ረቡዕ 29 ሜይ 2013

መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ መንግስትን ለመክሰስ መረጃ እያሰባሰቡ ነው

እዚህ ፍትህ ካጣን ወደ ዓለምአቀፉ ፍ/ቤት እንሄዳለን 20ሺ ሰው ሲፈናቀል አላውቅም ማለት ተቀባይነት የለውም በቅርቡ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሠማያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሠውን መፈናቀል አስመልክቶ ድርጊቱን በፈፀሙት የመንግስት ባለስልጣናት እና ተቋማት ላይ ክስ ለመመስረት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዋናነት የክሡ መነሻ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የደረሠው መፈናቀል ይሁን እንጂ ከአመት በፊት በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ የደረሠው መፈናቀልና ያስከተለው ጉዳትም በክሡ እንደሚካተት ፓርቲዎቹ ተናግረዋል፡፡
ማስረጃዎችን አሠባስቦ በማቀናጀት ሃገር ውስጥ ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች ክስ በመመስረት በኩል ደግሞ የቀድሞው የቅንጅት አመራር አባልና በአሁን ሠአት ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ተገልለው በአለማቀፍ የህግ ባለሙያነት በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ በክሱ አቀራረብና ባህሪ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምን በቢሮአቸው አነጋግሯቸዋል፡፡ የክሡ ሂደት ምን ላይ ደረሠ? በሠማያዊ ፓርቲና በመኢአድ አነሣሽነት ነው ክሡ ሊመሠረት የታሠበው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ክሡ አልተጀመረም፡፡ ማስረጃ ሠብስበን ከተጐዱት ሠዎች የውክልና ስልጣን ወስደን ወደ ስራው እንገባለን፡፡
አሁን ግን ገና ነው፤ የውክልና ስልጣኑም አልተዘጋጀም፡፡ በአካባቢው ያሉ ሠዎችን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ስራው አሁን በውል ተጀመረ ማለት ባይቻልም በቅርቡ ሠዎች ወደዚያው ሄደው የተጐዱና የተፈናቀሉ ሠዎችን በመጠየቅና የደረሠባቸውን ጉዳት በማየት መረጃ እያሠባሠቡ ነው፡፡ ክሡን የምንመሠርተው ከዚያ በኋላ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መጀመሪያ እንደሚታወቀው መረጃውን ማሠባሠብ ያስፈልጋል፡፡ በግልፅ ህግ መጣሡን በደንብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ከተሟሉ በኋላ በቀጥታ ወደ ክሡ እንሄዳለን፡፡ መጀመሪያ የሠዎቹን ውክልና ሣታገኙ እንዴት ለመክሠስ እየተዘጋጃችሁ መሆኑን ገለፃችሁ?
መጀመሪያ ውክልናውን ማግኘታችሁን ማረጋገጥ አልነበረባችሁም? እንግዲህ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘን የምንቀርበው በሁለት አይነት ነው፡፡ የወንጀልም የፍትሃ ብሄር ጉዳይም አለው፡፡ የወንጀል ጉዳይን በተመለከተ ማንኛውም ሠው እንደተጐጂው ሆኖ ለፍትህ አካል አቤት ብሎ፣ ፖሊሶች ጉዳዩን ከመረመሩና ማስረጃውን ካጠናቀሩ በኋላ ወደ አቃቤ ህግ ይመሩታል፡፡ አቃቤ ህግ ክስ ይመሠርታል ወይንም በቂ ማስረጃ የለኝም፤ ክስ አልመሠርትም ብሎ ሊተወው ይችላል፡፡ በቂ ማስረጃ ካለ ደግሞ ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በቀጥታ እኛ የምንሣተፍበት ደግሞ አለ። እነዚህ ሠዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ የንብረት መውደም ደርሶባቸዋል፣ ጤናቸው ታውኳል፣ ብዙ አይነት ጉዳት ነው የገጠማቸው፡፡ ያ ሁሉ በገንዘብ ተሠልቶ የሚገባቸውን ካሣ፣ ተጠያቂ የመንግስት አካላት እንዲከፍሉ ነው የሚደረገው፡፡ መኢአድና ሠማያዊ ፓርቲ ከተጐጂዎች መካከል በርካቶቹን ጠይቀው ፈቃደኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የውክልና ስልጣን ከዚያ በኋላ ይመጣል ማለት ነው፡፡
ክሱ በዚህ አገር ያልተለመደ ዓይነት ይሆናል ብለው ነበር፡፡ ሊያብራሩት ይችላሉ? ብዙ ሠው የያዘ ቡድን አንድ አይነት ጉዳት ከደረሠበት አንዱ ብቻ ከሶ ፍርድ ካገኘ ሌሎቹም ክስ ሣይመሠርቱ ከውጤቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሄ በፈረንጆች “ክላስ አክሽን ሱት” ይባላል። ለምሣሌ የተፈናቀለው የአማራው ህብረተሠብ ተመሣሣይ በደል ነው የደረሠጁ እና ከእነሡ ውስጥ አንድ ሠው ብቻ ከሶ ፍርድ ካገኘ (ከረታ) ሌሎቹ የተጐዱ ሠዎች ክስ ሣይመሠርቱ፣ ለፍርድ ቤቱ ተመሣሣይ በደል እንደደረሠባቸው በማመልከት ብቻ ከፍርዱ እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ይህ በሃገራችን ብዙም አልተለመደም ግን እኛ ይህ አካሄድ በሃገራችን ይሠራል የሚለውን ልንፈትሸው ነው፡፡ ጉዳዩን በምሣሌ ማየት ይቻላል። አንድ መለያ ያለው የጥርስ ሣሙና ከገበያ ገዝተህ ሣሙናው የተመረዘ ቢሆንና ብዙ ሠዎች ተጠቅመውት ከተጐዱና አንድ ሠው ብቻ ክስ አቅርቦ ከኩባንያው ካሣ ካገኘ፣ ያንን የጥርስ ሣሙና ተጠቅመው ተጐጂ የሆኑ ሠዎች ከዚያ ፍርድ ውጤት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
እኛም በዚህ መልኩ ነው ክሣችንን የምንመሠርተው፡፡ በእያንዳንዱ ተጐጂ ስም ክስ የማቅረብ ሃሣቡ የለንም፡፡ ውክልናውን ከአንድ ሠው ብቻ ብታገኙም መክሠስ ትችላላችሁ ማለት ነው? አዎ በሚገባ ይቻላል፡፡ ውክልና የሠጠን ሠው ከፍርድ ሂደቱ በሚያገኘው ውጤት ተመሣሣይ ጉዳት ያጋጠማቸው ሁሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሠረት የአንድ ሠውም ውክልና የመንግስትን ተጠያቂ አካላት ለመክሠስ ያስችለናል፡፡ በአገራችን ይህን ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አለ?
በህገ መንግሥቱም አለ፣ በወንጀለኛ መቅጫውም በፍትሃ ብሄር ህጉም አለ፡፡ ለምሣሌ በህገ መንግስቱ ላይ “ክላስ አክሽን ሡት” የሚባለውን በተመለከተ የተጠቀሠ አለ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 37 ላይ “ማንኛውም ቡድን ወይም ተመሣሣይ ጥቅም ያላቸውን ሠዎች የሚወክል ግለሠብ ወይም የቡድን አባል የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው” ይላል፡፡ እንግዲህ ማንኛውም ግለሠብ፣ ተመሣሣይ ጥቅም ያላቸው የቡድን አባላትን ወክሎ የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው፡፡ እንግዲህ ያ የሚወክለው ግለሠብ ጠበቃ ሊሆን ይችላል፡፡
የቡድኑ አባል ደግሞ ከተበዳዮች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከተጐጂዎች ውክልና የሚሠጣችሁ ሠው ብታጡስ…ምን ታደርጋላችሁ? የተሠሩ ወንጀሎችን ከአንዳንድ ሠዎች ጠይቀን፣ ያንን ሪፖርት ለፖሊስ እናቀርባለን። ፖሊሶች ለአቃቤ ህግ ያቀርባሉ፡፡ አቃቤ ህግ መረጃና ማስረጃዎችን መዝኖ ክስ ይመሠርታል፡፡ በፍትሃብሄር ካሣ ለማግኘት ግን እነሡ የውክልና ስልጣን ካልሠጡን አይሆንም፡፡ የወንጀሉ ክስ ግን እነሡ ውክልናውን ቢሠጡም ባይሠጡም ይቻላል፡፡ እኛ ሣንሆን በወንጀሉ አቃቤ ህግ ነው የሚከሠው፡፡ እኛ ግን እስካሁን የተረዳነው፣ ሠዎች የዚህ የፍትሃብሄር ክስን በተመለከተ በመኢአድና በሠማያዊ ፓርቲ አማካኝነት ክሡን ለማቅረብ ፍላጐት እንዳላቸው ነው፡፡ ዋነኛ ማስረጃችሁ ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው? ዋነኛ ማስረጃ የሚሆኑት ተጐጂዎቹ ራሣቸው ናቸው፡፡ ለምስክርነት ይቀርባሉ፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትም ለምስክርነት ይቀርባሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሣለኝ ይሄ ነገር ከባድ ወንጀል እንደሆነና መፈፀም እንደሌለበት፤ በአጥፊዎች ላይም መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል፡፡ እሣቸውም በአካልም ሆነ ንግግራቸው በቪዲዮ ማስረጃነት ያለ ጥርጥር ይቀርባሉ፡፡ እርግጥ ማስረጃ በተለይ በተጐጂዎች ሲቀርብ የፍርሃቱ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ የክልሎቹ ባለስልጣናትም ሆኑ የፌደራሎቹ ሊያስፈራሯቸው ይችላሉ፡፡ ጥቃት የደረሠበት ሠው ደግሞ ይፈራል። አሁንም ጥቃት ውስጥ ያሉ ሠዎች ናቸውና ሊፈሩ ይችላሉ፡፡ ግን መኢአድና ሠማያዊ ፓርቲ እንዳረጋገጡልን በዚህ ጉዳይ ላይ ለመግፋት የሚፈልጉ ሠዎች አሉ፡፡ አንዱ የክሱ ጭብጥ “ዘር ማጥፋት” የሚል መሆኑን በሠጣችሁት መግለጫ ላይ ጠቅሳችኋል። ዘር ማጥፋት ሲባል ምንድን ነው? ዘር ማጥፋት በሚለው ክስ ለማቅረብ የሚያስችላችሁ የህግ ማዕቀፍ ይኖራል? ሁለት አይነት ወንጀሎች ናቸው፡፡ የዘር ማጥፋት የሚለው አንዱን ብሄረሠብ ወይም ዘር በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በማቀድ፣ በማሠብ ጥቃት መፈፀም ማለት ነው፡፡ ያን ጥቃት መፈፀም እንግዲህ ዘር ማጥፋት ሊሆን ይችላል። ዘር ማጥፋት (ዲፖርቴሽን) ሊሆን ይችላል፣ ማፈናቀልም ሊሆን ይችላል፣ ልጆች እንዳይወልዱና የዘር መተካካቱ እንዳይቀጥል ማድረግም ሊሆን ይችላል፡፡
ይሄ እንግዲህ በሠው ዘር ላይ የሚሠራ ወንጀል ነው – ጀኖሣይድ ወይም የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው። አሁን እኛ እንደምንገምተው አማሮችን ከየክልሉ የማባረሩና የማፈናቀሉ ነገር ቆይቷል፡፡ ከበደኖ ጀምሮ አርባጉጉ፣ ጉራፈርዳ አሁን ደግሞ ቤንሻንጉል… ሌሎችም አሉ፡፡ ይሄ ቢደረግም የአማራን ዘር በከፊልም ሆነ በሙሉ ለማጥፋት ታቅዶ የሚደረግ ነው ወይ ለሚለው ማስረጃ የለንም፡፡ እነዚህ ሠዎች ለመፈናቀላቸው ከቦታ ቦታ መነቀላቸው፣ ንብረታቸውን ማጣታቸው፣ በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሡን እናውቃለን፤ ማስረጃውም አለ። እንግዲህ የዘር ማጥፋት ሣይሆን የዘር ማጥፋት ወንጀል የምንለው ከነበሩበት አካባቢ በዘራቸው ምክንያት ከተፈናቀሉ ነው፡፡ አንድ ሠው በዘሩ፣ በሃይማኖቱ ወይም በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት ጉዳት ከደረሠበት በሠው ዘር ላይ የሚሠራ ወንጀል ነው፡፡ አሁን ሠዎች በአማራነታቸው፣ በዘራቸው በተቀነባበረ መልክ ለብዙ ጊዜ የዘር ማጥፋት ወንጀል በዚህ መልኩ ተፈፅሞባቸዋል፡፡
በአካባቢው አንድ ዘር ብቻ እንዲኖር ካለ ፍላጎት፣ እነዚህ ዘሮች (አማሮች)ከሚኖሩበት ተፈናቅለዋል፡፡ እና ይሄ ዘር ማጥፋት ይባላል፡፡ ሁለተኛው የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጀምረው አንድ ሠው በሃይማኖቱ፣ በዘሩ ምክንያት በተቀነባበረ መልኩ በሠፊው ግድያ፣ መፈናቀል፣ የመሣሠሉ ነገሮች ከተፈፀሙበት ነው። ሁለቱም በጣም ከባድ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በአለማቀፍ ህግ መሠረትም በተመሣሣይ የወንጀል ፈርጅ ነው የሚቀመጡት፡፡ ተመሣሣይ ቅጣት ያስከትላሉ፡፡ እኛ አሁን በኢትዮጵያ የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት ነው ብለን ደፍረን ባንወጣም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ በአማራዎች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ እኔ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የሚለውን አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም አማርኛ ተናጋሪዎች ነን፡፡ በዚህ መሠረት አማራዎች ለረጅም ጊዜያት በተቀነባበረ መልኩ ከተቀመጡበት ሲፈናቀሉ ኖረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአለማቀፍ ህግም በሃገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ህግም ወንጀል ነው፡፡
“በዘር ማጥፋት” ወንጀል መክሠስ የሚያስችላችሁ የህግ ማዕቀፎች አሉ? በደንብ አሉ፡፡
አሁን እኔ እንዳጋጣሚ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን አልያዝኩትም እንጂ ይሄን የሚቀጣ አንቀፅ አለ፡፡ እንደውም የደርግ ባለስልጣናት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሠው ነበር፡፡ በእርግጥ ክሡ ትክክል ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ወንጀሉ ያነጣጠረው የፖለቲካ ቡድንን መሠረት አድርጐ ነበር፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል የምንለው በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በዘር ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካ እምነት መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር በህጋችን የዘር ማጥፋት ምንድን ነው የሚለው በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማለት በሠው ዘር ላይ የሚፈፀም ወንጀል ወይም ማፈናቀል መሆኑ በህጋችን በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የደርግ ባለስልጣናትም የተከሠሡት አንደኛ በዘር ማጥፋት፣ ሁለተኛ ደግሞ በዘር ማጥራት፣ ሶስተኛ ደግሞ በተራ ግድያ ተጠያቂ ሆነው ነበር፡፡ ጉዳዩ ከመሬት እና ከይዞታ ጋር የተገናኘ እንጂ የዘር ጥላቻ አይደለም የሚሉ አካላት አሉ? የዘር ጥላቻ ሆነም አልሆነም ዋናው ነገር መፈናቀላቸው ነው፡፡
ከቤት ንብረታቸው ብዙ ጊዜ የኖሩበትን ቦታ በግድ ማስለቀቅ ጥላቻ ቢኖረውም ባይኖረውም ወንጀል መሆኑ አይቀርም። በህገ መንግስቱ አንቀፅ 32፣ የመዘዋወር መብትን በተመለከተ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በህጋዊ መንገድ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሃገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል፡፡ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፤ ለውጭ ዜጐችም ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በፈለጉበት መኖርና ወደፈለጉበት መንቀሣቀስ ይችላሉ፡፡ ለውጭ ሃገር ሠዎች እንኳ መብቱ ተሠጥቷል፡፡ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል ላይ መኖርና ሠርቶ መለወጥ ይችላል ማለት ነው፡፡ እርግጥ አንዳንድ የተከለሉ አካባቢዎች አሉ፡- እንደጦር ሠፈር፣ ቤተመንግስት፣ የእንስሣት ፓርኮች የመሣሠሉት … እዚያ ልግባ ቢሉም ልኑር ማለት አይቻልም፡፡ በተረፈ ግን ዘሩም ሆነ ቋንቋው ምንም ቢሆን የፈለገበት ቦታ ሄዶ የመኖር መብት እንዳለው ህገ መንግስቱ በግልፅ ይደነግጋል፡፡
አንድ ጊዜ ከጉራፈርዳ ስለተፈናቀሉ ሠዎች ጉዳይ በፓርላማው ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ጠ/ሚ መለስ በወቅቱ እነዚህ ሠዎች ደን ይመነጥሩ ነበር ብለው መልስ ሠጡ፡፡ የዚህ አንደምታው የተወሠደው እርምጃ ትክክል ነው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሠዎች ዛፍ ይቆርጡ እንደሆነ ህግ ካለ በህግ ይጠየቃሉ፤ ጫካ ይመነጥሩ እንደሆነም እንደዚያው፡፡ አሁን አቶ ኃይለ ማርያም የተለየ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አቶ መለስ ፍፁም ህጋዊ አድርገው የቆጠሩትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ህገወጥ መሆኑንና መደረግ እንደሌለበት፤ መንግስትም እርምጃ እንደሚወስድ ገልፀዋል፡፡ ከአካባቢው አማራዎች ብቻ ሣይሆኑ ኦሮሞዎችም የመፈናቀል እጣ ገጥሟቸዋል ተብሏል።
ይሄንንስ እንዴት ነው የሚያዩት? በእርግጥ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ብለውታል፡፡ ነገር ግን በአማራዎች ላይ እየደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ ነው፡፡ የቆየም ነው፡፡ በግብታዊነት ሰዎችን ማፈናቀል በፕላን የተሠራ የቆየ ድርጊት ነው። ሊፈፀም የማይገባው ወንጀል ነው የተፈፀመው፡፡ አሁን ክስ እንመሠርትባቸዋለን ከምትሏቸው ሃላፊዎች መካከል በህዝብ ተመርጠው የምክር ቤት አባላት የሆኑ አሉ፡፡ የእነዚህን ሰዎች ያለመከሰስ መብት ከግምት አስገብታችኋል? እንግዲህ አንድ የህዝብ ተወካይ ሊከሰስ የሚችለው ፓርላማው የዛን ሰው ያለመከሰስ መብት ሲሰርዝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምናልባት እንደዚህ አይነት ያለመከሰስ መብት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ማጣራት ይኖርብናል፡፡
ካላቸው ፓርላማ ወይም ምክር ቤት በዚህ በዚህ ወንጀል ምክንያት ያለመከሰስ መብታቸውን መሰረዝ አለበት ብለን ማመልከት አለብን፡፡ ያኔ ምክር ቤቱ ፍቃድ ከሰጠና ከሠረዘ ይከሰሳሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሂደት ካልታለፈ መክሰስ አይቻልም። የትኛውም ፓርላማ እንዲህ አይነት ከባድና ግልጽ ወንጀል በሚፈፀምበት ጊዜ ያንን ያለመከሰስ መብትን ያሠርዛል፡፡ እኛም የትኛው ነው ያለመከሰስ መብት ያለው የሚለውን ካጣራን በኋላ፣ አስቀድመን ለምክር ቤቶቹ አመልክተን መብቱ እንዲሠረዝ እንጠይቃለን፡፡ ክሳችሁ የሚያካትተው በየትኛው ጊዜ እና በየትኛው የሃገሪቱ ክልል የተፈፀሙትን ወንጀሎች ነው? አሁን ለጊዜው ቤንሻንጉል እና ጉራፈርዳ የተከሰተውን ነው ያሰብነው፡፡ ሌላው በቀጠሩን ፓርቲዎች የሚወሰን ነው፡፡ በእርግጥ ድርጊቱ በብዙ ቦታዎች የተፈፀመ ነው፡፡ ግን ክስ የሚመሠረተው አንድም እንዲህ አይነት ድርጊት ለወደፊቱ እንዳይደገም ማስተማሪያ እንዲሆን ነው፡፡
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም ለማድረግ ነው፡፡ ክስ ብዙ ጊዜ የሚመሠረተው ከክሱ ውጤት ሌላው እንዲማርና ተበዳዩ እንዲካስ ነው፡፡ ክሱ በአገር ውስጥ ፍ/ቤቶች ተቀባይነት ካጣ ወደ አለማቀፍ ፍ/ቤት እንሄዳለን ብላችኋል፡፡ ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል ሳትሆን ክስ መመስረት ይቻላል? የክሱ አንዱና ዋናው አላማ ይህ ድርጊት ከእንግዲህ በማንም ኢትዮጵያዊ ላይ እንዳይፈፀም ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ይሄ ክስ እዚህ ሊሳካልን ባይችል በአለማቀፍ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ለነዚህ ኢትዮጵያውያን የዳበረ ማስረጃ ለመስጠት ነው፡፡ በአለማቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት መጀመርያ የአገር ውስጡን ማጣራት አለብን፡፡ በአገር ውስጥ ፍትህ ከተነፈግን ወይንም የአገሩ መንግስት ሊሰማ ካልፈለገ ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ሊያመራ ይችላል፡፡ በፊት እንደተባለው ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል አይደለችም፡፡ ለምን እንዳልሆነች እኔ በእውነት ሊገባኝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከአፄ ኃይለስላሴ ጀምሮ በደርግም ዘመን ኢትዮጵያ አለማቀፍ ስምምነቶችን በመቀበል ንቁ ተሣትፎ ነበራት፡፡ የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር ለመፈረም እኮ የመጀመሪያዎቹ ጥቁር ህዝቦች እኛ ነን፡፡
ኢህአዴግ ለምን ሊቀበለው እንዳልፈለገ አይገባኝም፡፡ ሆኖም ግን አገር ውስጥ ከባድ ወንጀል በሚፈፀምበት ጊዜ አባል አይደለችም፤ ስለዚህ አትከሰስም ተብሎ አይታለፍም፡፡ አባል ከሆነ በቀጥታ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ እንዲመረመር ያዛል፤ ተመርምሮ ክስ ይቀርብበታል። እንደ ኢትዮጵያ የፍርድ ቤቱ አባል ካልሆነ፣ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ቀርቦ፣ የፀጥታው ምክር ቤት ፍርድ ቤቱ ምርመራ እንዲያደርግና ክስ እንዲመሠርት ሊያደርግ ይችላል፡፡ አሁን ኢትዮጵያኖች የሚንቀሳቀሱበት መንገድ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ እጁን ያስገባና የአለማቀፍ ፍርድ ቤትን ምርመራ እንዲያደርግ ያዛል (ክስ እንዲመሠረት ሊያዘው አይችልም) ጉዳዩ ወደ ወንጀል ከመራ፣ ክሱ በተጐጂዎች ወይም ወኪሎች ሊቀርብ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል አለመሆኗ፣ ወንጀል ከተሰራ ከክስ ሊያስመልጣት አይችልም፡፡ እዚህ ፍትህ አለመኖሩ ከተረጋገጠ፣ በዚህ መልኩ ወደ አለማቀፉ ፍርድ ቤት እንሄዳለን፡፡
ክሱን የምትመሠርቱት ግለሰብ ባለስልጣናት ላይ ነው ወይስ ተቋማቱን ነው የምትከሱት?
ለምሣሌ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን እንደመስሪያ ቤት ነው ወይስ ሚኒስትሩን ነው? እኛ ተቋማቱን ነው የምንከሰው፡፡ እርግጥ ለተቋማቱ ተጠሪዎች አሉ፡፡ ተከሳሾች የሚሆኑት ደግሞ የክልል አስተዳዳሪዎች ብቻ አይደሉም። እንደውም ከፌደራል ጉዳይ መስሪያ ቤት ይጀምራል፡፡ እርግጥ አቶ ኃይለማርያም፤ ይሄ በኪራይ ሰብሳቢዎች፣ በሌቦች የተፈፀመ ነገር ነው፤ መንግስት አያውቀውም ብለው ነው መግለጫ የሰጡት፡፡ ይሄ ተአማኒነትና ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ሃያ ሺህ ሰው ሲባረር አላውቅም ማለት የማንን ጐፈሬ ሲያበጥሩ ነበር ያስብላል፡፡ ፌደራል መንግስት ማወቅ ነበረበት፤ ባያውቅም የግዴታ ማወቅ ነበረበት። አላወቅሁም ካለም አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ማወቅ ይገባው ነበር፡፡ ባያውቅ እንኳ ማወቅ ስለሚገባው በህግ ይጠየቃል። በዚህ መሠረት ክሳችን ከፌደራል መንግስት ይጀምራል፡፡ ወደ ክልል አስተዳደሮች ይሄዳል። ከዚያም ወደ ወረዳ፣ ፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ወደተነካኩት አካላት ይሄዳል፡፡
እንግዲህ ክሱ እንደገለጽኩት ገና አልተረቀቀም፤ በመነጋገርና መረጃ በማሰባሰብ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሀገር ውስጥ ካሉት ፍርድ ቤቶች ምን ውጤት ትጠብቃላችሁ? የመጨረሻ ውጤቱስ ምን ይሆናል ብላችሁ ነው የምታስቡት? እኛ መቸም የምንጠብቀው ህጉ ይተገበራል ብለን ነው፡፡ የወንጀል ህጉም ሆነ ሌሎች ህጐች ይተገበራሉ ብለን ነው የምንጠብቀው፤ ግን የሚሆነው ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ክሳችንን ውድቅ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ ካሣ የሚያስከፍል ወንጀል አላገኘንም ብሎ ክሱን ሊዘጋው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እኛ አስቀድሜ እንዳልኩት ይሄን ክስ ያነሳነው በአለማቀፍ ችሎት የቀረበ እንደሆነ፣ መጀመሪያ በሃገር ውስጥ ፍትህ ለማግኘት ተሞክሯል ወይ ተብሎ ስለሚጠየቅ ነው።
ፍትህ ለማግኘት ሞክሬ ፍትህ አላገኘሁም ወይም መንግስት ክሱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም ካልክ፣ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሊቀበለው ይችላል፡፡ ለዚህ ድጋፍ እንዲሆን ነው ይህን ክስ የምንመሠርተው፡፡ በእውነት ፍትህ በሀገር ውስጥ አግኝተን ለእያንዳንዱ ካሣ ቢከፈል በጣም እገረማለሁ፤ እደነቃለሁ፡፡ ቢሆን ግን እሰየው ነው። ጉዳዩን እንዴት እንደሚያመልጡት አላውቅም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በደል ተፈጽሟል፣ ህግ ተጥሷል ካሉ እንዲሁ ዝም ብሎ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በደል ከተፈፀመ የግድ ለተበዳዩ የሚሆን ካሣ ይከተላል፡፡ ይሄ ሊሆን ግድ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ተጠያቂ ይሆኑበታል፡፡ ወንጀል መሆኑን እያወቁ፣ በደል መፈፀሙን እያመኑ ዝም ብለው ካለፉት፣ ነገ በራሳቸው ቃል ተጠያቂ ይሆኑበታል፡፡

ሰኞ 6 ሜይ 2013

አሜሪካ የሽብር ህጉ አሰጋኝ አለች


አሜሪካ የሽብር ህጉ አሰጋኝ አለች
በሳምንቱ አጋማሽ በእነ አንዷለም አራጌና እስክንድር ነጋ ላይ የበታች ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ መጽናቱን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቃውሞ አሰምቷል። ቪኦኤ ድምጻቸውን ያሰማቸው የሚኒስቴሩ ተጠባባቂ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ቬንትል “ውሳኔው በጸረ ሽብር ህጉ ላይ ያለንን ስጋት ያጠናክረዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና በእነ እንዷለም አራጌ ላይ የተላለፈው ፍርድ በመጽናቱ አሜሪካ በጥልቅ ቅር ተሰኝታለች” ያሉት ቃል አቀባዩ ውሳኔው መንግስት የሚተቹትን ሁሉ ለፍርድ እንደሚያቀርብ አመላካች ነው ብለዋል።
ሰዎች በነጻነት የመናገርና የማሰብ መብት እንዳላቸው የጠቆሙት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ያሰፈረችውን የሰብአዊ መብቶችንና የዲሞክራሲ መብቶችን ማክበር የወደፊቱ ግቧ እንደሆነ አመልክተው “ኢትዮጵያ እነዚህን መሰረታዊ መብቶቻቸውን ስለተጠቀሙ ያሰረቻቸውን በሙሉ እንድትፈታ ደጋግመን እንጠይቃለን” ብለዋል። አሜሪካ በሽብርና ከሽብር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ኢህአዴግን በግንባር ቀደም የምታግዝና ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ የምታቀርብ አገር መሆኗ የሚታወቅ ነው።
የእስክንድር ነጋ ባለቤት ሰግታለች
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው እስክንድር ነጋን ወደ ዝዋይ ማረሚያቤት ወይም ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ለማዛወር መታሰቡን ባለቤቱ ሰርካለም ስጋቷን እንደገለጸች ሪፖርትር አስታውቋል። ጋዜጣው ዝርዝር ባያቀርብም እስክንድር ወደ ዝዋይ ከተዛወረ ባለቤቱና ልጁ እሱን ለመጠየቅ እንደሚቸገሩና ምን አልባትም ችግሩ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። እነ እስክንድር ነጋ ላይ የ18 ዓመት ፍርድ ያጸኑት ዳኛ ዳኜ መላኩ ናቸው።
ዳኜ መላኩ ውሳኔውን ካሳወቁ በኋላ ከፍተኛ የሃዘን ስሜት ችሎቱ ውስጥ ይታይ ነበር። ፍርደኞቹ ወደ እስር ቤት ሲመለሱ ድምጽ አውጥተው ስሜታቸውን የገለጹላቸው እንደነበሩ ሪፖርትር በደፈናው ግለጿል። እስክንድር እጁን ወደ ፈጣሪው በማንሳት “እውነት ተደብቃ አትኖርም” ሲል መናገሩን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል”፡፡
 የሽብር ህጉ የፕሬስ ነጻነትን አውድሟል ተባለ
ባለፈው አርብ በዓለም ተከብሮ የዋለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች “የኢትዮጵያ የሽብርተኞች ህግ የፕሬስ ነጻነትን አውድሟል” አለ። እስረኞች እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል።
ከመግለጫው በተጨማሪ የድርጅቱ የናይሮቢ ጥናት አቅራቢ ላቲቪያ ቤደር የሽብር ህጉ በረቂቅ ደረጃም ሆነ ህግ ሆኖ በስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የመናገር መብትን የሚነፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል። ለቪኦኤ ቃላቸውን የሰጡት ላቲቪያ ድርጅታቸው የምዕራቡን ዓለም የኒዖ ሊብራል ሃሳብ አቀንቃኝ ስለሆነ ነው በተደጋጋሚ ኢህአዴግን የሚቃወመው በሚል ስለሚሰነዘረው ለተጠየቁት “ይህ በማንኛውም መልኩ ርዕዮተ አለማዊ ጉዳይ አይደለም፤ ጥሪያችን ስለ መሰረታዊው የሰብአዊ መብት መከበር ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናደርገው የመብት ጥሪ ነው። በኢትዮጵያ ይበልጥ የሚያሳስበን ጸረ ሽብር የተባለ ሀግ ጸድቆ ጋዜጠኞችን ለማፈን ጥቀቅም ላይ መዋሉ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሂይውማን ራይትስ ዎች አጥኚ ላቲቪያ ቤደር ድርጊቱን ከመቃወም ባለፈ ጫና በመፍጠር የታሰሩት የፖለቲካ አስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ለቪኦኤ በሰጡት ቃል እንዳስታወቁት “አገራቱን በሚረዱ ወዳጅ አገሮችና ለነጻነት የሚቆረቆሩ ተጽዕኖ ፈጥረው እስረኞቹን እንዲያስፈቱ በየጊዜው እንወተውታለን” ብለዋል። በፕሬስ ነጻነት ቀን ይፋ እንደሆነው በኢትዮጵያ 11 ጋዜጠኞች በሽብር ህግ ተከሰዋል። ስድስቱ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ አምስቱ ወህኒ ቤት የሚገኙት ናቸው። ከአምስቱ መካከል ሶስቱ ተፈርዶባቸዋል። ሁለቱ ዮሴፍ ጌታቸውና ሰለሞን ከበደ የፍርድ ሂደታቸውን እየጠበቁ ነው።
ኤርትራ ካሰረቻቸው ጋዜጠኞች መካከል የተገደሉ አሉ
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካሰሯቸው ከ10 በላይ ጋዜጠኞች መካከል እስር ቤት በሚያሳዝን መልኩ የሞቱ እንዳሉ ታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡለት የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ሃላፊ ተናግረዋል። ሃላፊው ለቪኦኤ የናይሮቢ ዘጋቢ እንደነገሩት ኤርትራ ውስጥ የታሰሩት ጋዜጠኞች ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
እስረኞቹ ቤተሰቦቻቸውን አያገኙም፣ የት እንዳሉ በውል አይታወቅም፣ በዜግነት ስዊዲን የሆነው ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ ሁሉም እስረኞች በህይወት ስለመኖራቸው ቤተሰቦቻቸው ተስፋ በቆረጡበት ወቅት ሃላፊው ጉዳዩ ለአፍሪቃ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስለቀረበ ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከታህሳስ 2006 ጀምሮ ኢትዮጵያ ያሰረቻቸውን ተስፋ ልደት ኪዳኔና፣ ተስፋ እግዚ የተባሉትን ሁለት የኤርትራ ተወላጆች ጉዳይም ሃላፊው አንስተዋል “ጋዜጠኞቹ በኮሚኒካዶ ታስረዋል” ያሉት ሃላፊው እስረኞቹ በጠበቃ መወከልና በቀይ መስቀል ሊጎበኙ እንደሚገባ አመልክተዋል። ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤርትራ ዘልቆ ከገባ በኋላ ነበር። በወቅቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከተከፈለና ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ መለስ ጦሩ የያዘውን ቦታ ለቆ እንዲወጣ ማዘዛቸው አይዘነጋም።
በተዛማጅ ዜና በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2012 ብቻ 121 ጋዜጠኞች መገደላቸውን በመግለጽ ለጋዜጠኞች ጥበቃ እንዲደረግ ዩኔስኮ ጥሪውን አቅረቧል። ዩኔስኮ ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ ነው።
የአቶ አስግደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታሰረ
የህወሀትን የበረሀ ትግል ታሪክ የሚዘክረውን ገሀዲ ቊጥር አንድ፣ ሁለት እና ሶስት የሚሉ መጽሀፎችን ከመጻፍ በተጨማሪ በትግራይ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በማጋለጥ የሚታወቁት አቶ አስገደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታስሯል።
የ28 አመቱ የማነ አስገደ ገብረስላሴ የሶፍት ዌር ኢንጂነረግ ምሩቅ ሲሆን፣ በውቅሮ በመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ ነበር። አዲሱን ስራውን ሲጀምር አቶ አስገደ ልጅ መሆኑ በመታወቁ በቅጣት ወደ በረሀ ተመድቦ እንደነበር አባቱ አቶ አስገደ ገልጸዋል።
እናቱ ሻለቃ ግደይ ወ/ሚካኤል ልጃቸውን አያቱ ወደ ሚኖሩበት አዳህላይ ወደምትባል ቀበሌ ለህክምና መውሰዳቸውን ተከትሎ በቀበሌው የሚገኘው ትምህርት ቤት በመቃጠሉ የህወሀት ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው “ትምህርት ቤቱን ያቃጠለው አቶ አስገደ የሚባል የአረና ትግራይ ድርጅት አባል ልጅ ነው” በማለት ሊወነጅሉ ሲሞክሩ ህዝቡ “ሀሰት ነው ” በማለት በመቃወሙ ባለስልጣናቱ ሳይሳካላቸው እንደቀረ አቶ አስገደ ገልጸዋል። ስብሰባው ከተበተነና ህዝቡ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ ፖሊሶቹ ልጃቸውን አስረው መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በእስር ላይ የሚገኘው የ26 አመቱ አክህፎም አስገደ 06 እየተባለ ከሚጠራው ድብቅ እስር ቤት ወጥቶ ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወሩን አቶ አስገደ ገልጸው፣ አለም ባደረገው ጫና ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ልጃቸውን በአይናቸው ለማየት እንደቻሉ እና ከወር በኋላም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አክለዋል።
አቶ አስገደ በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ቤርሙዳ እየተባለ የሚጠራ እስር ቤት መኖሩን አውስተዋል። “የእነሱ ልጆች በህዝብ አንጡራ ሀብት ይማራሉ፣ የኛ ልጆች ይህን የተበላሸ ኑሮ ችለው በኖሩ በእንዲህ አይነት እስር ቤት ማሰቃየት ከዚህ በላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የለም ብለዋል። (ዘገባው የኢሳት ነው)

ማክሰኞ 30 ኤፕሪል 2013

ከፋውንዴሽኑ ጀርባ...(ከተመስገን ደሳለኝ (ክፍል ፩)

ያለ ወቅቱ በደረሰ ዝናብ እየራሰች ያለችው አዲስ አበባ ዛሬም ከመለስ መንፈስ ተፅእኖ ነፃ አልወጣችም፤ ጣራና ግድግዳዎቿ እንዲህ በምስሉ እና በድርጅቱ አርማ መዥጎርጎሯን ያስተዋለ አንድ ቀልደኛ የባህር ማዶ ወዳጄ ‹‹እኔ ከሀገሬ ከወጣሁ በኋላ የኢህአዴግ ዋና ከተማ ሆነች እንዴ?›› ብሎ ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡ በእርግጥ ይህችን ቀልድ ስንፍቃት የምናገኘው ቁም ነገር፡- ከተማዋ በመለስ ውርስ ድንዛዜ ላይ መሆኗ፣ አስተዳደሯም ያለ ቅድመ-ዝግጅት ‹‹አፍርሼ ካልሰራሁሽ›› በሚሉ ካድሬዎች ጫጫታና ሩጫ ልቧን እያጠፋት እንደሆነ፣ አንድ ፓርቲ ተመራጭ፣ አስመራጭ፣ ታዛቢ መሆኑን እና የመሳሰሉትን ነው፡፡ የአቶ መለስ ሞትም ወቅቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ስርዓቱን እያንገጫገጨው ነው፡፡ በግሌ በመለስ ህልፈት ያለማዘን በሥነ-ምግባር የመዝቀጥ ጉዳይ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቴ ሰውየው ክፉ አምባገነን ከመሆኑም በላይ በዙፋኑ ሙጭጭ እንዳለ ህይወቱ በማለፉ ነው፤ ታዲያ ይህንን ሰው እንዴት አድርገን ነበር ከስልጣን ማውረድ የምንችለው? መቼም አቅመቢሶች ከመሆንም አልፈን በተራራና ሸንተረር ሳይቀር የተከፋፈልን ለመሆናችን ከራሳችን በላይ መስካሪ የሚያሻን አይመስለኝም፡፡ እዚህች ጋ ከሩሲያዊው ሌኒን ህልፈት ጋር የተያያዘ አንድ ነገር ትዝ ስላለኝ ልንገራችሁ፡-

እንደሚታወቀው ሌኒን የሩሲያ አብዮትን የመራ ሁነኛ ኮሚዩኒስት ቢሆንም፣ ምሁራዊ ሰውነቱ ከሌሎች አብዮተኞች በእጅጉ ይገዝፍ እንደነበረ ጠላቶቹም ሳይቀር የመሰከሩለት ጉዳይ ነው፡፡ እናም ህልፈቱ ሲሰማ፣ ሩሲያን በአይነ ቁራኛ ይከታተሉ የነበሩ ምዕራባውያን ድንጋጤ አደረባቸው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት የአንዱ መሪም ድንጋጤውን እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር አሉ፡-
.
‹‹ሌኒን ሆይ፣ ባትወለድ መልካም ነበር፤ ከተወለድክ ደግሞ ትንሽ ብትቆይ ይሻል ነበር፤ ምክንያቱም ለማን ትተኽን እንደሄድክ እኔ አውቃለሁና!››

በእርግጥም ሌኒንን የተካው ባለ ብረት መዳፉ ጆሴፍ ስታሊን መሆኑን ስናስተውል የሰውየው ቁጭት ይገባናል፤ ግና ከአስር ወር በኋላም ሊገባን ያልቻለው የእኛው መለስ ለማን ትቶን እንደሄደ ነው፡፡ ከስታሊንም ለባሱት? ወይስ…

የሆነ ሆኖ መለስን ተክተው ከጀርባ የሚዘውሩትን አንጋፋ ታጋዮች ለጊዜው ባሉበት አቆይተን፣ ገብስ ገብሱን እንነጋገር ካልን የኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ወቅቱን የጠበቀ አይደለም የሚለው አያከራክረንም፡፡ የሶስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመትም እንዲሁ፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ነው አገዛዙን ወቅቱን ባልጠበቀ አጀንዳ እንዲወጠር ያደረገው፡፡
ያለወቅታቸው ‹‹ተከሰቱ›› ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉ አጀንዳዎች መካከል ‹‹የመለስ ፋውንዴሽን ምስረታ›› አንዱ ነው፡፡ በእርግጥ መለስ ባይሞት ኖሮ፤ ከሞተም በኋላ ስርዓተ ቀብሩ ትኩረት ባይስብ ኖሮ፤ ከተቀበረ በኋላም ‹‹ሌጋሲው ይቀጥላል›› ባይባል ኖሮ፤ ከሌጋሲው ውስጥም ‹‹ራዕዩ ፈለቀ›› ባይባል ኖሮ… ‹‹ፋውንዴሽን›› ጂኒ ቋልቋል… ባልተከታተለብን ነበር እያልን መቆጨታችን አይቀሬ ነው፡፡

ኢህአዴግ ከመለስ ህልፈት በኋላ ‹‹የመለስ ራዕይ›› እያለ መጮኹ አናዳጅ ብቻ ሳይሆን ‹‹እመራዋለሁ›› ለሚለው ህዝብም ያለውን ንቀት የሚያሳይ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳም ነው ‹‹መለስ ኖሮ፣ ራዕዩ በሞተ›› የሚያስብለው (አሁን የፋውንዴሽኑ ምስረታ ዕለት የተከሰቱ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዮች በአዲስ መስመር ጨርፎ ወደማየቱ እንለፍ)

ፋውንዴሽኑ ደረጃውን የጠበቀ መናፈሻ፣ ቤተ መፅሀፍት (የመለስ ስራዎች በአማርኛ ተተርጉመው ይቀመጡበታልም) እና የተለያዩ መዝናኛዎችን ጨምሮ አስክሬኑ የሚያርፍበት ልዩ ስፍራ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በግልባጩ ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ አዲስ አበባ ነው ከማለት ባለፈ በትክክል የት አካባቢ እንደሆነ ተለይቶ አልተገለፀም፡፡ ሆኖም ለግንባታው ተብሎ በግዴታ በርከት ያሉ መኖሪያ ቤቶች ከይዞታቸው እንደሚነሱ ተነግሯል፡፡ በግሌ ይህ አግባብ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምንም እንኳ በ‹‹ስመ-ልማት›› እየተደረገ ያለውን ማፈናቀል ጠቀሜታው የሀገር ነው ብለን ልንወስደው ብንችልም፤ ይህ ግን… (አጀንዳዬ የፋውንዴሽኑን ጥቅም ወይም ጉጂ ጎን መተንተን ሳይሆን፣ በምስረታው እለት የታዩ ጥቂት ተመንዛሪ ክስተቶችን መተንተን ነው ብያለሁና ወደዚያው አልፋለሁ)

ከዚህ ቀደም የህወሓት አመራር አባላት የመለስ ህልፈትን ተከትሎ በሁለት ጎራ ተቧድነው ‹‹ቀዝቃዛ ጦርነት›› ውስጥ መግባታቸውን ያመላክታሉ ያልኳቸውን ፍንጮች ጠቅሼ መነጋገራችን አይዘነጋም፡፡ (‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት፡- ከአመታት በፊት ዓለም በአሜሪካን እና ሶቭየት ህብረት ፊት አውራሪነት በርዕዮተ-ዓለም ተከፍሎ ሲፋለም ነበር፤ ያለታንክና መድፍ፤ ያለ ተዋጊ ወታደርና ያለ አዛዥ ጄነራል፤ ፍልሚያው ሟችም ሆነ ቁስለኛ፣ አሊያም ምርኮኛ አልነበረውም፤ የርዕዮተ-ዓለምን ልዩነት በበላይነት ለመወጣት ነበርና፡፡ አንደኛው ከሌላኛው ጎራ ከቻለ ሀገርን፣ ካልቻለም ስልጣን ላይ ያለ ግለሰብን ለማስኮብለል ይቀምራል፣ ያሴራል፣ ይሰልላል…፤ ይህንን ሁኔታ ነው የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› (Cold War) ያሉት) ዛሬ ደግሞ የህወሓት የአመራር አባላት በእንዲህ አይነት ጦርነት መጠመዳቸውን ጆሮአችን እስኪግል እየሰማን ነው፤ ልዩነቱ የህወሓት ችግር ርዕዮተ-ዓለምን መሰረት ያደረገ አለመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ህወሓት እንኳን ዛሬ፣ በትልቁ የተሰነጠቀ ጊዜም (በ1993 ዓ.ም.) ርዕዮተ-ዓለም አላጨቃጨቀውም፡፡ የስዬ አብርሃ ወደ አንድነት መግባትም ሆነ፣ የእነ ገብሩ አስራት በ‹‹ሶሻል ዴሞክራሲ›› አስተሳሰብ የሚመራውን አረናን መመስረት የልዩነቱ ምክንያት አልነበረም፡፡ እነገብሩ አረናን ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ፣ በክፍፍሉ ወቅት ‹‹የቡድን አባታቸው›› እንደነበር የሚነገርለት ተወልደ ወ/ማርያም የአዲሱ ፓርቲ መስራች እንዲሆን ሲጠየቅ ‹‹ርዕዮተ-ዓለማችሁ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ ከሆነ ብቻ ነው የምቀላቀለው›› አለ መባሉ መከራከሪያችንን ያጠነክረዋል፡፡

እናም የህወሓት ሰዎች (ከእነ አረጋዊና ግደይ ዘርአፅዮን ዘመን ጀምሮ) ስልጣን እንጂ፣ የፖለቲካ አመለካከት የፀብ መንስኤ ሆኗቸው አያውቅም፡፡ የዘንድሮውም ‹‹ቀዝቃዛ ጦርነት›› ቡድተኝነትና የስልጣን ፍላጎት የፈጠረው ቅራኔ ነው፤ አሊያም ከጆርጅ ኦርዌል ‹‹እንሰሳት ሁሉ እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንሰሳት ግን ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው›› መንፈስ የተናጠቀ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም የፋውንዴሽኑ ምስረታ የእነአዜብን ቡድን የሚያጠናክር ፖለቲካዊ አንድምታ አለው፡፡ በእነአባይ ፀሀዬ ቡድን ውስጥ ከተሰባሰቡት አብዛኛው ለመለስ ያደሩት ፈርተው እንጂ አምነውበት ወይም ወደውት አይደለም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከእነርሱ ቡድን አንድም የአመራር አባል የፋውንዴሽኑ ቦርድ አባል ሆኖ ያልተመረጠው፡፡
የሁለቱ ቡድኖች አሰላለፍ በ‹‹አባይ-ደብረፅዮ››ን እና በ‹‹አዜብ-አባይ ወልዱ›› አስተባባሪነት መሆኑን ሰምተናል (በነገራችን ላይ ከ1983-1993 ዓ.ም ኢህአዴግ ‹‹ሁሉም የግንባሩ አባል ፓርቲዎች እኩል ናቸው፤ ህወሓት ግን ከሁሉም ይበልጣል›› የሚል ያልተፃፈ ህግ ነበረው፡፡ በ93ቱ ክፍፍል አብዛኛው የህወሓት አመራር ከተባረረ በኋላ ደግሞ ያ ህግ ‹‹ሁሉም የኢህአዴግ የአመራር አባላት እኩል ናቸው፤ መለስ ግን ከሁሉም ይበልጣል›› ወደሚል ተቀይሮ ነበር፡፡ አሁን መለስ አልፏል፤ እናም አፍጦ የመጣው ጥያቄ ‹‹ከሁሉም የሚበልጠው ማን ነው?›› የሚለው ነው ብል ማጋነን አይሆንም)
የሆነ ሆኖ በ‹‹የመለስ ፋውንዴሽን ምስረታ›› ወቅት የታዩ ሁነቶች ሁለት ነገር ይፋ አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያው በእነአዜብ ጎራ እነማን እንደተሰለፉ የሚያሳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የጦር አዛዦችም ፍልሚያውን መቀላቀላቸውን ማመላከቱ ነው፡፡

የእነአዲሱ ለገሰ-ብአዴን ገና ከመነሻው ከእነአዜብ ጎን መሰለፉ ይታወቃል፡፡ በፋውንዴሽኑ ምስረታ ወቅትም ይኸው ነው የታየው፡፡ ‹‹የጠቅላይ ሚንስትር መለስ የሌጋሲ ኮሚቴ›› ሰብሳቢ የነበረው አዲሱ ለገሰ፣ የስብሰባውን አካሄድ እየተከታተለ የተጣመመውን ሲያቃና፣ ማጣመም የፈለገውን ደግሞ ሲገፋ ተስተውሏል፡፡ ለምሳሌ የብአዴኑ ካሳ ተ/ብርሃን የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባል ሆኖ መመረጡን ተቃውሞ በእርሱ ምትክ ሌላ ሰው እንዲመረጥ ሲጠይቅ፣ አዲሱ ስራው ጊዜን የማይሻማና ቦርዱን የሚመለከት ነገር ሲኖር ብቻ ውሳኔ መስጠት እንደሆነ ጠቅሶ ካሳ መቀጠል እንዳለበት ሲናገር፣ የመድረክ መሪው በፍጥነት ሃሳቡን ቤቱ እጅ በማውጣት እንዲደግፍ ቀስቅሶ የሰውየውን ተቃውሞ ውድቅ አድርጓል፡፡ በግልባጩ የኦህዴዱ ሙክታር ከድር ሲመረጥ፣ የብአዴኑ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑን መግለፁን ተከትሎ፣ ሙክታር ‹‹ድርጅቶቹ ራሳቸው ለምን አይጠቁሙም?›› ገና ከማለቱ፣ እነአዲሱ ተሽቀዳድመው ‹‹ከአንተ ነው መጀመር ያለበት›› የሚል ግፊት በማድረግ የተመረጠውን ሙክታር ከድርን በ‹‹ድርጅታዊ አሰራር›› ከጨዋታ ውጪ አድርገው፣ አስቴር ማሞን አስገብተዋል፡፡ ሶፍያን አህመድ፣ ቴዎድሮስ አድሀኖም፣ ቴዎድሮስ ሀጎስም የቦርዱ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በመጨረሻም አዜብ የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ሆና ስትመረጥ፣ ምክትሏ ደግሞ የብአዴኑ ካሳ ተ/ብርሃን እንዲሆን ተደርጓል (ሁሉም በእነአዜብ ቡድን ስር ናቸው)
የሁለቱም ቡድን አባላት ‹‹ቃየል››ን እንጂ ‹‹አቤል››ን መሆን አይፈልጉም፡፡ እናም የከፋ ነገር ከመጣ ‹‹ቃየላዊ›› እርምጃዎችን እስከመውሰድ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታም ሊሳካ የሚችለው የታጠቀውን ኃይል ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ ለተንቀሳቀሰ ኃይል ነው፡፡ እናም ከእርስ በእርስ ግጭቱ በበላይነት ለመውጣት እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ (እያሴሩ) ነው (እስከአሁን ባለው ሁኔታ ብአዴን ሙሉ ድጋፍ እያደረገለት ያለው የእነአባይ ወልዱ ቡድን ‹‹የተሻለ›› ሊባል የሚችል የበላይነት አሳይቷል)፡፡ በዚህን ጊዜም ከድንገቴ አደጋ ራስን መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ የግል ጥበቃቸውን አጠናክረዋል፡፡ ለምሳሌ በረከት ስምዖን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠባቂዎቹን ከሁለት ወደ ስድስት አሳድጓል፤ ሁለት ተጨማሪ መኪናዎችም ከፊትና ኋላ ሆነው እንዲያጅቡት አሰማርቷል፡፡

ባለፈው ወር በተካሄደው የግንባሩ ዘጠነኛ ጉባኤ አዜብ መስፍን ‹‹መለስ በስልጣን ላይ እያለ ደሞዙ ስለማይበቃን ብዙውን ጊዜ ከወር እስከ ወር ቀለብ ሳያልቅብን ለመድረስ እንቸገር ነበር›› የሚል አንድምታ ያለው ንግግር አድርጋ ካለቃቀሰች በኋላ ‹‹በደሞዝ (በፔሮል) የሚኖረው ባለስልጣን መለስ ብቻ ነው›› ስትል ማድመጣችን ይታወሳል፡፡ በእርግጥ አዜብ ልታስተላልፍ የፈለገችውን መልዕክት አንጓ ከ‹‹ሰሙ›› ለይተን ስናወጣው ‹‹ቅልጥ ባለ ዘረፋ ላይ የተሰማራችሁ ባለስልጣናት በልዩነታችን ላይ ካልተግባባን ላጋልጣችሁ እንደምችል እንድታውቁት›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የበረከት ‹‹ቴሌቪዥን ጣቢያ››ም ይህንን ሃሳብ በተለየ ሁኔታ ያስተላለፈው ትርጉሙ ሳይገባው ቀርቶ አይመስለኝም፡፡ እነዚህን ኩነቶችም ስንጨምቃቸው ‹‹ህወሓት የውስጥ ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየባሰ ሄዶበታል›› የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሱናል (የአዜብን መልዕክት ባደመጥን ማግስት አራት ኪሎ አካባቢ ከአንድ የአረና አመራር አባል ጋር ድንገት ተገናኝተን ይህንን ሁኔታ አንስተን ስናወራ እንዲህ አለኝ፡- ‹‹እነርሱ ቀልደኞች ናቸው፤ በ1993 ዓ.ም የክፍፍሉ ወቅት መለስ ለቤተመንግስቱ የተመደበው ሁለት ሚሊዮን ባጀት የት እንደሚገባ ሲጠየቅ ‹ይሄ ግቢ እኮ ከምንሊክ ዘመን ጀምሮ ጮማ የለመደ ነው› ብሎ አድበስብሶ አልፎት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በተቀረ አዜብ ‹በመለስ ደመወዝ ብቻ ስለምተዳደር ሽሮና በርበሬ እያለቀብኝ እቸገራለሁ› ማለቷ ከእርሷ ጋር የአቋም ልዩነት ላላቸው የህወሓት አመራር በጎንዮሽ የማስፈራሪያ መልዕክት ከማስተላለፍ የዘለለ ቁም-ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡››)

ሌላኛው በዕለቱ የታየው ዓብይ ጉዳይ መከላከያን የሚመለከተው ነው፡፡ የተመረጡት ሰዎች ውክልናቸው ተቋምን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረትም መከላከያን ወክለው የቀረቡት ጄነራል ሳሞራ የኑስና ጄነራል ሰዓረ መኮንን ናቸው፤ ሳሞራ ሙሉ ጀኔራል ነው፣ ሰዓረ ደግሞ ሌፍቴናንት፡፡ ስለዚህም መከላከያን ወክሎ የቦርድ አባል መሆን ያለበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለ አራት ኮከብ ጄነራል የሆነው ሳሞራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፤ በዚህም ማንም አልተቃወመም-ከጄነራል ሰዓረ በቀር፡፡ ለምን? ሁለቱ ጄነራሎች በግል ስለማይግባቡ? በጥቅም ተጋጭተው? ሰዓረ ‹‹ሳሞራ አይመጥንም›› ብሎ አስቦ? እውነት ጉዳዩ የሁለቱ ብቻ ነው? ወይስ የሰዓረ ተቃውሞ መነሻ ምንድር ነው? …ይህንን ተቃውሞ የግለሰብ አድርገን እንዳንወስደው የሚያስገድዱ ገፊ ምክንያቶች የምላቸውን መጥቀስ እችላለሁ፡- ሁለቱም ተመሳሳይ ተቋም ወክለው መቅረባቸው አንዱ ነው፤ ሁለቱም ወታደሮች መሆናቸው ሌላኛው ነው (የወታደር ዲሲፕሊን በተለይም የኢህአዴግ ወታደራዊ አደረጃጀት ከታች ወደላይ ተቃውሞን እንደማያበረታታ ማንም አይጠፋውም) ሆኖም ‹‹የሳሞራን የቦርድ አባል መሆን በምን አያችሁት?›› ሲል የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል፡፡ በተጨማሪም ሰዓረ ያ ሁሉ ህዝብ በተሰበሰበበት አዳራሽ የሳሞራን ስም ሲያነሳ በሰራዊቱ ደንብ መሰረት በማዕረግ ስሙ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው በዕለቱ የተከሰተው ነገር ሁለቱ ጄነራሎች እያራመዱት ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ነው የሚለውን መከራከሪያ የሚያጠናክረው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚከታተል የሠራዊቱን ወሳኝ ጄነራሎች ከጎኑ ማሰለፍ የቻለ ማንኛውም ቡድን ዳዊት የማይኖርበት ጎልያድ ሊሆን እንደሚችል አይጠፋውም፡፡ እናም ይህ ኩነት አንደኛ ዓመቱን ሊደፍን እየተቃረበ ላለው የሁለቱ ቡድኖች ፍጥጫ የመቋጫው ቀናት እየቀረበ እንደሆነ የሚያመላክት ይመስለኛል (በነገራችን ላይ በመከላከያ ውስጥ ከሳሞራ ቀጥሎ ባለ የስልጣን ወንበር ላይ የምናገኘው በተመሳሳይ ማዕረግ የሚገኙ ሶስት አቻ ጄነራሎችን ነው፡፡ ሁለቱ ጄነራል አበባው ታደሰ እና ጄነራል ሰዓረ መኮንን ናቸው፡፡ እነዚህ ጄነራሎች አንም ቀን ተስማምተው ሰርተው አያውቁም፡፡ ስልጣናቸውና ኃላፊነታቸው ተመሳሳይ ቢሆንም አበባው የሚመራው ቢሮ በተሰሚነት ጎላ ያለ ነው፡፡ …ሳሞራ በግልፅ ‹‹በዚህ ቀን›› ብሎ ባይናገርም ከኤታማዦር ሹምነቱ የመልቀቅ እቅድ አለው፡፡ በአሁኑ አሰላለፍም ከእነአዜብ ጎን ይመደባል፡፡ አበባውና ሰዓረ ደግሞ የእርሱን ቦታ ይፈልጉታል፡፡ አበባው የሳሞራ የቅርብ ሰው ነው፡፡ ከሰዓረ ጋር ያለው ግጭትም ከሳሞራ ጋር ካለው ግንኙነት ጋር ይያያዛል)

የሆነ ሆኖ ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት››ን በሚመለከት ተጨማሪ ነጥብ ልጥቀስ፡፡ ከቀኑ ስብሰባ በኋላ በሸራተን ሆቴል ለፋውንዴሽኑ ገቢ ማሰባሰቢያ አንድ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ የክልል አስተዳደሮች ‹‹አቅማችን ይመጥናል›› ያሉትን ያህል የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከሁሉም ቀድሞ አንድ ሚሊዮን ብር ያዋጣው እነአዲሱ ለገሰ እንደግል ንብረታቸው የሚቆጥሩት ‹‹ጥረት ኢንዶውመንት›› ሲሆን፣ የአላሙዲ ‹‹ሚድሮክ ኢትዮጵያ››ም ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገብቷል፡፡ ትኩረቴን የሳበው ግን ይህ አይደለም፤ ገቢና ወጪው ከህዝብ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ኦዲተርም አይን የተሰወረ ነው የሚባለው እጅግ ባለፀጋው የህወሓቱ ‹‹ኤፈርት›› በዕለቱ ሰባራ ሳንቲም ለማዋጣት ቃል አለመግባቱ እንጂ፡፡ ለምን? ኤፈርት በእነአዜብ ስር ከመሆኑ አኳያ ለትችት ያጋልጠናል በሚል? ወይስ ገና ያልተደረሰበት እንቆቅልሽ ይኖር ይሆን? ጥያቄው ይህ ነው፡፡ የዚህን መልስ ጨምሮ ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች ሲፍታቱ ልዩነቱን እና አሰላላፉን ያጎሉታል ብዬ አስባለሁ፡፡

እንደመውጫ

በሀገራችን ላይ ‹‹ለውጥ አመጣለሁ›› የሚለው የተቀውሞ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ‹‹ይህን ዓመት አያልፍም!›› በሚል ሟርት ሲጠመድ፣ ድርጅቱ ግን ሃያ ሁለተኛ ዓመቱን ሻማ ለኩሶ ሊያከብር ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ዘንድሮም የመለስን ሞት ወይም የግንባሩን መከፋፈል ብቻ ስናመነዥክ የቋመጥንለት ለውጥ የውሃ ሽታ ሆኖ ነገሩ ሁሉ ‹‹የሞትንም እኛ፤ ያለንም…›› እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡

እናም በላያችን ላይ እያመፀ ያለውን ፍርሃት ማረቅ ያስፈልጋል፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነት ያስፈልገናል፤ ከኢህአዴግ በኃላም ሊኖር ስለሚገባው ለውጥ መነጋገር ያስፈልጋል፤ ስርዓቱ ሀገር የሚጠቅም አለመሆኑን በበቂ ሁኔታ ገብቶናልና፣ የርዕዮተ-ዓለም ወይም የፖሊሲ ድክመቱን በምክንያትና አመክንዮ (ሎጂክ) እየተነተንን ብቻ ተጨማሪ ጊዜ ማባከኑ ፋይዳ የለውም፡፡ ፋይዳ ያለው በሰላማዊ መንገድ አደባባይ ወጥቶ የስርዓት ለውጥ ማድረግ ነው፤ ትንተናዎችም ይህ አይነቱን እንቅስቃሴ ወደ መሬት ማውረድ የሚቻልበት እና ከኢህአዴግ በኋላስ? የሚለው ላይ ሲያተኩሩ ነው፡፡

:ከተመስገን ደሳለኝ

ማክሰኞ 23 ኤፕሪል 2013

ህዝብ እየተፈናቀለ ያለው ከፌዴራል መንግስት በሚሰጥ ትዕዛዝ መሆኑን መኢአድ አሳወቀ


“የአገሪቱ ህዝብ በተለይ የአማራው ህዝብ ከሥራውና ከመኖሪያ እየተፈናቀለ ያለው በክልል ወይም በወረዳ ባለሥልጣናት ውሳኔ ሳይሆን ከፌዴራል መንግስት በሚሰጥ ትዕዛዝ ነው፡፡” ሲል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ/አስታወቀ፡፡
መኢአድ ይህንን ያሳወቀው ባለፈው አርብ ረፋዱ ላይ በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ፓርቲው ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት በመሄድ የኢትዮጵያ መንግስት በዘር ማጥፋት ወንጀል ለመክሰስ እየተዘሰጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡



መኢአድ “በአማራ እና በአፋር ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የአምባገነኖች እና ዘረኞች ጥቃት እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀል በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡” በሚል ርዕስ ባለ አራት ገጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው በመግቢያው ላይ “ኢህአዴግ የምኒሊክ ቤተመንግስትን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ በአማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ዘመቻ ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በበደኖ፣በአርባጉጉ፣በአረካና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጭፍጨፋ ፈጽሟል፡፡ ጥቃቱ ለ22 አመት ቀጥሎ ዛሬም በጉራፈርዳና በአፋርና በቤኒሻንጉል የዘር ማጥፋት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡”  በማለት ይዘረዝራል፡፡ መግለጫው በመጨረሻም “እንዲመለሱ ለተደረጉ ወገኖች ተገቢው የህግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ለደረሰባቸው አካላዊና ሞራላዊ ጥቃት ተገቢው ካሳ እንዲከፍል፣ ድርጊቱን የፈፀሙትን ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ ጥላቻንና ክፍፍልን የሚያራግቡ ኃይሎች ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው ባስቸኳይ እንዲታቀቡ፣ ሕዝብን በዘርና በኃይማኖት ከፋፍሎ በማፋጀት ሥልጣንን ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ላለፉት 21 ዓመታት ደም ያፋሰሰ በመሆኑ ባስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን ብሏል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው ፕሬዘዳንት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል፣ የፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የቀጠና አደራጅ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ናቸው ፡፡ መግለጫው በንባብ ከተሰማ በኃላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቆዎች መልስ ተሰቷል፡፡ ኢ/ር ኃይሉ በሰጡት መልስ “ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉት ሰዎች በወረዳ ባለሥልጣናት እንደሆነ በመግለጽ ስህተቱ ታርሞ ተፈናቃዮች ወደ ሥፍራቸው ተመልሰዋል ይባላል፡፡ ሐሰት ነው፡፡ የዘር ማጥፋት ዘመቻው የሚከናወነው የፌዴራል መንግስት በሚሰጠው ትእዛዝ መሆኑን መረጃ አለን፡፡ ህዝቡን እየደበደበ እያሰረ የሚያፈናቅለው ልዩ ኃይል የሚባለው ጦር ነው፡፡ ልዩ ኃይልን የሚያዘው ደግሞ ፌዴራል መንግስት ነው፡፡ ተፈናቃዮች ፍኖተ ሠላም በሠፈሩበት ወቅት ውሃ አጥተው የወንዝ ውሃ ሲጠጡ ነበር፡፡ ብዙዎቹ በተቅማጥ እየተሰቃዩ ናቸው፡፡ አሁን ወስደው ያስገቧቸው ቤታቸው በፈረሰበት፤ መዝጊያቸው ተነቅሎ በተወሰደበት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ቻግኒ ያሉትን አልመለሷቸውም ፍኖተሠላም ያሉትንም የወሰዳቸው የአገር ውስጥና የውጭ ጩኸት ስለደረሰባቸው 2 ተቃውሞውን ለማብረድ ተብሎ እንጂ በድርጊቱ ተፀጽተው አይደለም መንግስት በግልጽ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ሄደን ለመክሰስ የሚያስችለን ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን ፡፡ ለመክሰስ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ኮስማና መስለን ብንታይም ይህንን ለማድረግ አቅም አለን፡፡ ከጉራፈርዳ ተፈናቅለው በእኛ ጽ/ቤትና በአዲስ አበባ ከተማ ተጠልለው የነበሩት ተፈናቃዮች ለሊት አፍነው የት እንዳደረሷቸው አይታወቅም፡፡ በህይወት መኖር አለመኖራቸውም መረጃ የለም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ታሪኩ በበኩላቸው በሰጡት መልስ በቅርቡ ከቤኒሻንጉል ክልል የተፈናቀሉትን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡ “ በአሶሳ ኩምሩክ 60 ኢንቬስተሮች አሉ፡፡ 60ዎቹም የቀድሞ የህውሃት ታጋዮች ናቸው፡፡ በአካባቢው ከ200 በላይ ትግሪኛ ተናጋሪዎች አሉ፡፡ በርካታ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችም ይገኛሉ፡፡ ማንም የነካቸው የለም፤ አማርኛ ተናጋሪዎችን እየለቀሙ እየደበደቡ እያሰሩ ከአካባቢው ያባርራሉ፤ ባንባሲ ያለው ካድሬ አካባቢውን ከአማራ ሳላፀዳ ዕረፍት የለኝም፤ እያለ በግልጽ ይፎክራል፡፡ ሰብስበው ጭድ የተከመረበት ቦታ ሜዳ ላይ አስረዋቸዋል፡፡ ጭዱን ለኩሰው በእሳት ሊፈጁን ነው ብለው ሥጋት ላይ ናቸው፡፡ አንድ ተፈናቃይ የኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ተጠቃሚ ነኝ በፖሊስ ሄጄ መድኃኒት ላምጣ ብሎ ቢጠይቅ አትሄድም ድብን በል ተብሎ ተከልክሏል፡፡ ስለዚህ ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት መሄዳችን የማይቀር ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ረቡዕ 17 ኤፕሪል 2013

የቀድሞዋ የህወሀት ታጋይ ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ተቹ


ወ/ሮ አዜብ መስፍን የባለቤታቸው ወርሃዊ ደመወዝ አነስተኛ እንደነበር በመጥቀስ በኢህአዴግ ጉባዔ ላይ ያደረጉትን ስሜታዊ ንግግር የሕዝብን የማመዛዘን ችሎታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነበር ሲሉ የቀድሞ የህወሃት ታጋይ ወ/ት አረጋሽ አዳነ ተቹ፡፡ወ/ት አረጋሽ በዛሬው ዕለት በአዲስአበባ ለንባብ በበቃው “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ በሰጡት ሰፊ ቃለምልልስ ላይ የወ/ሮ አዜብን ንግግር አስመልክቶ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል፡፡አቶ መለስ በፔሮል 6ሺ500 ብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ብቸኛው መሪ እንደነበሩ ወ/ሮ አዜብ መናገራቸውን በመጥቀስ ጋዜጣው ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ
“የኢትዮጽያን ሕዝብ መቼም የማመዛዘን ችሎታ ያለው ነው፡፡የማስተዋል ችሎታ አለው፡፡ያውቃል፡፡የወ/ሮ አዜብ አባባል ግን የሕዝብን የማመዛዘን ችሎታ በትክክል የሚመዝን አድርጌ አልወሰድኩትም፡፡ምክንያቱም ሕዝቡ እውነታው ይህ እንዳልነበር ያውቃልና” ብለዋል፡፡አያይዘውም ጠ/ሚ/መለስ ቤተመንግስት ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ቤተመንግስት ደግሞ የራሱ አስተዳደር ያለው ትልቅ ተቋም ነው፡፡ራሱን የቻለ ባጀት አለው፡፡ይህ ባጀት የት እንደሚውል የማይታወቅ አይደለም፡፡ቤተመንግስት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚተዳደሩበት፣የሚኖሩበት ነው፡፡እንግዶች የሚያስተናግዱበትና የሚጠሩበት በጀት አላቸው፡፡ይህ አሁንየተፈጠረ ሳይሆን በፊትም የሚታወቅ ነገር ነው፡፡በየስብሰባው በሚሄዱበት ጊዜ ውጪ አገር ከሆነ በውጪ ምንዛሪ ይከፈላቸዋል፡፡የአገር መሪ ስለሆነ የአልጋና የምግብ ሊከፍሉ አይችሉም፡፡ስለዚህ ምን ያህል የውጪ ገንዘብ መሰብሰብ እንደሚቻል መገመት ይቻላል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እነአቶ መለስ ልጆቻቸውን ውድ የተባለ ት/ቤት እንደሚያስተምሩ ያስታወሱት ወ/ት አረጋሽ አዳነ ከዛሬ 12 እና 13 ኣመት በፊት ለአንዱ ልጃቸው ብቻ በዓመት 35 ሺ ብር ይከፍሉ እንደነበር አውቃለሁ ብለዋል፡፡ሶስቱም ልጆቻቸው በዚህ ሁኔታ እንደተማሩ ቢታሰብ ገንዘቡ በዓመት 100ሺ ብር ይከፍሉ ነበር ማለት ነው ካሉ በኃላ ይህን
በስድስት ሺ ብር ደመወዝ ሊያደርጉት አይችሉም ብለዋል፡፡በተጨማሪም ኢንዶውመንት የሚባለው ግዙፉ የኤፈርት ሐብት በወ/ሮ አዜብ ቁጥጥር ስር መሆኑም ወ/ት አረጋሽ በማስታወስ በ6 ሺ ብር ገቢ ብቻ ኖረዋል የተባለውን አጣጥለውታል፡፡


ኢሳት ዜና:-

ማክሰኞ 16 ኤፕሪል 2013

ገዢው ፓርቲ ያልጠበቀውን የምርጫ ውጤት አገኘ

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ያለምንም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባደረገው ምርጫ ያልጠበቀውን ውጤት ማግኘቱን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሰባሰብናቸው መረጃዎች አመለከቱ።

ምንም እንኳ ኢህአዴግ ምርጫውን ከ99 እስከ 100 ፐርሰንት እንደሚያሸንፍ ቢጠበቅም ህዝቡ በምርጫ ካርዶች ላይ ያሰፈረው መልእክት ግን ገዢው ፓርቲ ያልጠበቀውና ያለሰበው ነበር እንደ ታዛቢዎች አገላለጽ።

በአንዳንድ አካባቢዎች የቀበሌ እና የወረዳ ሹሞች የምርጫ ታዛቢዎች እና የድምጽ ቆጣሪዎች የተመለከቱዋቸውን ነገሮች በሚስጢር እንዲጠብቁ ሲያግባቡዋቸው መታየታቸውን ተዛቢዎች ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ ከገቡት የምርጫ ወረቀቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ባዶ ነጭ ወረቀት፣ ሌሎቹ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቁ ነበሩ። የሀይማኖት ነጻነታችን ይከበር፣ የታሰሩ መሪዎች ይፈቱ፣ የኑሮ ውድነቱ አስመርሮናል፣ ኢህአዴግ በቃህ ውረድ፣ ለውጥ እንፈልጋለን የሚሉት ጽሁፎች በዚህ የምርጫ ጣቢያ በብዛት ከተላለፉት መልእከቶች መካከል ይጠቀሳሉ እንደ አይን እማኞች አገላለጽ።

በሰሜን ሸዋ አጣየ ከተማ በሚገኝ አንድ ጣቢያ ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ምንም ምልክት ሳያደርግ ነጭ ወረቀት ብቻ ማስገባቱን አንድ ታዛቢ ተናግረዋል::

በአዲስ አበባ አንድ የምርጫ ጣቢያ ደግሞ ጥቂት መራጮች ብቻ ድምጽ የሰጡ ሲሆን፣ ሌሎች መራጮች ገዢውን ፓርቲ የሚሰድቡ እና ለውጥን የሚጠይቁ መልእክቶችን ማስገባታቸውን በቦታው የነበረው ታዛቢ ገልጿል::

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለከተማ ዋልያ ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረው ምርጫ ደግሞ አስመራጮች ሰው በማጣታቸውን ቁርስ እንብላ በማለት የምርጫ ጣቢያውን ዘግተው መሄዳቸውን ተከትሎ፣ በግዳጅ ለመምረት እንዲወጡ የተገደዱት ሰዎች፣ ጣቢያው ተዘግቶ በማየታቸው ወደ የቤታቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ጉዳዩን ሰምተው የመጡት የኢህአዴግ ካድሬዎች ከአስመራጮች ጋር አምባጋሮ ፈጥረው ነበር።

በአዋሳ ከተማ ደግሞ ምርጫው ከመካሄዱ ከአንድ ቀን በፊት የኢህአዴግ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ የምርጫ ካርድ ያካሂዱ ነበር። በጎንደር ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ እና አደባባይ ኢየሱስ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ካርድ ሲሰጥ መዋሉን ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዛሬ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

ምርጫ ቦርድ በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ 954 ወረዳዎች ፣ በተዘጋጁ 44 ሺ 509 የምርጫ ጣቢያዎች ፥ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን እጩዎችም ለውድድር ቀርበው 90 በመቶው ድምጹን መስጠቱን ገልጿል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ህብረተሰቡ በምርጫው ያሳየው ተሳትፎ የጎላ እንደነበር ገልጸው ተሳትፎው ህዝቡ ስለምርጫና ስለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለው ግንዛቤ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳየበት ነበር ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የወጡ የምርጫ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ከ99 እስከ 100 በመቶ አሸንፎአል። በዚህ ምርጫ ገዢው ፓርቲ በ2002 ዓም ይዞት የነበረውን የ99 ነጥብ ስድስት በመቶ ውጤት ረከርድ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የተገኘውን ሪከርድ ሁሉ የሚያሻሽልና ለዘመናትም ሳይሰበር እንደሚቆይ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።


ኢሳት ዜና:

ሐሙስ 11 ኤፕሪል 2013

በፍኖተሰላም ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲመለሱ እየተደረገ ነው


ዛሬ ሊነጋጋ ሲል ከ20 በላይ መኪኖች የፍኖተ-ሰላም ከተማን ማጨናነቃቸውን የተናገሩት ተፈናቃዮች፣ ከብር-ሸለቆ የመጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዞን እና ከወረዳ ፖሊስ አባላት ጋር በመተባበር፣ ተፈናቃዮቹ ወደ መኪኖቹ እንዲገቡ አዘዋል።
ጥሪው ድንገተኛ የሆነባቸው ተፈናቃዮች የሚያደርጉት ጥፍቷቸው ሲላቀሱ ፣ ወላጆቻቸውን ተከትሎም ህጻናት ሲያለቅሱ ይታዩ እንደነበር የአይን እማኞች ይናገራሉ።
አንድ ሌላ ተፈናቃይ ዛሬ ስላጋጠማቸው ነገር ሲናገሩ ” ሰው በተወለደበት አገር ይህን አይነት በደል ይደርስበታል” ብየ አላስብም ነበር ብለዋል።
ወደ መጣበት ቦታ ለመመለስ በመጠባበቅ ላይ የነበረ አንድ ወጣት ፣ ቤቱ መቃጠሉን ቢገልጽም መንግስት እንዳደረገ ያድርገን በማለት እንደሚሄድ ገልጿል።
ወደ መጣበት ቦታ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ ተፈናቃይ፣ ለምን እንደማይመለስ ሲጠየቅ ” በእርሱና በልጆቹ ላይ ለሚደርስበት ጉዳት ዋስትና ስላልተሰጠው” መሆኑን ገልጿል። የ2 ልጆች አባት መሆኑን የገለጸው አርሶአደሩ የልጆቹ እናት በህመም ምክንያት ራቅ ወዳለ ቦታ በመሄዷ፣ ልጆቹን ይዞ ለመመለስ አለመድፈሩን ተናግሯል።
በዛሬው እለት 16 መኪኖች ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ያቀኑ ሲሆን፣ በነገው እለትም ተጨማሪ ሰዎች ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተፈናቃዮች ስለሚያቀርቡት አቤቱታ የዞኑን የጸጥታ ሀላፊ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት ለማነጋገር ሳይቻል ቀርቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአማራ ተወላጆች ላይ የተወሰደውን እርምጃ በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፎችናንና የተለያዩ ዝግጅቶችን እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ስርክአዲስ ታየ ተጨማሪ ዘገባ ልካለች።


ኢሳት ዜና: