• ‹‹የራዲዮ ጣቢያውን አድሎአዊነት ያረጋገጠ ነው›› አቶ ስለሽ ፈይሳ
• ‹‹ፓርቲዎች ኢህአዴግ በቀደደው ቦይ እንዲፈስሱ የሚያስገድድ ነው›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
(ነገረ-ኢትዮጵያ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ (ኤፍ ኤም 96.3) ሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫ ቅስቀሳ እንዲተላለፍለት ለራዲዮ ጣቢያው የላከው የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ የተጠቃለሉትን የፓርቲውን ፕሮግራም አካል የሆኑ ሀሳቦች ማውጣትና ማጀቢያ ሙዚቃውን ማስፈቀድ አለበት በሚል የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራሙን መለሰ፡፡
ራዲዮ ጣቢያው ፓርቲው በቅስቀሳ ፕሮግራሙ ካካተታቸው ሀሳቦች መካከል ‹‹ሀገራችን ዛሬ በቀሪው ዓለም የምትታወቀው በእርስ በርስ ጦርነት ነው›› የሚለው ለአመጽና ለሁከት የሚያጋልጥ ነው በሚል እንዲሁም፤ ‹‹ህዝቧ የዘር፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶችን ተቀብሎ ለበርካታ ዘመናት ተቻችሎ የኖረ ቢሆንም ዛሬ ግን እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያይና አንድነቱ እንዲላላ እየተደረገ ነው›› የሚለውን የቅስቀሳውን አካል ብሔር፣ ብሔረሰቦችን የሚያጋጭ ወይንም እርስ በርስ ግጭት የሚያስነሳ፣ አመፅና ጦርነት የሚቀሰቅስ ነው በሚል እንዲስተካከል ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ ገልጾአል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቅስቀሳ ፕሮግራሙ የታጀበበትን ሙዚቃ የድምጻዊ ፍቃድ ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ ብሏል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ የቅስቀሳ ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲስተካከሉ የላካቸው ሀሳቦች የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ያፀደቃቸው፣ የፓርቲው ፕሮግራም አካልና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የተቀበላቸው መሆናቸውን ጠቅሶ ራዲዮ ጣቢያው በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ቅድመ ምርመራ እያደረገ ነው ሲል ወቅሷል፡፡ ሙዚቃውን በተመለከተም ‹‹መብቱ የሙዚቀኛው እንጂ የራዲዮ ጣቢያው አይደለም፡፡ ሙዚቀኛው ደስተኛ ካልሆነ ካስተላለፍነው በኋላ ሊከሰን ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ጣቢያው የሚያገባው ነገር የለም›› ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ‹‹ሀሳቡ ፕሮግራሙ ላይ እንዳለ ሆኖ በእርስ በርስ ጦርነት ነው የምትታወቀው የሚለውን ሀሳብ 99.6 በመቶ ፓርላማውን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ እንኳን አልካደውም፡፡ በፓርላማ አሸባሪ የተባሉ 3 ታጣቂ ቡድኖችን ጨምሮ በርካታ መሳሪያ ያነሱ ቡድኖች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ስላለ የውጭ መንግስታት የአየር በረራ ክልከላ እስከማድረግ ደርስዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ሪፖርቶችም ሆነ ፓርላማው ግጭቶች እንዳሉ አምኗል›› ሲልም ራዲዮ ጣቢያው አስተካክሉ የሚላቸው ጉዳዮች ችግር እንደሌለባቸው አስረድቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ (ኤፍ.ኤም 96.3) የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ፕሮግራም ላይ የሰፈሩትን ሀሳቦች እንዲቀይር መጠየቁ ቅድመ ምርመራ ነው ያለው አቶ ዮናታን ‹‹ድርጊቱ ፓርቲዎች አቋማቸውን እንዳያንፀባርቁና ኢህአዴግ በቆፈረው ቦይ እንዲፈሱ የሚያስገድድ ነው›› ብሏል፡፡ ‹‹ድርጊቱ ሰማያዊ ፓርቲ ከተቋቋመለት አላማ በፍጹም የሚጻረር ስለሆነ የምንቀበለው አይደለም›› ያለው አቶ ዮናታን ‹‹በእነዚህ ምክንያቶች ሰማያዊ ፓርቲ ፕሮግራሙ ላይ ያስቀመጣቸውን መርሆች ኤፍ.ኤም 96.3 ምክንያት አይቀይርም›› ብሏል፡፡
በሚናገሩት ቋንቋ መነሻነት ብዙ ዜጎች በተደጋጋሚ ከቀያቸው እንደሚፈናቀሉ፣ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ዘርን ያማከለ ሹመት ምክንያት በርካቶች የጎሪጥ እንደሚተያዩ፣ የጎሳ ፌደራሊዝሙ ለተደጋጋሚ ግጭት መዳረጉን መንግስት በሚያሰራቸው ጥናቶችም ጭምር መረጋገጡን የገለጹት የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሽ ፈይሳ በበኩላቸው፣ ራዲዮ ጣቢያው የቅስቀሳ ፕሮግራሙ ላይ እንዲቀየሩ የጠየቃቸው ሀሳቦች በመረጃ የተደገፉ ናቸው ብለዋል፡፡ አቶ ስለሽ አክለውም ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ፕሮግራሙ ላይ ያለውን ሀሳብ አውጣ እየተባለ ቅድመ ምርመራ ሲደረግበት ኢህአዴግ ግን ተቃዋሚዎችን ‹‹ህገ-ወጥ›› ከሚላቸው አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እየከሰሰና እያንቋሸሸ ቅስቀሳ እያካሄደ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ራዲዮ ጣቢያው በግልጽ አድሎአዊነቱን እያሳየ እንደሆነ ትልቅ ማስረጃ ነው›› ብለዋል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ