ረቡዕ 18 ዲሴምበር 2013

በሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በተደረገው ውይይት ምሁራኖች ስለ አምዬ ምኒልክ የተናገሯቸውን አንኳር ጉዳዮች

"አጼ ምኒልክ ‹‹ታላቁ›› የሚለው ስያሜ ይገባቸዋል::" ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማሪያም 

አጼ ምኒልክ ‹‹ታላቁ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ›› ሊባሉ ይገባል፡፡ ለዚህ ምክንያት አለኝ፡፡ በተለያዩ አገራት ትልቅ ታሪክ የሰሩ መሪዎች ታላቅ ተብለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ቴተር ዘ ግሬት›› በሩሲያ በሰራው ታሪክ የተሰጠው ስም ነው፡፡ ‹‹ካትሪን ዘ ግሬት›› የተባለችው መሪም ሩሲያውያን ላበረከተችው ስራ የሰጧት ስም ነው፡፡ ‹‹አሌክሳንዴር ዘ ዘግሬት›› ለግሪክ ባበረከተው ታሪክ ይህን ስም ተሰጥቶታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስካሁን የምኒልክን ያህል ታሪክ የሰራ መሪ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ከአሁን በኋላ ምኒልክ ይህንን ስም እንዲሰጣቸው አሳስባለሁ፡፡ 

"ተቃዋሚዎች ከአጼ ምኒልክ ሊማሩ ይገባል::" ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ 

የአጼ ምኒልክ ታሪክ ክርክር የሚያስነሳው ከእሳቸው ትልቅነት የነተሳ ነው፡፡ ትልቅ ስራ ያልሰራ መሪ ሊያከራክር አይችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን የተለያየ አመለካከት እንዳለን ሁሉ በምኒልክ ታሪክም አለመስማማትና የየራሳችን አመለካከት መያዝ እንችላለን፡፡ እርሳቸው አዋጅ ሲያስነግሩ እንኳ ‹‹አመልህን በሆድህ ሰንቅህን በአህያህ›› ጭነህ ተከተለኝ ነው ያሉት፡፡ የተለያየ አመልና አመለካከት እንዳለን ምኒልክም አልዘነጉትም፡፡ ግን በዋና ዋና ጉዳዮች መስማማት አለብን፡፡ በብዙዎቹ ባንግባባ በአድዋ ልንስማማ ይገባናል፡፡ ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከአጼ ምኒልክ ሊማሩ ይገባል፡፡ አጼ ምኒልክ ዓለምን ያስደመሙት ድል በማድረጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ የጦር አበጋዞች በእሳቸው ላይ ሳይከዱ ተባብረው ለአገራቸው እንዲሰለፉ በማድረጋቸው፣በወቅቱ መቻቻል በመፍጠራቸው ነው፡፡ ጣሊያን የጦር አለቆቹ ከምኒልክና እርስ በእርሳቸው ለማጣላት ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም አጼ ምኒልክ ግን በሰከነ መልኩ በተቀናቃኞች መካከልም ጭምር አንድነት በመፍጠር ታሪክ ሰርተዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ስሜታዊ አልነበሩም፡፡ እርሳቸው ያራምዱ የነበሩት መሬት የያዘ ፖለቲካን ነው፡፡ ከአጼ ዮሀንስ ጋር አለመግባባት በተፈጠረበት ወቅት አጼ ዮሃንስ ወደ ሸዋ ይዘው የዘመቱት ልምድ ያለው ሰራዊት ነው፡፡ በወቅቱ ምኒልክ በስሜት ለመግጠም አልሞከሩም፡፡ ለሶስት ቀን ያህል ተወያዩበት፣ እኔ ምን አለኝ፣ እነሱስ? የሚለውን መሬት የነካ ፖለቲካ አጤኑት፡፡ የሀይል አሰላለፉን ተገንዝበውም አስር አመት ጠበቁ፡፡ ፖለቲካ ትግስት ይጠይቃል፡፡ ቅንጅቶች ፓርላማ የመግባት አለመግባት ክርክር ሲነሳ አምስት አመት ጠብቁ ሲባሉ አልጠበቁም፡፡ እንግሊዝና ሱዳን በተጣሉበት ወቅት ሁለቱም ምኒልክ ጦር እንዲልክላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አጤ ምኒልክ ሁለቱንም እምብይ አላሉም፡፡ ለሁለቱ ቀና ምላሽ አሳይተው (ለይምሰል ነው) በርካታ ሺህ ወታደሮችን ወደ ሱዳን ልከዋል፡፡ ሆኖም ሰራዊቱ ቶሎ እንዳይደርስ ቀስ ብሎ እንዲሄድ አድርገዋል፡፡ ሰራዊቱ ሱዳን ድንበር የደረሰው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ነው፡፡ ከሁለቱም ጋር አለመግባባት ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ ሁለት አይነት ፖለቲካ አለ፡፡ አንዱ የሀላፊነት ፖለቲካ ነው፡፡ ሌላኛው የእልከኝነት፣ የስሜታዊነት ፖለቲካ ነው፡፡ በሀላፊነት ፖለቲካ ፖለቲከኛው ቅስሚያ የሚሰጠው ድርድርን ነው፡፡ የአጼ ምኒልክ ፖለቲካ የድርድር ፖለቲካ ነበር፡፡ የምኒልክ ቤት የምክክር ቤት ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ምክክር የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ መጀመሪያ እንደገባ በፈለጉት መልኩ ይደራደሩ ነበር፡፡ ከዛ ግን አንድ ሰው የሚወስነው ሆነ፡፡ የመንግስቱና የመለስ ቤት የምክክር ቤት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢህአፓም የሀላፊነት ፖለቲካ አልተወጣም፡፡ በዓለም ከፍተኛ ወታደራዊና ሌሎች ድጋፎችን የሚያገኘውን ደርግን ፊት ለፊት ነው የገጠመው፡፡ እንደ ምኒልክ ምን አለው፣ እኔስ ምን አለኝ የሚል የሀላፊነት ፖለቲካ አልተከተለም፡፡ ትልቅ ሀይል ካለው ደርግ ጋር የእልህ ፖለቲካ ነው የገባው፡፡ ለዛ ነው የእሳት እራት የሆነው፡፡ የዛሬዎቹ የሀላፊነት፣ የምክክር፣ የድርድር ፖለቲካንና ሌሎች አሳምኖ አንድነት የመፍጠር ፖለቲካን ከምኒልክ ሊማሩ ይገባል፡፡

"ታሪክ እንዳይሰረቅ መጠበቅ ያስፈልጋል::" አቶ ታዲዮስ ታንቱ

ምኒልክ ድሮ በህይወት እያሉ ከነበራቸው ታሪክ በላይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ጠላች አሏቸው፡፡ አክሱም ሆቴል ውስጥ ለመቁጠር የሚታክቱ በርካታ ምኒልክን የሚሰድቡ መጽሃፍቶች ተመርቀዋል፡፡ የምኒልክን ታሪክ ለማንቋሸሽ ብዙ እየተሰራ ነው፡፡ ይህን ለመከላከልም ታሪካችን ማወቅ አለብን፡፡ ታሪካችን ሰው እንዳይሰርቀን መጠበቅ አለብን፡፡ ታሪካችን ለልጆቻችን ካላስተማርን ከ80ና 90 አመት በኋላ አድዋን ያሸነፈው መለስ ነው ይሉናል፡፡ የአባይን የጀመረው መለስ ዜናዊ እንደሆነ እየነገሩን ነው፡፡ የድሮዎቹ መሪዎች አባይን ማንም ሳያግደን እንገድባለን ብለው ጊዜ ሲጠብቁ ቆይተዋል፡፡ መንግስቱ ሀይለማሪያም ሳይቀር አባይን ለመገሰደብ ትልቅ ጥረት አድርጓል፡፡ እንዲያውም የድሮዎቹ መሪዎች ገና ከራባት እንዳሰሩ የሙባረክን እግር ስመው ‹‹እባክህን አባይን ልገድብ›› ብለው አልጠየቁም፡፡

"ለነገስታቶቻችን ክብር መስጠት አለብን::" አስራት አብርሃም

ሰማያዊ ፓርቲ የታላቁን ዳግማዊ አጼ ምኒልክ 100ኛ ሙት አመት በማስታወሱ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ለነገስታቶቻችን ክብር መስጠት አለብን፡፡ እኔ ለአጼ ምኒልክ ከፍተኛ ክብር አለኝ፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የአድዋን ድል እንዳሸነፈው ምኒልክ ያህል ሊቀርበኝ የሚችል የለም፡፡ ሆኖም የነገስታቶቻችን ታሪክ ሁሉም መልካም አሊያም መጥፎ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያውያን ችግራችን ይህ ነው፡፡ የእኛ ዋናው ችግር ታሪክና ፖለቲካን መቀላቀል ነው፡፡ ምኒልክን አንዱ ሰይጣን ሲያደርገው ሌላኛው ጻድቅ ያደርገዋል፡፡ ለእኔ ሁለቱም አይደለም፡፡ እውነታው መሃል ላይ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ነው ብሄራዊ መግባባት መፍጠር የምንችለው፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ