ሐሙስ 4 ኤፕሪል 2013

ብአዴን የት ናት…?

ባለፈው ሰሞን ከደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ "አማሮች ስለሆናችሁ ወደ ሀገራችሁ ሂዱ" ተብለው ሲፈናቀሉ የነበሩ ዜጎች ጉዳይ ምን እንደደረሰ ምንም የረባ ነገር ሳንሰማ ይሄው ዛሬ ደግሞ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል "አማሮች ውጡ" ተባሉ ሲባል እየሰማን ነው፡፡ የአሁኑ ይባስ እንዲሉ፤ የአሁኑ ደግሞ ጭራሽ ተፈናቃዮቹ ሲጓዙበት የነበረው መኪና አደጋ ደርሶበት ስደተኞቹ በሙሉ ህይወታቸው ተቀጥፏል፡፡ 

በየአመቱ ህዳር አስራ አንድ ልደቷት የምታከብር አማራውን እወክላለሁ የምትል ብአዴን የተባለች ፓርቲ አለች፡፡ 
ብአዴንን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርች አንዱ የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን ይመሯታል፡፡ በስራቸውም በርካታ አንጋፋ ታጋዮች ይገኛሉ፡፡ አቶ አያሌው ጎበዜም አቶ አዲሱ ለገሰም አንዱ እና ሁለቱ ናቸው፡፡ ሌሎችም ብዙ አበል የሚበሉ አባሎች አሏት… ብአደዴን!

እንግዲህ በተደጋጋሚ የክልሉ ተወላጆች በዘራቸው የተነሳ ወደ ሀገራችሁ ሂዱ እየተባሉ ከተለያዩ ክልሎች ሲባረሩ ብአዴን ምን እያደረገች ነው… መቼም ወግ ነውና ልጠይቅ ብዬ ነው አንጂ… ብአዴንም ሆነች መላዋ የትዳር አቻዎቿ በጥቅሉ እነ ኢህአዴግ ጥያቄ ለመመለስ ጊዜ ያላቸው አይመስሉም፡፡ አነርሱቴ፤ ርስ በርስ ተቃቅፈው የሞቀ ፍቅር እየሰሩ ነው፡፡

ሳስባት ብአዴን የኢህአዴግ ፍቅር አለቅጥ አስክሯታል፡፡ "በልጆቿ" ላይ የሚያደርሰው መከራም ከነጭርሹ ሊታያት አልቻለችም፡፡ ፍቅር እውር ነው ብቻ ሳሆን እውርም ያደርጋልና እነሆ ብአዴን ልጆቿን ረስታለች፡፡ የት እንደሆኑ ምን እንደሆኑም አልሰማችም፤ አላየችምም፡፡

ብትሰማም ጆሮ ዳባ ብላለች፡፡ ብታም አይኔን ግንባር ያድርገው ብላለች፡፡

ጥያቄዬ አጭር ናት፤ ብአዴን የት ናት…!? ብኤዴን የማናት…!? ለመሆኑ ደህና ናት…!? ስራዋስ ምን ይሆን…!?
ብአዴን ሆይ ልደት ማክበር፤ መጨፈር እና ከጎረምሳው ኢህአዴግ ጋር ሲቃበጡ ማደር… በቃ ይሄው ነው ያንቺ ሞያ…!? እባክሽ ተንፍሺ…!

እንበል ይሆን… !?


Source:Abe Tokichaw

ሰኞ 1 ኤፕሪል 2013

ኩዌት ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሠራተኞችን አልቀበልም አለች


ኩዌት በቅርቡ የሕክምና ምርመራ እንዲከናውኑ ተብለው በተመለመሉ አዳዲስ ክሊኒኮች አማካይነት አልፈው የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞችን ወደ አገሯ እንደማታስገባ አስታወቀች፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የኩዌት ኤምባሲ መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ኩዌት ወደ ባህረ ሰላጤው አገሮች የሚሄዱ ሠራተኞች የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ በቅርቡ ለተመለመሉ አዳዲስ ክሊኒኮች ዕውቅና አልሰጠችም፡፡
ኩዌት ኤምባሲ በዚሁ ደብዳቤው እንደገለጸው፣ ራሱ ሌላ ማረጋገጫ ደብዳቤ እስካልጻፈ ድረስ የክሊኒኮችን ሥራ የሚያስተባብረው ጋምካ የተባለው አስተባባሪ ተቋም አንድም ተመርማሪ ሠራተኛ በቅርቡ ምርመራ እንዲያካሂዱ ወደተመደቡ የጤና ማዕከላት እንዳይልክ አሳስቧል፡፡
የባህረ ሰላጤው አገሮች ማኅበራት (Gulf Cooperative Council) አባላት ሳውዲ ዓረብያ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ባህሬን፣ ኳታር፣ የመንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ የእነዚህ አገሮች የጤና ሚኒስትሮች በበኩላቸው የራሳቸውን ማኅበር አቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትሮቹ ማኅበሩ ባለሙያዎችን ወደ አዲስ አበባ በመላክ በከተማው ውስጥ የሚገኙትን ክሊኒኮች ከገመገመ በኋላ አልአፍያ ከፍተኛ ክሊኒኮች፣ አልያንስ ሜዲካል ክሊኒክ፣ ቶዝ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ወሰን ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ቤተዛታ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ኦአይሲሶ ስፔሻላይዝድ ክሊኒክ፣ ሜዲገልፍ የጤና አገልግሎትን የመረጠ ሲሆን፣ ኩዌት ለጊዜው በእነዚህ ክሊኒኮች ተመርምረው የሚመጡ ሠራተኞችን እንደማትቀበል ገልጻለች፡፡
ከዚህ በፊት በጤና ሚኒስትሮቹ ተመርጠው ከግንቦት 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ባህረ ሰላጤ አገሮች ለሥራ የሚሄዱ ሠራተኞች ጤና ለመመርመር አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት አርሾ ሜዲካል ላቦራቶሪ፣ ቢታንያ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ሃሌሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ኬቲ ቅዱስ ገብርኤል ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ሰንቴ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ዘንባባ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ዛክ ከፍተኛ ክሊኒክና ሳይመን ከፍተኛ ክሊኒክ ነበሩ፡፡

ተማሪዎች ብሪትሽ ካውንስልና መንግሥትን ለመክሰስ ዝግጅት እያደረጉ ነው


ከእንግሊዙ ካምብሪጅ ኮሌጅ ዲግሪ ለማግኘት በማሰብ በአገር ውስጥ በትብብር ሥልጠናውን ይሰጥ ከነበረ ተቋም የተልኮ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና የተመረቁ መንግሥትን ጨምሮ፣ ተቋሙንና የብሪትሽን ካውንስልን ፍርድ ቤት ለማቆም እየተዘጋጁ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡
ዘመን ዲቨሎፕመንት ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተሰኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በድንበር ዘለል ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ዕውቅና ተሰጥቶት፣ 400 ያህል ተማሪዎችን ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ካለፈው ታኅሳስ ወር 2005 ጀምሮ ዕውቅናው መሰረዙን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ውሳኔው ኤጀንሲው ምክንያት ያደረገው ከካምብሪጅ ኢንተርናሽናል ተሰጥቶኛል ያለውን የታደሰ የዕውቅና ማረጋገጫ፣ ዘመን ኢንስቲትዩት እንዲያቀርብለት ቢጠይቅም ሊቀርብለት ባለመቻሉ እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡
ይሁንና ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ቢጽፍም ትምህርት ሚኒስቴር ግን የኤጀንሲው ውሳኔ እንዲፀና በማድረግ የትምህርት ተቋሙ የተጠየቀውን ዕውቅና እንዲያመጣ አሳስቧል፡፡ ይልቁንም ካምብሪጅ ኮሌጅ በእንግሊዝ አገር በማስትሬት ዲግሪ መርሐ ግብሮች ሥልጠና ለመስጠት ዕውቅና የተሰጠው ነው በማለት ምስክርነቱ ሰጥቶ የነበረው ብሪቲሽ ካውንስል ሁለት ጊዜ መሰል ማረጋገጫ መስጠቱ ስህተት እንደሆነ በመግለጽ ይቅርታ መጠየቁን የተገነዘበው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ተቋሙ በድንበር ዘለል ትምህርት ዘርፍ ሥልጠና እንዳይሰጥ ብቻ ሳይሆን መዝግቦ ሲያስተምራቸው የነበሩትንም ተማሪዎች ተመጣጣኝ ወደሆኑ ሌሎች ተቋማት እንዲያዛውር፣ በትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የተወሰነበትን ውሳኔ አጠናክሮበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በዘመን ኢንስቲትዩት ለተመረቁ ተማሪዎች ዕውቅና እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
እንዲዘጋ የተወሰነበት ዘመን ኢንስቲትዩት በምትኩ ብሪቲሽ ስኩል ኦፍ ቢዝነስ ኤንድ ፋይናንስ ከተባለ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን በማስታወቅ፣ ወደሌላ ተቋም እንዲያዛውራቸው የተባሉትን ተማሪዎች በዚህ ተቋም ዕውቅና በሚሰጠው አኳኋን ለማስተማር እንዲፈቀድለት ጠይቆም ውድቅ ተደርጎበታል፡፡
እነዚህን ውሳኔዎችና ሒደቶች ሲከታተሉ የቆዩት ተማሪዎች ግን ዕውቅና ከሌለው ተቋም ለተገኘ ዲግሪ ዕውቅና ይሰጠዋል በማለቱና በአግባቡ ዕውቅናውን ሳያጣራ የድንበር ዘለል ሥልጠና እንዲሰጥ ለዘመን ኢንስቲትዩት ዕውቅና በመስጠቱ ጭምር ኤጀንሲው መከሰስ እንደሚገባው በመመካከር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘመን ኢንስቲትዩት ላደረሰባቸው የጊዜ፣ የገንዘብና የሞራል ኪሳራ በፍርድ ቤት እንደሚጠይቁ መወሰናቸው ሲታወቅ፣ ብሪቲሽ ካውንስልም ዕውቅና የሌለውን ተቋም ዕውቅና እንዳለው በማስመሰል ማረጋገጫ መስጠቱ፣ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ እንደሚሆን ከተማሪዎቹ መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡
ወደሌሎች የትምህርት ተቋማት እንዲዛወሩ የተባሉት ተማሪዎች በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንት በማስተር ኦፍ አርትስ ዲግሪ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል የተመዘገቡ በመሆናቸው፣ በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ ከሚሰጡት ጥቂቱ ብቻ በሁለቱ ተቋማት እንደሚሰጡ በማረጋገጣቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹም ከሁለቱ ተቋማት የሚገኘውን ዲግሪ ለማግኘት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዲግሪ ለማግኘት ብለው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ሲማሩ እንደቆዩም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግሥት እዚህ አገር በመስጠት ላይ ካሉ የአሜሪካ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሊያስቀጥልላቸው ይገባ እንደነበር በመግለጽ ይወቅሳሉ፡፡
ethiopian reporter

እጅግ አስደንጋጭ ቭዲዮኢትዮጵያውያን በመደበኛነት ከቆሻሻ ገንዳ የተደፉ ምግቦችን በመሰብሰብ ይመገባሉ::


እጅግ አስደንጋጭ ቭዲዮኢትዮጵያውያን በመደበኛነት ከቆሻሻ ገንዳ የተደፉ ምግቦችን በመሰብሰብ ይመገባሉ::



ከ100.000 በላይ ኢትዮጵያውያን በመደበኛነት ከቆሻሻ ገንዳ የተደፉ ምግቦችን በመሰብሰብ ይመገባሉ::ይህ የሚያሳየው ሃገራችንን የሚያስተዳድረው የወያኔ ጁንታ 11% እድገት አለ እያለ ቢሆንም ዉሸት መሆኑን ነው ::ወያኔ እየደረሰበት እያለው ኪሳራ መውድቂያው በመሆኑ ህዝቡን ለከፋ ችግር ዳርጎታል::https://www.youtube.com/watch?feature=player_embedded&v=MNY_7cUDHcU

አዲሱ የስም ማጥፋት ዘመቻ በሎሚ መፅሔተ በልዕልና አዘጋጆች ላይ



መጀመሪያም በፍትህ አዘጋጀች ከዛም በአዲስ ታይምስ መታተም ከጀመረች ጀምሮ በስርአቱ ሎሌዎች ፍትህን ለማዘጋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም ከዚህም ውስጥ የአዲስ ዘመን ገፅ 3፣ አይጋ ፎረም፣ዋልታ ፣ እንዲሁም በተረጴዛዋ ሟርተኛ ሚሚ ስብሃቱ የሚመራው ዛሚ ፌፍ ኤም ከነዚህ ውስጥ ይገኛሉ፡፡የሚገርመው የአሁኑ ዘመቻ ከበፊቱ ለየት ያለ መሆኑን ፍንጭ የደረሳቸው የልዕልና አዘጋጀች በልዕልና ጋዜጣ ቅፅ 1 ቁጥር 4 አርብ መጋቢት 13 2005 ባወጡት ፅሁፍ እንዲህ ብለው ነበር‹‹ከዚህ ቀደም ከተለመደው የመፈረጅ ፣ የማስፈራራት ፣ የማጥላላት ፣የማንኳሰስ ዘመቻ ይህንን ለየት የሚያደርገው እንደዚህ ቀደሙ በአዲስ ዘመን፣ በአይጋ ፎረም፣እና ዛሚ ሬዲዮ ጣቢያ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ፤ በአዲሱ ዘመቻ በ‹‹ግል(ነፃ)›› ስም የሚታተሙ መፅሔቶችንም በተባባሪነት መጠቀምን የሚጨምር እንደሆነ የልዕልና ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡›› እያለ ይቀጥልና በመጨረሻም
‹‹ ልዕልና ነፃ ፕሬሱን ለማፈን ለሚደረገው ኢህአዴግ መራሹ ዘመቻ ‹‹ ነፃ ፕሬስ ››ን እንደ ሽፍን በመጠቀም መፅሔታቸውን በማከራየት የሚተባበሩትንም ሆነ በአዲስ ዘመን እና በአይጋ ፎረም ላይ በብዕር ስም ይህንኑ የአፈና ተግባር የሚፈፅሙትን እየተከታተለች ለአንባቢን ታቀርባለች ፡፡››
የሚገርመው ይህ ፅሁፍ በወጣ በነጋታው ቅዳሜ ነው ሎሚ መፅሔት ‹‹ለተመስገን ደሳለኝ የኢህአዴግ ማስተንፈሻ ማን ነው? በሚል ርዕስ አዲሱን ዘመቻ የጀመሩት ከዚህ ቀደም ካነበብኳቸው የዘለፋ ፅሁፎች የዚኛው በጣም ስልታዊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ፡፡ ይህም የልዕልናን አዘጋጆች ከገዢው ፓርቲ ጋር እያገናኘ የፃፈው ነው፡፡;ይህን ማንም ሊጠረጥረው የማይችለው እና የተረጋገጠ እውነት የሆው ነገር አምባገነኑ ስርአት የነዚህን አይነት ጋዜጦች መኖር ከናካቴው አይፈልግም የልጁ መከራከሪያ ምን ያህል ዜሮ እንደሆነ የሚያረጋግጠው ጋዜጣው ብርሃንና ሰላምን በመሰሉ ማተሚያ ቤቶች በአነስተኛ ዋጋ ማሳተም እንዳይችሉ አድጎ በተለየ ይዘት እና በውድ ዋጋ እንዲያሳትሙ አስገድዷቸዋል፣ እንዲሁም 30 ሺህ ኮፒ ከታተመ ቦኋላ እንዳይወጣ አድርጎ አቃጥሎታል ፡፡ ይህም የሚያረጋግጠው ስርአቱ እንደ ፍትህ አይነት ጋዜጣዎችን መመልከት አለመፈለጉን ያሳያል፡፡ምንልክሳልሳዊ ብሎግ
ሌላው ደሞ እነእስክንድር ነጋ ጋዜጣ እንዳያወጡ ታግደው ፣የአወራምባ ታይምስ አዘጋጆች አውራምባ ታይመስ ከተዘጋች ቦኋላ ተሰብስበው ሄደው ሌላ ጋዜጣ ለማተም ሳይፈቀድላቸው ለነፍትህ አዘጋጆች ግን በየ 6 ወር በአዲስ ጋዜጣ የሚመላለሱት እነሱ ማን ሆነው ነው አይነት ከስርአቱ ጋር የማያያዝ ነገር ያንፀባርቃል ፡፡ ይህንን ማንም የሚያወቀው ሃቅ ይመስለኛል፡፡ እስክንድር ነጋ የታገደው ዛሬ አይደለም እሱምኖ ሆነ ባለቤቱ የታገዱት ምርጫ 97 ቦኋላ ነው እንጂ ዛሬ አይደለም ልጁም እንዲህ ማለቱ ለተነሳለት የቅጥፈት ተግባር ማለትም ከ97 ቦኋላ የተከፈቱትን አዲስ ነገር ፣ አውራምባ ታይምስ ፣ ፍትህ ፣ አዲስ ታይምስ እንዲሁም አሁን በነብስ ያለችውን ልዕልናን ገዢው ፓርቲ በማስተንፈሻነት እንደሚጠቀምባቸው ለመግለፅ ፈልጎ ነው ይህም የሎሌ እና የአድርባዮች ተላላኪ መሆኑን በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ 4ቱ በህትመት የሉም ታድያ እንዴት ሆነው ነው በህትመት ሳይኖሩ ማስተንፈሻ የሆኑት ደሞም እነዚህ ጋዜጦች በህትመቱ ለመዝለቅ የቻሉት ስርአቱን በማስገደድ ነው እንጂ ስርአቱ ፈልጎ እንዳልሆነ ሰይጣንም ያውቀዋል፡፡ 
ሌላው ደሞ ሌሎች ተከልክለው ፍትህ በአዲስ ታይመስ አሁንም በልዕልና ይመላለሳሉ የሚል ነው ፡፡ ይህም ቢሆን ምንም እውነትነት የሌለው ነው፡፡ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የፍትህ አዘጋጆች ፍትህ የሚሰደዱ እግሮች የሏትም ብለው በቁርጠኝነት መነሳታቸው ለስርአቱ አንንበረከክም ማለታቸውን የሚያሳይ ነው ፤ ይህም አንዱ በር ቢዘጋ በአንዱ መምጣታቸው ነገር ለፕሬሱ የሚያስብ ሰው ቢሆን በመልካም ጎኑ ሊያየው በተገባ ግን ምን ዋጋ አለው አቶ ታዲዮስ ታንቱ እንዳሉት አድርባይ እንዴት ሀገር ሊጠቅም ይችላል? ሲሉ የጠየቁት መጣልኝ እውነትዎን ነው አቶ ታድዮስ በምንም መንገድ አድርባይ አገር ሊጠቅም አይችልም ፡፡ ብሮድካስትም ሆነ አንባገነኑ መንግስት ለነሱ አዲስ የጋዜጣ ፍቃድ እንደማይሰጣቸው እርግጠኛ ስለሆኑ ወደህትመት ለመመለስ ሌላ አማራጭ መውሰድ ግድ ስለሆነባቸው ነው ከህትመት የወጡትን ጋዜጦችና መፅሔቶች እየገዙ ለመመለስ የተዘጋጁት ይህም እንደሚመስለለኝ በንግድ ህጉ መሰረት ባለቤትነትን ማዘዋወር በመሆኑ ለአፈና ብዙም ያልተመቸ በመሆኑ እንጂ ስርአቱ የነሱን መኖር ስለሚፈልግ አይደለም፡፡
ተመስገንን እና የልዕልና አዘጋጆችን እራሳቸውን እንደ እውነተኛ ሌላውን እንደሎሌ ያያሉ የሚል ነው፡፡ ይህ እኮ እሙን የሆነ ነገር ነው ለምሳሌ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች ከ 97 ሱናሚ አምልጠው አስራምናምን አመት መቆየታቸው በምን ምክንያት እደሆነ ሳያውቅ ነው እንግዲህ የፍትህ 4 አመት የአዲስ ታይምስ 6 ወር መቆት ያንገበገበው ይህ ደሞ ግልፅ ነው በ2004 መጨረሻ ፍትህ የጠቅላዩን ሞት ይዛ ስለወጣች ስትታገድ አዲስ አድማስ እና ሪፖርተር አንድ ግዜ ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ አንድ ግዜ ከህመማቸው አገግመው በቤተመንግስት አመራር እየሰጡ ነው እያሉ ውሸት ሲዘባርቁ ነበር ይሄ በራሱ ተመስገንም ሆነ የልዕልና አዘጋጆች ያሉት እውነት መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ሲባል ግን ከልእልና ውጪ ያሉ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን የስርዐቱ ሎሌዎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡
እንግዲህ ለዚህ ሎሌ አዲስ ነገር ፣ አውራምባ ታይምስ ፣ ፍትህ ፣ አዲስ ታይምስ አይነት የዕውነት ነፃ ፕሬሶች የህብረሰቡን ንቃተህሊና በማጎልበት ሰርተው ያለፉትን እንዲሁም ልዕልና አሁን እየሰራችው ያለቸውን ስራ ለሱ ምንም አለመሆኑ እሙን ነው ለኛ ግን ብዙ ነገሮቻችን ናቸው ወደፊት በሁሉም መንገድ አድጋ በልፅጋ ማየት ለምንፈልጋት ኢትዮጵያ የነዚህ አይነት ጋዜጦች መኖራቸው ግድ ነው!!
ከ97 ሱናሚ ቦኋላ ተከፍተው አሁን በህትመት የሌሉ ጋዤጦች አዲስ ነገር፣አውራምባ ታይምስ፣ጉግል፣ ፍትህ፣ፍኖተ ነፃነት፣ ነጋድራስ፣አዲስ ታይምስ ፣አዲስ ወሬ፣መሰናዘሪያ፣ኢትዮ ምሕዳር ወ.ዘ.ተ ይህም የሚያሳየው ስርዐቱ ፕሬሱን ምን ያህል እንደ ጦር እንሚፈራው ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሬሱ አሁን ሰለሚገኝበት ሁኔታ ለመገንዘብ በልዕልና ጋዜጣ ቁጥር 3 የ‹‹ፍትህ›› ወደ ‹‹አዲስ ታይምስ›› ከዚያም ወደ ‹‹ልዕልና ›› መቀየር ፤ የመንግስት ‹‹ትልቅነት›› ወይስ ‹‹ትንሽነት›› ማሳያ? በሚል ብርሀኑ ደቦጭ የፃፈውን ፅሁፍ ማንበብ በጣም ጠቃሚ ነው!!

በሳኡዲአረቢያ ሊያኖረው የሚችል ፈቃድ ስለሌለው ብቻ ረቡእ ማታ 1 ወጣት አውራሪስ ተሾመ ከለሊቱ አምስት ሰአት ገደማ በአረቦች ተገደለ :

በሳኡዲ አረቢያ በአቋራጭ ጎዳና በመሰደድ አስከፊ ህይወታቸውን ለመታደግ ብሎም ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ደፋ ቀና እያሉ ከአገራቸው ዳር ድንበር እየተሰደዱ የሚገኙት ወጣቶች ከፍተኛ ስቃይ እና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን የደረሰን ዜና ዘገባ
ያመለክታል ።
በዚህ ባሳለፍነው ረቡእ ማታ ከለሊቱ አምስት ሰአት ገደማ በአረቦች ተገደለ የተባለው ወጣት ።በሳኡዲአረቢያ ሊያኖረው የሚችል ፈቃድ ስለሌለው ብቻ እንዲገደል ማድረጋቸውን እና አስከሬኑ ወደ ሃገሩ ይላክ ሲባልም ህገወት የገባ ስደተና ስለሆነ ልንሰጣችሁ አንችልም በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ከስፍራው ያነጋገርናቸው ወገኖቻችን ገልጸዋል ። እንደ ህበረተሰቡ አገላለስ ከሆነ ልጁን እኛ አልገደልነውም እያሉ ይዋሹናል የገደለው መብረቅ ነው ብለው እያሉ እኛንም እያስፈራሩን ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል ።

የተገደለው ልጅ ስሙ ወጣት አውራሪስ ተሾመ የሚባል ሲሆን ትውልዱም በሰሜን ሸዋ ክፍለ ሃገር በኤፍራታና ጅሌ ወረዳ የካራቆሬ ከተማ ተወላጅ እንደሆነ ካገኙት የመታወቂያ መረጃ ለማወቅ ተችሎአል ።የማለዳ ታይምስ ዝግጅት ክፍል በአሁን ሰአት በጂዳ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለማነጋገር እና የዚህን ሟች አስከሬን ወደ ትውልድ አገሩ የሚላክበት ዘዴ ይፈጥር ዘንድ ትረት በማድረግ ላይ እንገኛለን ።
እንዲህ አይነቱ ችግር ሲፈጠር ማናቸውም ግለሰቦችም ቢሆኑ በግላቸው ጥረት በማድረግ አስፈላጊውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳይታቀቡ የማለዳ ታይምስ ዝግጅት ክፍል ያሳስባል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በአረብ አገር ላይ እየተሰደዱ በሚገኙት ወጣቶች ላይ የድብደባ እና ግድያ ወንጀል መበራከቱን ባሳለፍነው ሳምንታት ያቀረብናቸው የምስል ቅንብሮች ማስታወስ የሚቻል ነው ። ማለዳ ታይምስ ዝግጅት ክፍል ለወላጅ ቤተሰቦቹ መጥናናትን እየተመኘ ለእልፈተ ህይወቱም የሰላም እረፍት ነፍስን በገነት ያኑርልን ይላሉ ።source Minilik Salsawi

ወ/ሮ አዜብ ተጨንቀዋል


አቶ መለስ ከሞቱ ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ንግግርና መዕልክት የሚያስተላልፉት ወ/ሮ አዜብ መስፍን መረጋጋት እንደማይታይባቸው ተገለጠ። አሁንም በባለቤታቸው ስምና መንፈስ ሙግትና ማብራሪያ ከማቅረብ አልተላዘቡም። ይህን የሚያደርጉት ከጭንቀት የተነሳ እንደሆነ ተመልክቷል።

ሰሞኑንን በተጠናቀቀው የኢህአዴግ ጉባኤ አቶ መለስን አስመልክቶ ወ/ሮዋ የተናገሩት ንግግር በጭንቀት ውስጥ ስለመሆናቸው ማሳያ እንደሆነ የተናገሩት አብረዋቸው ባህር ዳር ስብሰባ የተቀመጡ የድርጅታቸው ኢህአዴግ “ባልደረቦቻቸው” ናቸው።

በጉባኤው ወቅት አቶ መለስ ዜናዊን በማወደስ የተዘጋጀው “ዝክረ – መውደስ” ታሪካዊ ሰነድ እንዲሆን ከመጽደቁ በፊት ወ/ሮ አዜብ በሰጡት አስተያየት “በፔሮል የሚከፈለው ብቸኛ መሪ መለስ ብቻ ነው” በማለት ራሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በፔሮል በሚከፈላቸው ገንዘብ ብቻ እንደማይኖሩ የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።

መለስ ደመወዛቸው ስድስት ሺህ ብር እንደሆነ፣ ሁለት ሺህ ብር ሲቆረጥ አራት ሺህ እንደሚቀርና “ይህችኑ ገንዘብ” እየተቀበሉ ላገር ሲሰሩ ያለፉ መሪ መሆናቸውን ያወሱት ባለቤታቸው፣ ለመለስ ዝክረ-መወደስ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ይህ መካተት ይገባዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

“መለስ ጭንቅላቱን ይዞ ወደዚህች ዓለም መጣ፣ ለዚህች ዓለም፣ አገር፣ ምድር፣ የምታገለግል ሃሳብ አመነጨ” ያሉት ወ/ሮ አዜብ፣ ባለቤታቸው ግለኝነት ሳይፈታተናቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን በመርሳት፣ ላገራቸው የለፉና ድህነትን ሲዋጉ ኖረው ያለፉ መሪ መሆናቸው ሊረሳ እንደማይገባው አመልክተዋል። አያይዘውም ሊተኩ የሚችሉ መሪ እንዳልሆኑ በማሳሰብ ዝክረ-መወድሱ ከአቶ መለስ የሕይወት ጉዞ ብዙ ቁምነገሮችን የዘለለና ያልተሟላ ነው ብለውታል፡፡ እንዲሁም መለስ የኢትዮጵያ መሪም ብቻ ሳይሆኑ የአዲስ ራዕይ መጽሄት አዘጋጅ መሆናቸው አለመጠቆሙ አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙ የድርጅት አባላት እርስ በርሳቸው ሲለዋወጡ የነበረውን የተከታተሉና በግልጽ ከስርዓቱ ባህርይ በመነሳት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ እንዳሉት ወ/ሮ አዜብ የቀድሞው ስብዕናቸው አብሯቸው የለም። እንዲያውም በጭንቀት ውስጥ ያሉ ይመስላሉ ብለዋል።

በድርጅቱ አባላት ከላይ እስከታች የባለቤታቸውን ስልጣን ተገን በማድረግ በጣልቃ ገብነታቸውና ከፍተኛ የሚባል ንብረት በማካበት የሚታሙት ወ/ሮ አዜብ የባለቤታቸውን ስም በመደጋገም የሚያነሱት የሚታሙበትን ጉዳይ ለማስረሳት እንደሆነ እርስ በርስ በእረፍት ሰዓት ይወራ እንደነበር እነዚሁ ክፍሎች ተናግረዋል።

“ሴትየዋ በግልጽ ስለሚነሳባት ጉዳይ ለምን አትናገርም” በማለት የጠየቁ እንዳሉ፣ ከዚህም በላይ በድርጅቱ ውስጥ ነግሷል የሚባለው ሙስና በግልጽ ለምን አጀንዳ ሆኖ እንደማይቀርብ አባሉ ውስጥ ውስጡን ሲያወራ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። በትክክለኛው መንግድ ለመታደስና ለመጥራት የሙስና ጉዳይ የድርጅቱ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት አስተያየት የሰጡም አሉ።

ወ/ሮ አዜብ ይህ ገብቷቸው ይሁን አይሁን ስለ ባለቤታቸው ድህነት ሲናገሩ “እንደሚባለው ሳይሆን እኛ እንኮራበታለን” ማለታቸው ከሙስና ጋር በተያያዘ ስጋት ስለገባቸው የአባሉን ልብ ለማራራት እንደሆነ አድርገው የወሰዱትም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። በግልጽ ባያብራሩትም “እንደሚባለው” ብለው በመጥቀስ በይፋ እስከማስተባበል መድረሳቸው በባለቤታቸው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ራሳቸውም የተረዱት አይመስልም፡፡

አቶ መለስ ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ በሚያገኙት መድረክ ስለ ባለቤታቸው ድህነትና ያለ እረፍት ያለፉ መሪ በማድረግ በስፋት የሚናገሩት ወ/ሮ አዜብ፤ ባለቤታቸውን ዴሞክራት መሪ አድርገው ቢስሉም ሪፖርተር በፖለቲካ አምዱ ያስነበበው እውነተኛ ታሪክ የስጋታቸውና የፍርሃታቸው መነሻ እንደሚሆን ከግምት በላይ የሚናገሩ አሉ። ሪፖርተር ወ/ሮ አዜብን በስም ባይጠቅስም፣ “መሐንዲስ አልባው መተካካት” በሚል ርዕስ በጻፈው “(መለስ) በተለያዩ ጊዜያቶች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ከፖለቲካ ጨዋታ ውጪ ማድረግ ቢችሉም፣ እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ ሥልጣን የግላቸው አልነበረም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ላይ ሆነው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ሰውም አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የሕወሓት መሰንጠቅን ተከትሎ የድርጅቱ ርዕዮተ ዓለም ቁንጮ (አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም) የወታደራዊ ስትራቴጂ ባለቤት (የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ)፣ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊው (የቀድሞ የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት) እና ሌሎች የድርጅቱ ከ10 በላይ ከፍተኛ አመራሮች መወገድን አስከትሏል፡፡ የእነዚህ የድርጅቱ ወሳኝ ሰዎች መወገድን ተከትሎ በመንግሥትም ሆነ በፓርቲ ሥልጣናቸውን የተደላደለና ምንም የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሌላቸው ሰው መሆን የቻሉበት ጊዜ ነበር፡፡ የፈለጉትን ሕግ ማውጣት ያልፈለጉትን የመደቆስ ሥልጣኑም ጉልበቱም ነበራቸው” ሲል ሪፖርተር የጻፈላቸው አቶ መለስን ተገን በማድረግ ወ/ሮ አዜብ በሃብት፣ በጣልቃገብነት፣ በተለያዩ ውሳኔዎች፣ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው መቆየታቸው በርካታ ወዳጅ ያፈራላቸው ባለመሆኑ የስጋታቸው መጠን ሰፊና ጥልቅ እንደሆነ በስፋት አስተያየት እየተሰጠበት ነው። 
(http://www.goolgule.com/)