ረቡዕ 9 ማርች 2016

ፍርድ ቤት የመኢአድ ፕሬዚዳንት የፓርቲውን ማኅተም እንዳይጠቀሙ አሳልፎት የነበረው ዕግድ ተነሳ

ፍርድ ቤት የመኢአድ ፕሬዚዳንት የፓርቲውን ማኅተም እንዳይጠቀሙ አሳልፎት የነበረው ዕግድ ተነሳ


የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሦስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ የፓርቲውን ማኅተም እንዳይጠቀሙ አሳልፎት የነበረውን የዕግድ ውሳኔ የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ አነሳ፡፡
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቱ ማኅተሙን እንዳይጠቀሙ ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የዕግድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ያደረገው የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት አባላት በፕሬዚዳንቱ ላይ ያቀረቡት ክስ ነበር፡፡
ፓርቲው ዕገዳው እንደተነሳለት ያሳወቀው ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡ ፓርቲውን የማዳከም ሥራ ከውስጥም ከውጭም ተጠናክሮ እንደቀጠለበት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው በመግለጫው ወቅት ገልጸዋል፡፡
‹‹መኢአድ ለኢትዮጵያ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ፓርቲው ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ ከውስጥና ከውጭ በሚነሱ ችግሮች የተነሳ መጠነ ሰፊ የሆነ ፈተና ሲጋረጥበት ቆይቷል፡፡ አሁንም በቅርቡ የግል ጥቅማቸውን ባስቀደሙ ግለሰቦች የሚመራ ቡድን በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመደለል ፓርቲውን ለማዳከም ብዙ ጥረት አድርጓል፤›› በማለትም የቀረበባቸው ክስ ፓርቲውን ለማዳከም በተነሱ ኃይሎች እንደተቀነባበረ አመልክተዋል፡፡
የመኢአድ ላዕላይ ምክር ቤት ጥር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው መሐሪ ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ እስከሚካሄድ ድረስ ማገዱንና ቀዳሚው ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አንድርያስ ኤሮ ፓርቲውን እንዲመሩ መወሰኑን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባውና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ሙሉጌታ አበበ ይህን ውሳኔ ክፉኛ የተቹትና የተቃወሙት ሲሆን፣ ይህን ውሳኔ ያስተላለፉት ግለሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ከፓርቲው የተባረሩና ራሳቸውን ከፓርቲው ያገለሉ ግለሰቦች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
‹‹ፕሬዚዳንቱን አግደናል የሚል ውሳኔ ያሳለፉት ግለሰቦች 16 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ 16 ግለሰቦች መካከል ደግሞ ከፓርቲው ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት የነበራቸው አራቱ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ ውሳኔው የፓርቲውን መተዳደርያ ደንብም ሆነ የአብዛኛውን አባላት ይሁንታ ያገኘ አይደለም፤›› በማለት አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹የመኢአድ የምክር ቤት መቀመጫ ብዛት 105 ነው፡፡ እንዴት ነው 16 ግለሰቦች ፕሬዚዳንቱን ማውረድ የሚችሉት?›› በማለት ውሳኔው የአካሄድ ችግር እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እንኳን 16 ግለሰቦች 105ቱም የምክር ቤቱ አባላት ቢገኙና ቢስማሙም ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቱን የማውረድ ሥልጣን የለውም፡፡ በፓርቲው ደንብ መሠረት ፕሬዚዳንቱን የሚያስቀምጠውም ሆነ የሚያነሳው ጠቅላላ ጉባዔው ነው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱን ያገደው ቡድን በምክንያትነት ከሚያስቀምጣቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ፕሬዚዳንቱ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም የሚል ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን መቼ ያካሂዳል በማለት ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ አቶ አበባው ሲመልሱ፤ ‹‹ምንም እንኳን ቀኑን ባንወስንም በመጋቢት ወር ውስጥ ለማድረግ ዝግጅት አጠናቅቀናል፤›› ብለዋል፡፡
ፓርቲው ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶች በሰላማዊና በድርድር እንዲፈቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ አቶ አበባው ‹‹የከፋ ቅራኔ ሳይፈጠር የሚመለከታቸው አካላት ሕግንና ከዚህ ቀደም የነበረን የአመጣጥና የአሰፋፈር ታሪክን መሠረት በማድረግ በአስቸኳይ መፍትሔ ይፈለጉለት፤›› ብለዋል፡፡
በሽግግሩ መንግሥት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) በሚል በታዋቂው የሕክምና ባለሙያ በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የተመሠረተው ፓርቲ በ1994 ዓ.ም. ለሁለት ሲሰነጠቅ፣ አንዱ ቡድን መኢአድ በሚባል ኅብረ ብሔራዊ ቅርፅ ወዳለው ፓርቲነት ከተለወጠ በኋላ በኢንጂነር ኃይሉ ሻውል እየተመራ በ1997 ዓ.ም. ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የነበረው ቅንጅት ቁልፍ አባል እንደነበር ይታወሳል፡፡
መኢአድ በሌሎች የቅንጅት የቀድሞ አባላት ከተመሠረተው አንድነት ፓርቲ ጋር ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የተገመቱና በአንድ ወቅትም ወደ ውህደት ሊያመሩ ነው ተብሎ የተነገረ ቢሆንም፣ የምርጫ ቦርድ በውስጥ ክፍፍል ጉዳይ ላይ የሰጠው ውሳኔ እጅግ በተዳከመ ሁኔታ ለምርጫው እንዲቀርቡ አድርጓል ተብሎ ይተቻል፡፡
ከምርጫ ቦርድ ውሳኔ በኋላ ይህን መሰል ውዝግቦች ከሁለቱም ፓርቲዎች መስማት የተለመደ ሲሆን፣ ፓርቲዎቹ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርጉም አይስተዋልም፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ