ረቡዕ 22 ኤፕሪል 2015

A young Ethiopian girl beaten unconscionable by the federal police is being taken to hospital. ራስዋን እስክትስት ድረስ በፌዴራል ፖሊስ የተቀጠቀጠችው አንዲት ወጣት ኢትዮጵያዊት ወደሆስፒታል ተወስዳለች። በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድባ ራስዋን የሳተችው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ደግሞ 14 ዓመት የማይሞላት ልጅ ነች። እነዚህ ለጋ ወጣቶች ከቤታቸው በጥዋት የወጡት በሊቢያ ለታረዱት ወገኖቻቸው ሀዘናቸውን በሰላም ለመግለጽ ነበር። የ"ኢትዮጵያ መንግስት" ነኝ የሚል አካል በዚህ ሁኔታ ይጨፈጭፈናል ብለው አላሰቡም ነበር።



ማክሰኞ 21 ኤፕሪል 2015

በአዲስ አበባ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው፣ ሰልፈኛው በሊቢያ የኢትዮጵያውያንን መገደልና መንግስት ያሳየውን ቸልተኛነት በመቃወም ላይ ነው

ሰበር ዜና፣ ሰልፈኛው የኢቲቪ/ ኢብኮ ጋዜጠኞችን ደበደበ ****

(ነገረ-ኢትዮጵያ) ከደቂቃዎች በፊት የኢቲቪ/ ኢብኮ ጋዜጠኞች በለቀስተኞች መደብደባቸው ተሰምቷል፡፡ የኢትቪ /ኢብኮ ጋዜጠኞች ለቅሶ ቤት ውስጥ ቀረጻ አድርገው ሲመለሱ ‹‹ሌቦች እናንተ ልታስተላልፉት አይደለም፡፡ ስለ እኛ ምን አገባችሁ?›› ተብለው እንደተደበደቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
—————————
በሊብያ አሸባሪዎች በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝና መንግስት ነኝ ባዩ ወያኔ ያሳየውን ቸልተኛነት ለመቃወም በአዲስ አበባ ህዝቡ ነቅሎ አደባባይ ወጥቷል።
ይሁንና ፖሊስ እንደተለመደው ሰልፉን ለመበተን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፣ ነገረ-ኢትዮጵያ እንደዘገበው ከሆን ፖሊስ ሰልፈኛውን በዱላ መደብደብ ጀምሯል።
ሰልፉ ከፖሊሶቹ ቁጥጥር በላይ ሆኗል፣ በርካታ ህዝብ እየጮኸ እና እያለቀሰ ሰልፈኛውን መቀላቀሉን ቀጥሏል።
ሰልፈኞቹ ከሚያሰሙት መፈክሮች መካከል፣
‹ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት የለም!››
‹‹መንግስት የሌለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው!››
‹‹የወንድሞቻችን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም!››
‹‹የወንድሞቻችን ደም ውሃ አይደለም!››
ሰልፈኛው በተለይ ወጣቱ በቁጭት ለሟቾቹ ትኩረት ያልሰጠው መንግስት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰማ ነው!
‹‹ሌባ! ሌባ!ሌባ! ሌባ!ሌባ! ሌባ!››
ሰልፉ ቀጥሏል፣ ፖሊስ ሰዎች ሰልፈኛውን እንዳይቀላቀሉ ጥረት እያደረገ ነው።

ለቀጥታ ዘገባ የፌስቡክ ገጻችንን ይከታተሉ

Addis Ababa protest against Ethiopian government
Porotest in Addis Ababa, against ISIS and Ethiopian government
protest in Addis Ababa

ሰኞ 20 ኤፕሪል 2015

ኢትዮጵያውያን የሀገራችንና የራሳችን ክብር እና ደህንነት ማስጠበቅ ካለብን መጀመሪያ ሀገራችን ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፅኑ መታገል የግድ ይለናል”ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ገለጸ።

ሚያዝያ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው ፦«ከራሳችን ውጪ ለችግራችን ደራሽ መንግስት የለንም!»በሚል ርእስ በየመንና በደቡብ አፍሪካ በሚገኚ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ፣የኢትዮጵያውያን የውርደት ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሰሞኑን ከተከሰተው እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ አድርሶናል ብሏል።
“የመን ውስጥ በተከሰተው ጦርነት ተጎጂ የሆኑትን የውጭ ዜጎች መንግስታቶቻቸው ቀድመው ሲያስወጡ ለኢትዮጵያውያን ግን የሚደርስላቸው አልተገኘም”ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ይህንንውርደትም ወገኖቻችን «የመን ውስጥ የቀረነው እኛና ውሻ ብቻ ነን» ሲሉ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ እንደገለጹት አውስቷል። “ ኢትዮጵያውያን ላይ የመድፍ፣ የሞርታርና የአውሮፕላን ድብደባ ሲዘንብባቸው በመከራ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስልክ እንዲደውሉ በፌስቡክ ላይ በመለጠፍ ከማላገጥ ውጭ ምንም ያላደረገው የህዝብን ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው ገዥው ፓርቲ ፤ ይባስ ብሎ ለራሱ ስልጣን ይጠቅሙኛል ያላቸውን የጦርነቱን ተሳታፊዎች ደግፎ መግለጫ መስጠቱ- የኢትዮጵያውያንን ስቃይ እጥፍ ድርብ አድርጎታል”ብሏል። በአጭሩ ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲል ብቻ በማያገባውና በማይወጣው ዓለም አቀፍ ጦርነት ውስጥ ሀገራችንን ሲዘፍቅ ፤ ጦርነቱን ያወጀው፦ የሚደርስላቸው ባጡ ምስኪን ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ላይ ነው ብሏል-ሰማያዊ ፓርቲ።
በየመን የተከሰተውን መርዶ ሰምተን ሳንውል ሳናድር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አስደንጋጭ አደጋና እና ሰቆቃ ልንሰማ ተገደናል የሚለው የፓርቲው መግለጫ፤ኢትዮጵያውያንሀብትና ንብረታቸው መዘረፉ ሳያንስ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተከታትለናል ብሏል።
የዚህ አሰቃቂ አደጋ ሰለባ የሆኑ የሌሎች ሀገራት ዜጎች በቶሎ ከደቡብ አፍሪካ ሲወጡ፣ እንዲሁም ሀገራቱ ዜጎቻቸውን መታደግ ያስችላል ያሉትን መፍትሄዎች ሲያስቀምጡ እና ሲያስጠነቅቁ ቢደመጥም፤ ኢህአዴግ ግን እንደተለመደው የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃና ስቃይ ከምንም እንዳልቆጠረው በግልፅ እየታየ ነው ሲልም ሰማያዊ ፓርቲ ቁጣውን ገልጿል።
በእርግጥ ላለፉት 24 ዓመታት ኢህአዴግ ሀገር ውስጥ የሚኖሩትን ዜጎች ሲያሰቃይ፣ በውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንም የሆነ ያልሆነ ስም እየለጠፈ በጠላትነት ሲፈርጃቸው እንደቆየ አይተናል ያለው ፓርቲው፤ ኢህ አደግ  ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የራሱን የግል ጥቅም ሲያሳድድም መቆየቱን አውስቷል።
በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሱ ባሉት ተደጋጋሚ ግፎች ተሸፈነ እንጅ ሰሞኑን ሌላ ኢህአዴግ ለዜጎች እንደማይጨነቅ የታየበት ክስተት እየተፈፀመ ያወሳው ሰማያዊ ፓርቲ፤  ኢህአዴግ ለሱዳን መንግስት አሳልፎ በሰጠው ሰፊና ለም የሀገራችን ሉዓላዊ መሬት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አሳፋሪ እና አሰቃቂ ወንጀል እንደተፈፀመ ምመዘገቡን ጠቅሷል። “ኢትዮጵያውያን የሀገራችንና የራሳችን ክብር እና ደህንነት ማስጠበቅ ካለብን መጀመሪያ ሀገራችን ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፅኑ መታገል የግድ ይለናል።”ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ አስተዳደር፣ ዴሞክራሲያዊና ለዜጎች የሚያስብ ስርዓት ቢኖር መጀመሪያውኑም ወገኖቻችን በገፍ ለአደጋ ወደሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ባልተሰደዱ ነበር።”ብሏል።  በመሆኑም በቅድሚያ ክብራችንን ለማስመለስ የነፃነት ትግሉን አጠናክረን መቀጠል አልብን ብሏል-ፓርቲው። ሰማያዊ ፓርቲ አክሎም፦“ክብራችንን ልናስመልስ የምንችለው ሀገራችን ውስጥ እንዳንኖር ያደረገንን ስርዓት ቀይረን አንድም በገዛ አገራችን መኖር ስንችል፣ አንድም በአደጋ ወቅት ሊደርስልን የሚችል ተቆርቋሪና ለዜጎች የሚያስብ መንግስት መመስረት ስንችል ብቻ መሆኑን ልንገነዘበው ይገባል።”ብሏል።

ማክሰኞ 14 ኤፕሪል 2015

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የርሃብ አድማ ጀመሩ


ሚያዝያ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ከሚገኙት ፖለቲከኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መካከል ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድና ፍቅረማርያም አስማማው የረሃብ አድማ ጀምረዋል። የረሃብ አድማው መንስኤ ወጣት
እየሩሳሌም ተስፋው በቤተሰቦቿ የመጎብኘት ፈቃድ በመከልከሏ፣ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ለብቻዋ ታስራ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባት በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለመቃወም ነው።
ወጣት ብርሃኑና ፍቅረማርያም በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ምንጮች ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ ቃላቸውን ሰጥተው ድብደባው የቆመላቸው ቢሆንም፣ በእየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ስቃይ ግን እንደጨመረ ነው።
በእየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ስቃይ እስካላበቃና ቤተሰቦቿ እንዲያዩዋት እስካልተፈቀደ ድረስ በረሀብ አድማው እንደሚገፉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልጸዋል።
ብርሃኑ ተክለያሬድ ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና ፍቅረማርያም አስማማው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመሳተፋቸው ታስረው ተደብድበዋል።
ወጣቶቹ በምን ምክንያት እንደታሰሩ እስካሁን በይፋ መግለጫ የሰጠ አካል የለም። ይሁን እንጅ በቅርቡ ፍርድ ቤት በቀረበቡበት ወቅት፣ ሶስቱም ወጣቶች ከግንቦት7 ጋር በተያያዘ መከሰሳቸው ተገልጿል።

ቅዳሜ 4 ኤፕሪል 2015

የመኢአድ አመራሮች አዲስ አበባ ማዕከላዊ ይገኛሉ


ስለነ ዘመነ ምህረት አዲስ ነገር
ለገሰ ወ/ሃና
ዘመነ ምህረት ; መለሰ መንገሻ እና ሌሎች ጥር 10/2007 ዓም ከጎንደር ተይዘው አዲስ አበባ ማዕከላዊ ይገኛሉ ሰሞኑን በርካታ ወጣቶች ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተይዘው እየገቡ እንደሆነ መረጃ ደርሶኛል
ዘመነ ምህረት ከጥር 10/2007 ጀምሮ ላለፉት 75 ቀናት ማዕከላዊ ቁ 84/10 ጨለማ ቤት እንደሚገኝ ታውቋል ድሮ በዚህ ክፍል ውስጥ የመአሕድ መስራችና በኋላ የመኢአድ የአስተዳደርና ፋይናንስ ክፍል ሀላፊ የነበሩት አቶ ገብረፃዲቅ ሀይለማሪያም ታስረውበት የነበረ ነው ዛሬ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ም/ል ፕሬዝደንትና የሰሜን ቀጠና ሀላፊ ዘመነ ምህረት ታስሮበት ይገኛል 84/09 ኢንጂነር ሀይሉ ሻውል ታስረውበት የነበረ የዛሬውን ተራኛ አልታወቀም 84/08 ዛሬ ማን እንዳለበት አላውቅም በፊት ሻለቃ ጌታቸው መንግስቴ ታስረውበት የነበረ ነው ሌላው 84/07 አቶ ማሙሸት አማረ ታስረውበት የነበረ ነው የነዚህ ክፍሎች በር ሲዘጋና ሲከፈት የሚፈጠረው ድምጽ እኳን የተኛ የሞተም የሚቀሰቅስ ይመስለኛል ያሉኝ አሉ ሌላው በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኝ እስረኛ በካቴና ይታሰራል ቅዝቃዜው ውሃን ወደ በረዶነት የመቀየር አቅም ሳይኖረው አይቀርም ብለውኛል የቀመሱት በተመሳሳይ መንገድ መለሰ መንገሻም 84/06 ይገኛል ቀደም ሲል በዚሁ ክፍል ታስረውበት የነበሩ ሰዎች እንደነገሩኝ በነሱም (በአሳሪዎቹም) እንደሚታመነው አንድ ሰው በነዚህ ክፍልሎች ውስጥ ከ27 ቀን በላይ በዚህ ክፍል ውስጥ ከቆየ የአይን ብርሀኑ ሙሉ ጤናማ እንደማይሆን ይታመናል በነዚህ ክፍልሎች ምንም አይነት የተፈጥሮ ብርሃን አያገኙም እነዚህ ክፍልሎች ከ1984 ዓም ጀምሮ በርካታ የመአሕድና የመኢአድ አመራሮችና አባላት ታስረውበት የነበረ ነው እነዛ ክፍልሎች ታስረው የወጡ ታሳሪዎች እንዳጫወቱን ከክፍሉ ቅዝቃዜ የተነሳ ለከፋ የጤና ችግር ተዳርገው እንዳሉ በዚሁ ምክንያት ያጡትን ጤና ለመመለስ እውጭ ሀገር ድረስ ሄደው ቢታከሙም መዳን እንዳልቻሉ ገልፀውልኛል
እነ ዘመነ ምህረት ላለፉት 2 ወር ከ15 ቀን በነዚሁ ክፍሎች ውስጥ ሌሊትና ቀን እጅና እግራቸው በካቴና ታስሮ በመከራና በስቃይ እንዳሳለፉ ይገመታል ።
ሰው ሆኖ በሰው ልጅ ላይ ሊደርስ ይችላል ተብሎ የማይታመንና አለም በሙሉ በአስከፊነቱ ያስወገደውን ኢሰብአዊ ድርጊት በነዚህ ወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመባቸው ለመሆኑ የጉዳዩ ባለቤቶች ገልፀዋል ።
ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች
ማዕከላውይ በሚባለውና በሌሎች ማሰቃያ ቦታዎች እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው የመኢአድ አመራርና አባላት ያሉበት ሁኔታ በመኖርና ባለመኖር መካከል ያሉ ስለሆነ የነዚህን ወገኖቻችን ጉዳይ በመከታተል ባላችሁ ሀላፊነት መሠረት በናንተ ላይ ወድቋል የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ታደርጉ ዘንድ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችሁ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ሀላፊነታችሁን ትወጡ ዘንድ እናሳስባለን ።

ኢ/ር ይልቃል ከአገር አንዳይወጡ የተከለከሉበትን ምክንያት የሚነግራቸው ማጣታቸው ተዘገበ



መጋቢት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ወደ አሜሪካ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ በደህንነት ሰዎች እንዲሰረዝ ከተደረገ በሁዋላ፣ እስካሁን ድረስ ምክንያቱን የሚነግራቸው አካል መጥፋቱን ሊ/መንበሩ
ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መስሪያ ቤት ‹‹ፓስፖርቱ እኛ ጋር አልደረሰም፡፡ ቆይተው ደውለው ይጠይቁ››  ብለው ስልክ እንደሰጧቸው የገለጹት ኢ/ር ይልቃል፣ ይህም ሆን ተብሎ ጉዞውን ለማጓተት የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ የሚያደርጉት አገር የማስተዳደር
ብቃት ስለሌላቸው፣  የፖለቲከኛን እንቅስቃሴ በማጓተትና በማገድ የተፈጠረባቸውን ስጋት የሚቀርፉ ስለሚመስላቸው ነው፡፡  ከአቅመ ቢስነታቸው የመነጨ ነው›› ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያለው ተቀባይነት ገዢውን ፓርቲ እንዳስፈራውም አክለዋል።