“ኢትዮጵያን ለመታደግ በንቃት እንደራጅ!!
ዛሬ በረገፈ ዘውዱና በረገበ ዙፋኑ ላይ ያለ አቅሙና ያለ ህዝባዊ ይሁንታ የቆጥ ላይ እንቅልፍ የሆነበትን “ሥልጣን” የሙጥኝ ብሎ ያለው መካሪና ዘካሪ አልባው የህወሓት /ኢህአዴግ “መንግሥት” የሚንሊክ ቤተ-መንግሥትን ከተቆጣጠረ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የራሱን ስውር ደባ ለማስፈፀም በሚያመቸው መንገድ ጥንተ ገናናዋን፣ የዓለም የነፃነት ተምሳሌቷን፣ የጥበብና የሥልጣኔ ጮራዋን፣ የይሁዲ የክርስትና የእስልምና ማደሪያ የሆነች ምድረ ገነት የብዙሺህ ዓመት እመቤት ውዲት ሀገራችን ኢትዮጵያን ከፋሺስት ጣሊያን ተውሶ ባመጣው ሽንሸና በዘርና በቋንቋ አቧድኖ ላለፉት 22 ዓመታት በአሰቃቂ ጭቆና በግፍ ረግጦ ሲገዛህ ቆይቷል፤ ይህንን ህዝብን በሙልጭልጭ ሰንካላ ምክንያቶች በመከፋፈል /በመለያየት፣ በማባላት /በማናከስ፣ በመናቅ/ በማዋረድ፣ በማሸማቀቅ /አንገት በማስደፋት ለመዋሸት /በመቅጠፍ ላይ የተመሰረተ የእውር ድንብር አስተዳደሩን የሚቃወሙ ዜጎችን በማሳደድ፣ በመደብደብ፣ በመግደል፣ ከሥራና ከመኖሪያ በማፈናቀል፣ ያፈሩትን ሃብት በመዝረፍ፣ ከቤተሰብና ከትዳር በመለያየት፣ ዘብጥያ በማውረድ፣ በኃይማኖት ጣልቃ በመግባት ከፈጣሪያቸው በመለየት፣ ራሳቸውን እንዲያጠፉ በማድረግ፣ የገዛ ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከፈተኛ ጫና በማድረግ “የነፍስ ውጪ የነፍስ ግቢ” የጣር እስትንፍሱን ለማራዘም ሲፍጨረጨር ቆይቷል እየተፍጨረጨረም ይገኛል፡፡
ህወሓት /ኢህአዴግ የአንባገነንነቱን በትር ከጨበጠበት እለት ጀምሮ ከራሱ መሰል ግለሰቦችና ተላላኪዎች በስተቀር ሌሎች ዜጐች በሀገራችን ባይተዋርና የበይ ተመልካች ሆነን ለአንዲት ቀን እንኳ ከኑሮ ግብግብ አፎይ ሳንል በምንጓዛት አንዲት እርምጃ ሁሉ እንቅፋት የተሞላው ድቅድቅ ጨለማ ሆኖብናል፡፡ በዚህም ምክንያት ቀደም የነበረን የውስጥ ደስታና የርስ በርስ ፍቅር አጥተን በአስከፊ ስቃይ ላይ እንገኛለን፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማህበራዋ እንቅስቃሴ ፈፅሞ ፍትህ የጐደለው ከመሆኑ የተነሳ ጥቂት አፍቃሬ ህውሓት /ኢህአዴግ የሆኑ ግለሰቦች በአንድ ጀንበር ሚሊየኒየር ሲያደርግ አጠቃላይ ዜጐችን ደግሞ እያንደረደረ ወደ ድህነትና ድንቁርና የሲኦል አዘቅት ያለርህራሄ ይወረውራቸዋል፣ ከዚህም የተነሳ የመላ ሃገሪቱ አዛዥና ናዛዥ እነርሱ አንተ ደግሞ ሁሉ ነገርህን ተነጥቀህ ጭሰኛ ከሆንክ ሰነባብቷል፡፡
ይህንንም አገዛዝ ለማሰንበት ይቻለው ዘንድ የህወሓት /ኢህአዴግ አምባገነን “መንግሥት” በየጊዜው የሚያወጣቸውና የሚያፀድቃቸው ፌደራላዊም ሆነ ክልላዊ ፖሊሲዎች በሙሉ ለሀገርም ሆነ ለህዝብ ጥቅም ታስቦ ሳይሆን ለህወሓት /ኢህአዴግ የፖለቲካ ትርፍ እንዴት እንደሚያስገኙለት ታሳቢ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሀገርንም ሆነ ህዝብን አጥፊ የሆነ ሒደት ተገቶ በአገራችን ኢትዮጵያ ለህዝብ ተጠያቂና ተገዢ፣ የሆነ መንግሥት ተቋቁሞ ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕ፣ ሰላምና ብልፅግና ማስፈን እንዲቻል መኢአድ “የስልጣን ምንጭ ሕዝብ ነውና!” ኑ! አብረን በሰላማዊ ትግል ህወሓት /ኢህአዴግን እናበርክከው እያለ ህዝባዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ