላጅ 95 በመቶ ሲሆን፤ ያሉትም እኩል መብትና ስልጣን የላቸውም፤
- ትግራይ ክልል መሆን አንፈልግም ብለው የተቃወሙትን ከ300 በላይ የሚሆኑ የወልቃይት ተወላጆች ከየቤታቸው በጨለማ ታፍነው ተወስደው ያለፍርድ ጠፍተዋል። ለዚህ አባሪውን መመልከት ይቻላል። የእነዚህ ወገኖች በአመለካታቸው መጥፋት ዋናው ምክንያት የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው በመሆኑ የወገኖቻችን መጥፋት ሕገ-መንግስታዊ ጥሰት ስለሆነ ይህን የፈፀመው የትግራይ መንግስት መሆኑ፤
- ወልቃይት በመወለዳችን በማንነታችን እንድናፍር ሁነናል፤
- ትግራይ አይደለንም ያሉትን በቀጥታ ንብረታቸውን ሀብታችን ተወርሰዋል። ሃብትና ንብረታቸው የተወሰደባቸው ዝርዝር ከአባሪው ጋር ተያይዟል፤
- መሬታቸው ተነጥቆ ለትግራይ ተወላጅ በመስጠት የወልቃይት ተወላጆች ወደ ድህነት እንዲወርድ ተደርገዋል።
- በግልባጩም የትግራይ ተወላጅ አለአግባብ ሃብታም እንዲሆኑ ተደርጓል
በወልቃይት ሕዝብ በማህበራዊ ኑሮ ላይ የደረሰው ጉዳት፣
- ከመንገድ አንጻር የትግራይ አካባቢ ከወረዳው ቀበሌ የሚያገናኝ ጥርጊያ አብዛኛው ተሰርቷል። የወልቃይት አካባቢ ግን ከወረዳ ቀበሌ ይቅርና ከወረዳ ወደ ወረዳ የሚያገናኝ አንኳን በቅጡ ተሰርቶ አይታይም። ዛሬም የወልቃይት እናት መኪና አጥታ በወሊድ የምትሞት ናት።
- ውሃ ዛሬ በብዙ የትግራይ አካባቢ ንፁህ ውሃ ሲጠጣ የወልቃይት ህዝቦች ግን እንስሳ እና ሰው በአንድ የሚጠቀሙበት በብዙ ቦታ ይታያል።
- ትላንትና የመጣ የትግራይ ሰፋሪ ህዝብ ቧንቧ ውሃ ሲዘረጋለት ጥንታዊ የወልቃይት ህዝብ ግን ምንም ውሃ እና የጉድጓድ ውሃ ሲጠቀም ይታያል የህክምና ተቋማትም ተመሳሳይ ለትግራይ ተወላጆ በሚጠቅም መልኩ የተሰራ ነው።
- የትምህርት ተቋማትም አንድም ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ የለም
የፌዴሬሽን ም/ቤት ባለው ስልጣንና ኃላፊነት በሰላማዊ መንገድ ያነሳነው የዴሞክራሲ ጥያቄያችን ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን፣ እኛ የህዝባችን ተወካዮች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ህዝባችን የደረሰበት ሕገመንግስታዊ ጥሰትና እየደረሰበት ያለ በዴሞክራሲ መንገድ እንዲፈታ ከህዝባችን ጋር ለመወያየት እንዲፈቀድልን፣ የህግ ከለላ እንዲሰጠን። በሌላ በኩል ወደእዚህ የመጣን የህዝባችን ወኪሎች ስንመለስ በራሳችን፣ በቤተሰቦቻችንና በሀብታችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስብን የሕግ ከለላ እንዲደረግልን በታላቅ ትህትና እንጠይቃለን።
ው