ረቡዕ 21 ጃንዋሪ 2015

ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
በአንድነት ላይ የተቀነባበረው ዘመቻ በአስቸኳይ ይቁም!
ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/
የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ የ2007 አገር አቀፍ ምርጫን በአሸናፊነት ለመወጣት የተለየ ስትራቴጂ በመንደፍ በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ አንድነት የምርጫ ውድድር የይስሙላ ሳይሆን የምር መሬት ላይ በሚታይ ደረጃ መሆን እንዳለበት ወስኖ፤ የተንቀሳቀሰበት ሁኔታ በገዥው ፓርቲ የተወደደ ባለመሆኑ፤ በምርጫ ቦርድ፣ በሬዲዮ ፋና፣በቀድሞ ኢቲቪ በአሁኑ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን እና የአንድነት አባል ነን በሚሉ በተግባር ለአፍራሽ ተልዕኮ በተሰለፉ ወገኖች የተቀነባበረ ዘመቻ ከተጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ዓላማው ግልፅ ነው፤ ህዝቡ በተቃዋሚዎች በተለይም በአንድነት ላይ እምነት እንዳይኖረው እና ተስፋ እንዲቆርጥ በማድረግ አሉታዊ የምርጫ ቅስቀሳ በፓርቲያችን ላይ በማሳደር ለገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ መንገድ እየጠረጉ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ ባፈጠጠ እና ባገጠጠ መልኩ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ፈተና ላይ ወድቋል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ በሩ ሙሉ ለሙሉ እየተዘጋ መጥቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሌሎች ትልልቅ በሮችን ይከፍታል፡፡ በዚህ መንገድ አገሪቱን ለከፋ ችግር እየተጋለጠች መሆኑ ግልፅ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በፓርቲያችን በኩል ለሰላማዊ ትግል መጐልበት፤ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የቻልነውን ብናደርግም ህዝብ በሚከፍለው ታክስ የሚተዳደሩት የመገናኛ ብዙኃን እና የግል ተቋም ነኝ የሚለው፤ በተግባር ግን የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆነው ሬዲዮ ፋና በፓርቲያችን ላይ ከምን ጊዜውም በላይ አፍራሽ ዘመቻቸውን አጠናክረው ገፍተውበታል፡፡ የዚሁ ተልዕኮ አካል የሆነ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፓሬሽን ከ3 ወር በፊት ያስተላለፈውን ፕሮግራም አቧራውን አራግፎ እንደ አዲስ ሐሙስ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም ምሽት ፕሮግራም እንዳዘጋጀ ተከታትለናል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ በቀድሞ ኢቲቪ በአሁኑ ኢቢሲ የሚተላለፉ ዘገባዎች ላይ ያለውን ዕምነት ብናውቅም ስለዚህ ፕሮግራም በፓርተያችን በኩል ማለት የምንፈልገው፤ የተለያዩ አካላት የፓርቲው አባላት ነን ከሚሉት ጋር በመሆን የተቀነባበር ቀጣይ አፍራሽ ድራማ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው ነው፡፡
በመጨረሻም የመንግስት ኃላፊነት እና ልዩ ልዩ ስልጣኖች ያልፋሉ አገር እና ሕዝብ ግን ህያው ናቸው፡፡ ዛሬ በአንድት ፓርቲ ላይ የተቀነባበረው ዘመቻ ለአባላቱና ለደጋፊው ጥንካሬን ይሰጠዋል “ታጋይና ምስማር ሲመቱት ይጠብቃል” እንደሚባለው ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ በግልፅ እየታዘበ ነው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሬዲዮ ፋና የቀድሞ ኢቲቪ የአሁኑ ኢብኮን ተባባሪዎቻቸውን ታሪክ እና ጊዜ ይፈረዳቸዋል፡፡ ፓርቲያችን አይጠፋም፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም ሊያጠፉት የሚቅነዘነዙት ይጠፋሉ፡፡ የሕዝብ ፓርቲ ሁሌም ዘላለም ይኖራል፡፡
ድል የሕዝብ ነው!!
ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ