ሰኞ 8 ኤፕሪል 2013

በጀሞ የጋራ መኖርያ መንደር አንድ ኮንዶሚኒየም ለመፍረስ እያዘነበለ ነው










ባለሙያዎች አስተዳደሩን ተጠያቂ ያደርጋሉ
• አስተዳደሩ ነዋሪዎችን አስወጥቷል
• አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መንስዔውን እንዲያጠና ተጠይቋል
በአዲስ አበባ አስተዳደር የቤቶች ልማት ፕሮጀክት የተገነባው የከተማዋ ትልቁ የጋራ መኖርያ መንደር በሆነው ጀሞ መንደር ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለ አንድ ኮንዶሚኒየም ለመደርመስ ወደኋላ እያዘነበለ ነው፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በደረሰው ጥቆማ መሠረት የተባለውን ሕንፃ በመመልከት በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ የጀሞ የጋራ መኖርያ መንደር በ1.3 ቢሊዮን ብር የተገነባ ሲሆን፣ 10 ሺሕ የተለያዩ መጠንና ክፍሎች ያላቸው ቤቶች የሚገኙበት፣ እንዲሁም 50 ሺሕ ያህል ነዋሪዎችን የሚያስጠልል ነው፡፡ በዚህ ጀሞ ቁጥር አንድ ተብሎ በተሰየመው መንደር ውስጥ ብሎክ ቁጥር 220 የጋራ ሕንፃ ግን ከሌሎቹ በአካባቢው ከተገነቡ ቤቶች ተለይቶ ለመውደቅ በማዘንበል ላይ ይገኛል፡፡
ዕጣ ደርሷቸው የሕንፃው ባለቤት የሆኑ ነዋሪዎች በሕንፃው የውስጥ ክፍሎች ያስተዋሉትን መሰነጣጠቅና አጠቃላይ የሕንፃውን ወደ አንድ ጐን መስመጥና ማጋደል አሳስቧቸው ቤቱን ላስተላለፈላቸው የከተማዋ አስተዳደር አሳውቀዋል፡፡ የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎችም አካባቢውን በመጐብኘት የነዋሪዎችን ሥጋት የተቀበሉ መሆናቸውንና በዚህ ሳምንት ውስጥም ለሁሉም ተለዋጭ ቤት እንዲሰጣቸው መወሰኑን አረጋግጠናል፡፡ የችግሩ መንስዔ፣ ተጠያቂውስ ማን ሊሆን ይችላል? መፍትሔውስ? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ካሳ ወልደ ሰንበትን ብንጠይቅም፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን መመለስ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት የችግሩ መንስዔ ገና ያልተጠና መሆኑን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ነዋሪዎቹ እንዲለቁ የተደረገ መሆኑን፣ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ጥናቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ካሳ፣ ኮንዶሚኒየሙን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን መናገር የሚቻለው ከጥናቱ በኋላ ነው ብለዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ግን በግንባታና ተያያዥነት ባላቸው የሥራ ዘርፎች ላይ ባለሙያ የሆኑና በዚህ መንደር የቅድመ ግንባታ ጥናቶች ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የችግሩ መንስዔ የአስተዳደሩ የቁጥጥር ቸልተኝነት ሊሆን እንደሚችል ይስማማሉ፡፡ ሰሞኑን ‹‹የከተማ ሕዝቦች አገልግሎት በኢትዮጵያ›› በሚል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክት፣ የሕንፃ ግንባታና የከተማ ልማት ኢንስቲትዩት የኢኮ ሲስተም ዕቅድና ማኔጅመንት ኃላፊ ዶክተር ቁምላቸው የሺጥላ ስለጀሞ የጋራ መንደር ሙያዊ ሂሳቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ዶ/ር የሺጥላ እንደሚሉት፣ ጀሞ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሠረት ለከተማ ግብርና እንዲሆን የተከለለና ለግብርና ምቹ የሆነ የከርሰ ምድር ውኃ ያዘለ አካባቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከማስተር ፕላኑ ውጭ ለጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታ እንዳዋለው ተናግረዋል፡፡
ከዶ/ር የሺጥላ ጥናት መረዳት የሚቻለው፣ አስተዳደሩ ከማስተር ፕላኑ ውጭ ለመኖርያ ቤቶች ግንባታ አካባቢውን ሲመርጠው የከርሰ ምድር ውኃ ያዘለና ለግንባታ ምቹ ያልሆኑ ጥቁር አፈር ያለበት አካባቢ መሆኑን እየተረዳ እንደሆነ ነው፡፡
በሥፍራው ተገኝተው የተባለውን ሕንፃ በመጐብኘት አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎችም ግንባታው ከመካሄዱ በፊት ጥቁር አፈሩ ሙሉ ለሙሉ መውጣት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ጥቁር አፈር ከወጣ በኋላም ቢሆን በሌላ የግንባታ አፈር መሞላት እንደሚገባው ያስረዳሉ፡፡ በአካባቢው የሚገኘው የከርሰ ምድር ውኃም በክረምት ወቅት የበለጠ የሚሞላ በመሆኑ ይህንን ያገናዘበ ግንባታ ማካሄድ የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በጀሞ መንደር ግንባታ ከመካሄዱ በፊት በአስተዳደሩ ተቀጥረው የጂኦቴክኒካል ጥናት ላይ ከተሳተፉ ድርጅቶች መካከል ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የግል ድርጅት በበኩሉ፣ በተደረገው ጥናት መሠረት የግንባታ ሥራውን ለማካሄድ ለአስተዳደሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዳቀረበ ይህም ከሌሎቹ ድርጅቶች ጋር ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል፡፡ ነገር ግን የተጠቆሙትን የመፍትሔ ሐሳቦች ለመተግበር እንዲሁም ተጨማሪ ጥናት ለማካሄድ አስተዳደሩ የመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ ሊቸገር እንደሚችል ድርጅቱ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች የተከፈላቸው ገንዘብ አነስተኛ እንደነበር በዚህም ሳቢያ ሙሉ ጥናት ማከናወን እንዳልቻሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ ገልጸዋል፡፡
ግንባታውን የፈጸመው ኮንትራክተርን የሚቆጣጠረው አማካሪ ድርጅትም በቁጥጥር ወቅት ቸልተኝነት አሳይቶ ሊሆን ስለሚችል አስተዳደሩ አማካሪ ድርጅቱ ያሳለፋቸውን የግንባታ ውሳኔዎች ወደኋላ ተመልሶ ሊመረምር ይገባል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚደረገው ጥናት ከተጠቀሰው ሕንፃ ውጭ በአጠቃላይ በመንደሩ ላይ ሊያተኩር ይገባል ሲሉም ይመክራሉ፡፡ http://www.ethiopianreporter.com/

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ