እሑድ 13 ማርች 2016

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በአገራችን እየተነሱ ያሉ ግጭቶች መኢአድን በእጅጉ አሳስቦታል!

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
I. የኢህአዴግ መንግሥት በ1983 ዓ.ም ሥልጣን ከመያዙ በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በተወለደበት ቀዬ፣ በዘሩና በቋንቋው ሳይሆን በኢትዮጵያዊ ማንነቱ በመኩራት በአንድነትና በመተባበር የአገሩን ዳር ድንበር ሲያስከብርና አገሩን ሲገነባ ኖሯል፡፡ በ1983 ዓ.ም የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት በተደነገገው በሕገመንግሥት አንቀጽ 39 ላይ ባወጣው የራስን እድል በራስ መወሰን እንከመገንጠል መብት በመገፉፉት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ይልቅ ለተወለደባት ቀበሌና ለወጣበት ዘር፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ አብሮ በመሥራትና አብሮ በማደግ ከመበልጸግ ይልቅ ተበታትኖ የጐሪጥ ስለሚተያይ በአገራችን ዕድገት ላይ መሰናከል በመፈጠሩ በችግር ላይ ይገኛል፡፡
ይህ የመለያየትና የመከፋፈል በሽታ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ እያደገ መጥቶ ዛሬ ልንወጣው በማንችልበት የገደል አፋፍ ላይ ጥሎናል፡፡
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ሕዝብ የቀረበው ጥያቄ በወጉና በባህሉ መሠረት ሊመለስ ባለመቻሉ ጥያቄው ወደ ሕዝባዊ አመፅ ተቀይሮ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡ ይህ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ መመለስ አለመቻልና በድብደባ፣ በእስራትና በግድያ ለማብረድ መሞከሩ አመፁን ከማባባሱና ጉዳቱን ከማስፋት ውጭ የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለም፡፡
ከዚህ ቀደም ከአለን ተሞክሮ እንደምንረዳው እንደነዚህ ያሉ ቅራኔዎች በሚከሰቱበት ወቅት እየተናቁና ትኩረት እያጡ በመቆየታቸው በአገራችንና በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ቀውስና ውድቀት ሲያስከትሉ ቆይተዋል፡፡
ከኢህአዴግ መንግሥት ባለሰልጣናት የሚነገረው የቅራኔው መነሻ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው የሚል ነው፡፡ ይህ አባባል መልካም ሰው ከአገር አጥፍቶ መልካም አስተዳደርን አመጣለሁ ማለቱ ስህተት ቢሆንም ቅሉ በአገሪቱ ውስጥ እየተነሱ ያሉ ቅራኔዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት የዘለሉና ብዙ ድርብርብ ጥያቄዎችን ያዘሉ ለመሆኑ መንግሥት ሊጠራጠር አይገባውም፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ያለው የኑሮ ውድነት፣ ሙስና፣ ፍትሀዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍልና የመለካም አስተዳደር እጦት በአገሪቱ ተንሰራፍተዋልና ነው፡፡
ስለዚህ፡-
1. በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሰላማዊ በሆነ ውይይትና መግባባት እንዲፈታ አጥብቀን እንጠይቃለን፤
2. እስራት፣ ድብደባውና ግድያው ቅራኔውን ከማባባሱ ውጭ የሚያመጣው ፋይዳ ስለማይኖር በአስቸኳይ ቆሞ ለጉዳዩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት
II. በአንዳንድ አላዋቂ እና ፅንፈኛ የፖለቲካ ሰዎች የተደረጉ ውሳኔዎች በፍቅርና በአንድነት ለብዙ ሺ ዓመታት አብሮ የኖረውን ወንድማማች ሕዝብ ወደማይመለስ ቅራኔ እየከተቱት ይገኛሉ፡፡ ይኸም በወልቃይት ጠገዴ፣ በፀለምትና በሴቲት ሁመራ አካባቢ የሚገኘው መሬት በአማራ ክልል ወይስ በትግራይ ስር ነው? በሚል የተነሳው ጥያቄ ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ወደከፋ ግጭት ውስጥ ለማስገባት ከጫፍ ላይ ደርሶ ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ግጭቶች በአሁኗ ኢትዮጵያ አዲስ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ፡- በቦረናና በጉጂ፣ በሀሪና በኮንሶ፣ በደቡብና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ በደቡብ ክልሎች መካከል በመሬት ይገባኛል ስበብ ተመሳሳይ ቅራኔዎች ተነስተው ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረትም ወድሟል፡፡ ይሁን እንጂ ሁኔታው በሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ሰፊ ውይይት እንዲፈታ ተደርጓል፡፡ በወልቃይትና በሁመራ ምክንያት የተነሳው ቅራኔ ግን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በቅራኔ ብቻ በመጦዝ ላይ በመገኘቱ መኢአድን እጅግ አድርጐ አሳስቦታል፡፡ ይሀ ሁኔታ ማንንም የማይጠቅም ስለሆነ ጊዜ ሳይሰጠው በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡
ከዚህ ላይ የህውሓትና የትግራይ ክልል አመራሮች በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ፍንጮችን ሲሰጡ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በኩል አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ ሲሰጥ ተሰምቶ አያውቁም፡፡ ይኸም እወክለዋለሁና እመራዋለሁ ለሚለው ሕዝብ ትክክለኛውን አቅጣጫ ሊያመላክተው አለመቻሉ ከትዝብት ላይ የሚጥለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ስለዚህ መኢአድ ለሁለቱም ክልል አመራሮችና የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያሳስበው፤
1ኛ. በሁለቱ ወንድማማች መካከል የከፋ ቅራኔ ሳይፈጠር የሚመለከታችሁ አካላት ሕግንና ከዚህ ቀደም የነበረን የአመጣጥ እና የአሰፋፈር ታሪክን መሠረት በማድረግ በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲያፈላልጉለት፡፡
2ኛ. የፌዴራሉ መንግሥትም ቅራኔውና ብጥብጡ እንስከሚነሳ ዝም ብሎ ከመመልከት ይልቅ በእነዚህ ሁለት ወንድማማች ህዝቦች አመጣጥና አሰፋፈር ታሪክ ላይ በመመርኮዝ የመፈትሄ ሀሳብ መሰጠት ይቻል ዘንድ እንዲያመቻች አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
3ኛ. ከዚህ በተጨማሪ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሁኔታው በህግ በሞራልና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት እንዲያደርጉ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
III. የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለኢትዮጵያ የተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር ፈር ቀዳጅ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መኢአድ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ ከውስጥና ከውጭ በሚነሱ ችግሮች የተነሳ መጠነ ሰፊ የሆነ ፈተና ሲጋረጥበት መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ መሪውን ክቡር ኘሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ጨምሮ ብዙ አመራሮቹና አባላቱ በውስጥ አርበኞች ጠቋሚነትና መስካሪነት ታስረዋል፣ አካላቸው ጐድሏል፣ ተገድለዋልም፡፡ መኢአድን ለማፍረስ ብዙ ቡድኖች በተለያዩ አካላትና በተለያዩ ጊዜያት ተቋቁመዋል፡፡ ነገር ግን መኢአድን ለማዳከም የቻሉ ቢመስልም ሊያጠፉት ግን አልቻሉም፡፡ አሁንም በቅርብ ጊዜ በቀድሞው የመኢአድ ኘሬዝዳንት የግል ሹፌርና በሌሎች ምንደኛ ግለሰቦች የሚመራው ቡድን በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደለል ፓርቲውን ለማዳከም ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የአራዳ ምድብ ችሎትን በሀሰት ቃለ-መሐላ በማሳሳት የፓርቲውን ማህተም አሳግደው ኘሬዝዳንቱን አግደናል በሚል ለአንድ ሳምንት ብዙ አካላትን አሳስተው ሲያወናብዱ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፍ/ቤቱ በአደረገው ማጣራት ሕገወጦች ናቸሁ በማለት ፋይሉን ዘግቶ አባሯቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ በጣም ያሳዘነንና ያስቆጨን ኘሮፌሰር አሥራት በተቀመጡበት ወነበር ላይ የቀድሞ የመኢአድ ኘሬዝዳንት የግል ሹፌር የሆኑት በኘሬዝዳንትነት ተሰየምኩ በማለት ኃላፊነቱን ለመውረስ መምጣታቸው ነው፡፡
ከዚህ ላይ በጣም ያሳዘነንና ተስፋችንን ያሟጠጠው አንዳንድ በሕዝብ ዘንድ ተነባቢነት ያላቸው ጋዜጦችና የሬዲዮ ባቢያዎች እነዚህ ህገወጥ ግለሰቦች የሰጧቸውን ወረቀት በመያዝ ሁኔታውን ሳያጣሩ ሚዛናዊነቱን ያጣ ዘገባ ማድረጋቸው ነው፡፡ እንደዚህ ያለው ድርጊትም በአገራችን ዲሞክራሲን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ስለሚኖረው ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል እንላለን፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ ግለሰቦች በአሰራጩት የሀሰት ኘሮፓጋንዳ የተነሳ፤
1. በአገር ውሰጥ የምትገኙ የመኢአድ አባላት እና ደጋፊዎች እንዚህ ህጋዊ ያልሆኑ ግለሰቦች ባሰራጩት ውዥንብር ሳትደናገጡ በፅናትና በአንድነት ከፓርቲያችሁ ጋር እንድትቆሙ፤
2. በውጭ የምትገኙ የመኢአድ አባላትና ደጋፊዎች እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች እየሰሩት ያለው የውሸት ውዥንብር በመፍጠር ፓርቲውን ለማዳከም ስለሆነ በውዥንብሩ ሳታዝኑና ሳትጨነቁ የተለመደ አብሮነታችሁ ከፓርቲያችን እንዳይለይ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
3. እንደነዚህ ያሉ ጥቅመኞች ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በመቀበል ፓርቲዎችን ለማፍረስ ጥረት ማድረጋቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የየፓርቲዎቹ አባላትና ደጋፊ እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦችን በአንድነት ሊያወግዟቸውና ሀይ ሊላቸው ይገባል፡፡
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
አዲስ አበባ
የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ