9ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በጅጅጋ ለማክበር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ከተማ ያቆሽሻሉ ተብለው
ተይዘው ከጅጅጋ 25 ኪሜ ገደማ ከምትገኘዋ ቀብሪበያህ እስር ቤት እንዲገቡ ከተደረጉት መካከል ከ40 በላይ ሰዎች
ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በመሞታቸው በታሰሩበት አካባቢ እንዲቀበሩ ተደርጓል። ሟቾቹ በደንብ ባለመቀበራቸውና
የአንዳንዶችን አስከሬን ጅብ አውጥቶ ስለበላው፣ ሌሎቹ ከእስር ቤቱ ራቅ ብለው በድጋሜ እንዲቀበሩ መደረጉን ኢሳት
ከክልሉ ባለስልጣናት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በህይወት የተረፉት ሰዎች ከትናንት ጀምሮ የተለቀቁ ሲሆን፣ የዘመዶቻቸውን መሞት የተረዱ አንዳንድ ቤተሰቦች ሀዘን ተቀምጠዋል።
“ከተማ ታቆሽሻላችሁ እና ለጸጥታ ስጋት ትሆናላችሁ” በሚል ምክንያት ታስረው ከነበሩት ሰዎች መካከል ፣ የጎዳና
ተዳዳሪዎች፣ በጋሪ መግፋት እና በጉልበት ስራ የሚተዳደሩ ነዋሪዎች፣ አይነ-ስውሮች፣ አካለ ስንኩላን፣ መታወቂያ
አሳዩ ሲባሉ የክልሉን መታወቂያ ማሳየት ያልቻሉ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣታቸው ጸጉረ ልውጥ ተብለው የተያዙ
የሌላ አካባቢ ነዋሪዎች ይገኙበታል።
በጅጅጋ መታወቂያ ለማውጣት 1 መቶ 15 ብር የሚጠይቅ ሲሆን፣ በችግር ምክንያት መታወቂያ ያላወጡና በድንገት
መታወቂያ በተጠየቁበት ጊዜ ማሳየት ያልቻሉ በርካታ ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ ተደርገዋል።
የክልሉን የጸጥታ ዘርፍ ሃለፊ የሆኑትን አቶ አብዱላሂ ኢትዮጵያን ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልላቸውም ልናገኛቸው አልቻልንም።
Source: esat
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ