ረቡዕ 18 ዲሴምበር 2013

በሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በተደረገው ውይይት ምሁራኖች ስለ አምዬ ምኒልክ የተናገሯቸውን አንኳር ጉዳዮች

"አጼ ምኒልክ ‹‹ታላቁ›› የሚለው ስያሜ ይገባቸዋል::" ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማሪያም 

አጼ ምኒልክ ‹‹ታላቁ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ›› ሊባሉ ይገባል፡፡ ለዚህ ምክንያት አለኝ፡፡ በተለያዩ አገራት ትልቅ ታሪክ የሰሩ መሪዎች ታላቅ ተብለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ቴተር ዘ ግሬት›› በሩሲያ በሰራው ታሪክ የተሰጠው ስም ነው፡፡ ‹‹ካትሪን ዘ ግሬት›› የተባለችው መሪም ሩሲያውያን ላበረከተችው ስራ የሰጧት ስም ነው፡፡ ‹‹አሌክሳንዴር ዘ ዘግሬት›› ለግሪክ ባበረከተው ታሪክ ይህን ስም ተሰጥቶታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስካሁን የምኒልክን ያህል ታሪክ የሰራ መሪ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ከአሁን በኋላ ምኒልክ ይህንን ስም እንዲሰጣቸው አሳስባለሁ፡፡ 

"ተቃዋሚዎች ከአጼ ምኒልክ ሊማሩ ይገባል::" ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ 

የአጼ ምኒልክ ታሪክ ክርክር የሚያስነሳው ከእሳቸው ትልቅነት የነተሳ ነው፡፡ ትልቅ ስራ ያልሰራ መሪ ሊያከራክር አይችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን የተለያየ አመለካከት እንዳለን ሁሉ በምኒልክ ታሪክም አለመስማማትና የየራሳችን አመለካከት መያዝ እንችላለን፡፡ እርሳቸው አዋጅ ሲያስነግሩ እንኳ ‹‹አመልህን በሆድህ ሰንቅህን በአህያህ›› ጭነህ ተከተለኝ ነው ያሉት፡፡ የተለያየ አመልና አመለካከት እንዳለን ምኒልክም አልዘነጉትም፡፡ ግን በዋና ዋና ጉዳዮች መስማማት አለብን፡፡ በብዙዎቹ ባንግባባ በአድዋ ልንስማማ ይገባናል፡፡ ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከአጼ ምኒልክ ሊማሩ ይገባል፡፡ አጼ ምኒልክ ዓለምን ያስደመሙት ድል በማድረጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ የጦር አበጋዞች በእሳቸው ላይ ሳይከዱ ተባብረው ለአገራቸው እንዲሰለፉ በማድረጋቸው፣በወቅቱ መቻቻል በመፍጠራቸው ነው፡፡ ጣሊያን የጦር አለቆቹ ከምኒልክና እርስ በእርሳቸው ለማጣላት ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም አጼ ምኒልክ ግን በሰከነ መልኩ በተቀናቃኞች መካከልም ጭምር አንድነት በመፍጠር ታሪክ ሰርተዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ስሜታዊ አልነበሩም፡፡ እርሳቸው ያራምዱ የነበሩት መሬት የያዘ ፖለቲካን ነው፡፡ ከአጼ ዮሀንስ ጋር አለመግባባት በተፈጠረበት ወቅት አጼ ዮሃንስ ወደ ሸዋ ይዘው የዘመቱት ልምድ ያለው ሰራዊት ነው፡፡ በወቅቱ ምኒልክ በስሜት ለመግጠም አልሞከሩም፡፡ ለሶስት ቀን ያህል ተወያዩበት፣ እኔ ምን አለኝ፣ እነሱስ? የሚለውን መሬት የነካ ፖለቲካ አጤኑት፡፡ የሀይል አሰላለፉን ተገንዝበውም አስር አመት ጠበቁ፡፡ ፖለቲካ ትግስት ይጠይቃል፡፡ ቅንጅቶች ፓርላማ የመግባት አለመግባት ክርክር ሲነሳ አምስት አመት ጠብቁ ሲባሉ አልጠበቁም፡፡ እንግሊዝና ሱዳን በተጣሉበት ወቅት ሁለቱም ምኒልክ ጦር እንዲልክላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አጤ ምኒልክ ሁለቱንም እምብይ አላሉም፡፡ ለሁለቱ ቀና ምላሽ አሳይተው (ለይምሰል ነው) በርካታ ሺህ ወታደሮችን ወደ ሱዳን ልከዋል፡፡ ሆኖም ሰራዊቱ ቶሎ እንዳይደርስ ቀስ ብሎ እንዲሄድ አድርገዋል፡፡ ሰራዊቱ ሱዳን ድንበር የደረሰው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ነው፡፡ ከሁለቱም ጋር አለመግባባት ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ ሁለት አይነት ፖለቲካ አለ፡፡ አንዱ የሀላፊነት ፖለቲካ ነው፡፡ ሌላኛው የእልከኝነት፣ የስሜታዊነት ፖለቲካ ነው፡፡ በሀላፊነት ፖለቲካ ፖለቲከኛው ቅስሚያ የሚሰጠው ድርድርን ነው፡፡ የአጼ ምኒልክ ፖለቲካ የድርድር ፖለቲካ ነበር፡፡ የምኒልክ ቤት የምክክር ቤት ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ምክክር የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ መጀመሪያ እንደገባ በፈለጉት መልኩ ይደራደሩ ነበር፡፡ ከዛ ግን አንድ ሰው የሚወስነው ሆነ፡፡ የመንግስቱና የመለስ ቤት የምክክር ቤት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢህአፓም የሀላፊነት ፖለቲካ አልተወጣም፡፡ በዓለም ከፍተኛ ወታደራዊና ሌሎች ድጋፎችን የሚያገኘውን ደርግን ፊት ለፊት ነው የገጠመው፡፡ እንደ ምኒልክ ምን አለው፣ እኔስ ምን አለኝ የሚል የሀላፊነት ፖለቲካ አልተከተለም፡፡ ትልቅ ሀይል ካለው ደርግ ጋር የእልህ ፖለቲካ ነው የገባው፡፡ ለዛ ነው የእሳት እራት የሆነው፡፡ የዛሬዎቹ የሀላፊነት፣ የምክክር፣ የድርድር ፖለቲካንና ሌሎች አሳምኖ አንድነት የመፍጠር ፖለቲካን ከምኒልክ ሊማሩ ይገባል፡፡

"ታሪክ እንዳይሰረቅ መጠበቅ ያስፈልጋል::" አቶ ታዲዮስ ታንቱ

ምኒልክ ድሮ በህይወት እያሉ ከነበራቸው ታሪክ በላይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ጠላች አሏቸው፡፡ አክሱም ሆቴል ውስጥ ለመቁጠር የሚታክቱ በርካታ ምኒልክን የሚሰድቡ መጽሃፍቶች ተመርቀዋል፡፡ የምኒልክን ታሪክ ለማንቋሸሽ ብዙ እየተሰራ ነው፡፡ ይህን ለመከላከልም ታሪካችን ማወቅ አለብን፡፡ ታሪካችን ሰው እንዳይሰርቀን መጠበቅ አለብን፡፡ ታሪካችን ለልጆቻችን ካላስተማርን ከ80ና 90 አመት በኋላ አድዋን ያሸነፈው መለስ ነው ይሉናል፡፡ የአባይን የጀመረው መለስ ዜናዊ እንደሆነ እየነገሩን ነው፡፡ የድሮዎቹ መሪዎች አባይን ማንም ሳያግደን እንገድባለን ብለው ጊዜ ሲጠብቁ ቆይተዋል፡፡ መንግስቱ ሀይለማሪያም ሳይቀር አባይን ለመገሰደብ ትልቅ ጥረት አድርጓል፡፡ እንዲያውም የድሮዎቹ መሪዎች ገና ከራባት እንዳሰሩ የሙባረክን እግር ስመው ‹‹እባክህን አባይን ልገድብ›› ብለው አልጠየቁም፡፡

"ለነገስታቶቻችን ክብር መስጠት አለብን::" አስራት አብርሃም

ሰማያዊ ፓርቲ የታላቁን ዳግማዊ አጼ ምኒልክ 100ኛ ሙት አመት በማስታወሱ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ለነገስታቶቻችን ክብር መስጠት አለብን፡፡ እኔ ለአጼ ምኒልክ ከፍተኛ ክብር አለኝ፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የአድዋን ድል እንዳሸነፈው ምኒልክ ያህል ሊቀርበኝ የሚችል የለም፡፡ ሆኖም የነገስታቶቻችን ታሪክ ሁሉም መልካም አሊያም መጥፎ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያውያን ችግራችን ይህ ነው፡፡ የእኛ ዋናው ችግር ታሪክና ፖለቲካን መቀላቀል ነው፡፡ ምኒልክን አንዱ ሰይጣን ሲያደርገው ሌላኛው ጻድቅ ያደርገዋል፡፡ ለእኔ ሁለቱም አይደለም፡፡ እውነታው መሃል ላይ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ነው ብሄራዊ መግባባት መፍጠር የምንችለው፡፡

ማክሰኞ 17 ዲሴምበር 2013

አቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካ ተመለሱ

አቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካ ተመለሱ
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢሆንም ግን ፈተናውን ወድቋል የሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ የኢኮኖሚ እድገቱን መካድ ስህተት ነው፤ እድገቱ ዘላቂነት እንደሌለው አለመገንዘብም ስህተት ነው በማለት የኢዴፓ “ሦስተኛ አማራጭ” የተሰኘ የኢዴፓ አቋምን ይተነትናሉ፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም አንዱ ምክንያት የመንግስት ተጽእኖ እንደሆነ አቶ ልደቱ ገልፀው፤ ነገር ግን ህዝቡን አሰባስቦ በመታገል የመንግስትን ተጽእኖ ማስቆምና ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይልቅስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለመፈተሽና ስህተታቸውን ለማረም አለመዘጋጀታቸው ትልቅ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ ለሁለት ስሜታዊ ጽንፎች ፖለቲካ እንደሰፈነ ጠቅሰው፤ ስር የሰደደውን የተሳሳተ የጽንፍ አስተሳሰብ በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመተካት ሦስተኛ አማራጭ መያዙ ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ ከ1997 ወዲህ የአገሪቱ ፖለቲካ ቁልቁል እየተንሸራተተ በ15 አመት ወደኋላ መመለሱን ሲያስረዱ፤ አሁንም ከደጡ ወደ ማጡ እንዳይሰምጥ፣ ከዚያም ወደፊት እንዲራመድ ቁልፍ ያለው በገዢው ፓርቲ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በህዝቡ ዘንድ ነው ብለዋል አቶ ልደቱ፡፡ አቶ ልደቱ እነዚሁ 3 ቁልፍ አካላት ካሁን በፊት ምን ስህተት እንደሰሩና ወደፊት ምን እንደሚጠበቅባቸው ከመተንተን በተጨማሪ፤ ለበርካታ ጉዳዮች ላይ የሰነዘሩትን ሃሳብ በዚህ ቃለ ምልልስ እናቀርባለን፡፡
አቶ ልደቱ ለረጅም ጊዜ ጠፍተዋል..ከፓለቲካውም ከሃገሪቱም.. ከመገናኛ ብዙሃን ትንሽ ራቅ ስላልኩ የጠፋሁ ይመስላል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለትምህርት ከኢትዮጵያ ውጪ ነው የነበርኩት፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ከሃያ አምስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ብሆንም፣ በጠቅላላ ጉባኤ ከሊቀመንበርነት ስለወረድኩ የፓርቲው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አልመራም፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ከመገናኛ ብዙሃን ርቄያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ ፓለቲካ ግን አልራቅኩም፡፡ አሁን ትምህርቴን አጠናቅቄ እዚሁ አገሬ እየኖርኩ ነው፡፡ የነበሩበት ትምህርት ቤት ምንድን ነበር የሚባለው… ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ውስጥ፤ ስኩል ኦፍ ኦሬንታል ኤንድ አፍሪካን ስቴዲስ የሚባል አለ፡፡ እዚያ ነው ዲቨሎፕመንት ስተዲስ ያጠናሁት፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢዴፓ ‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የሚል ሃሳብ ይዟል፡፡ ይሄ ሃሳባችሁ ከምን አደረሳችሁ? ‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የምንለውን ነገር በአግባቡ ያለመረዳት ነገር አለ፡፡ እኛም በበቂ ሁኔታ አላስረዳን ሊሆን ይችላል፡፡
ሶስተኛ አማራጭ ሲባል፣ ልዩ የርዕዮተ አለም መስመርን ለመግለጽ ሳይሆን፣ የአቀራረብና የስልት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፓለቲካ፣ እስከ አሁን ድረስ ሁለት ፅንፍ የያዘ ነው። ሁለትም ነገር መደገፍ ወይም ሁሉንም ነገር መቃወም፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ከተሆነ፤ ተቃዋሚ የሚሰራውን ነገር ሙሉ በሙሉ ማጥላላት፤ የተቃዋሚ አባል ከተሆነ ደግሞ መንግስት የሚሠራውን ነገር ሁሉ መቃወም፡፡ እንዲህ ሁለት ጫፍ የያዘ አሰላለፍ፤ ለአገራችን ፖለቲካ አልጠቀመም፡፡ ከመቻቻል ከመደማመጥ አርቆናል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከሁለቱ ጽንፎች የተለየ አማራጭና የተለያየ አቀራረብ ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ይዘን የመጣነው፡፡ በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚ የተሠራ ነገር ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ከሆነ ልንደግፈው ይገባል፡፡ የማይጠቅምና የሚጐዳ ከሆነ ደግሞ በተጨባጭ መረጃ መቃወምና እንዲቀየር መታገል ያስፈልጋል፡፡ በስሜታዊ ጽንፍ ሳይሆን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው ፖለቲካው ሊመራ የሚገባው፡፡ አለበለዚያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ዲሞክራሲያዊ የመቻቻል ባህል ሊቀየር አይችልም። ሁለት ስሜታዊ ፅንፎችን ይዞ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው የሚያዋጣን ብለን ሶስተኛ አማራጭ ይዘናል፡፡ ይሄንን አቀራረብ ይዘን ስንመጣ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡
ሁለቱ ጽንፎች ለረዥም ጊዜ ስር የሰደዱና የከረሩ ስለነበሩ፣ ብዙ ሰዎች የእኛን አስተሳሰብ ለመቀበል በጣም አስቸግራቸዋል፡፡ ደግሞም አያስገርምም፡፡ ሰዎች በቀላሉ ይሄን አስተሳሰብ የሚቀበሉ ከሆነ፤ ከመነሻው የአገራችን ፖለቲካ ከባድ ችግር የለበትም ማለት ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ግን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ ስለሆነም፤ ሦስተኛ አማራጭ ብለን ያቀረብነው የምክንያታዊ አስተሳሰብ አቅጣጫችንን ብዙ ሰዎች በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም። “ተቃዋሚ ከሆንክ በቃ ማንኛውንም ነገር ትቃወማለህ፡፡ ኢህአዴግም ከሆንክ ማንኛውንም ነገር ትደግፋለህ፤ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የለም” የሚል የተዛባ አመለካከት ይሰነዘርብን ነበር፡፡ “እንዲያውም ሦስተኛው አማራጭ የምትሉት ነገር ወላዋይነት ነው” በማለት ውዥንብር የመፍጠር ነገርም ነበር። በሂደት ግን፣ ብዙ ሰው ጉዳዩን እያብላላው፣ እያጤነውና እየተገነዘበው እንደሆነ አይተናል፡፡ እኛ በምንፈልገው ፍጥነት ህብረተሰቡ ተረድቶታል የሚል እምነት የለንም፡፡ ገና ብዙ ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከአሁን በመጣበት የጽንፈኝነት መንገድ የትም ሊያደርሰን እንደማይችል ብዙዎች እየገባቸው ነው፡፡ ሁለቱ ጽንፎች የሚፈጥሩት ቅራኔና ውጥረት፣ ከዴሞክራሲ እያራቀን እንጂ ወደ መቻቻል እያመጣን እንዳልሆነ ሰው እየተገነዘበው ነው፡፡
“ሁለቱ የፅንፍ ሃይሎችና ጐራዎች አይጠቅሙም ትክክል አይደሉም” የሚለው አስተሳሰብ እየጐላ መጥቷል፡፡ “ሁለቱም ፅንፎች አይጠቅሙም፤ ችግር አለባቸው” ከተባለ ክፍተት መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ያንን ክፍተት የመሙላት ጉዳይ ነው የሶስተኛው አማራጭ ፋይዳ፡፡ ይሄንን አስተሳሰብ ይዘን እንደነበር በተለይ በፓርላማ በነበረን ተሳትፎ በደንብ ማሳየት ችለን ነበር፡፡ ፓርላማ ውስጥ ሌሎች ተቃዋሚዎች ከሚያራምዱት አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ፣ መንግስት ከሚሠራቸው ነገሮችና ከሚያራምዳቸው አቋሞች ውስጥ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅም ነገር ስናገኛቸው በድፍረት ስንደግፍ ታይቷል፡፡ ሰው ለዛ የሚሠጠው ትርጉም ምንም ይሁን እኛ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብለን እስካመንበት ድረስ በድፍረት ወጥተን፤ ይሄ አቋም ከገዢው ፓርቲም ይምጣ ከተቃዋሚ ፓርቲም ይምጣ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ እንደግፋለን ብለን ማሳየት ችለናል፡፡ ገዢው ፓርቲ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ሲሰራ ደግሞ ከሌሎች ተቃዋሚዎች በበለጠ በመረጃ በተደገፈ ከመተቸትና በጠነከረ መልኩ በመታገል ምክንያታዊነታችንን ማሳየት ችለናል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥም ጥፋት ወይም ድክመት ሲኖር፣ ተቃዋሚ ነውና እሱን አንነካውም አንልም፡፡ እንዲስተካከል እንተቻለን፡፡ ለሰላማዊ ትግልና ለአገር የማይበጅ፣ ለመቻቻል ፖለቲካ ማይጠቅም ሆኖ ካገኘነው፣ ተቃዋሚውንም ቢሆን በድፍረት የመተቸት አዲስ ባህል ይዘን መጥተን አሳይተናል፡፡ ያን የማይወዱ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡
በሂደት እየተረዱ ሲመጡ፣ ግን እኛ የያዝነው አቋም ትክክል እንደሆነ መገንዘብ የቻሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ አቋማችን በአገራችን ያልተለመደ አዲስ አቋምና አካሄድ ስለሆነ፤ አንዳንድ ሰዎች በእኛ ላይ የሚያወሩትን አሉባልታ ማራገብ ተጠቅመውበታል። በእኛ ላይ ከንቱ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲስፋፋ በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። በሌላ በኩል ግን ከነባሩ የጽንፈኝነት ፖለቲካ የተለየ ምክንያታዊ ፖለቲካ ማራመድ ለዚህ አገር እንደሚያስፈልግ በደንብ ለማሳየት ችለናል፡፡ ስለዚህ ሦስተኛ አማራጭ ይዘን መምጣታችን፣ ጥቅምም ጉዳትም ነበረው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንፃር፣ ሊያስወድድ የሚችል የፖለቲካ አቋም አልነበረም፡፡ ለአሉባልታ አጋልጦናል፡፡ ከረጅም ጊዜ አንፃር ግን ይሄ ምክንያታዊ የፖለቲካ መስመራችን እየሰፋና እያደገ፣ በተለይ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የሚመጣ አቋም ነው፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየተጠናከረ ነው፡፡ ግን ሂደቱን እኛ ስለተናገርነውና ስላራመድነው ብቻ ውጤት ያመጣል ማለት አይደል፡፡ ከአጠቃላይ ከአገራቱ ሶሽዬ ኢኮኖሚክ የእድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ ነው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወጥቶ ስለተናገረ ብቻ፣ የበቃ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ህብረተሰብ ይፈጠራል ማለት አይደለም፡፡ እንደዛ አይነት ህብረተሰብ የሚመጣው ኢኮኖሚያችን ሲያድግና ሲዳብር፤ ትምህርት ሲስፋፋና ከሌላው አለም ጋር መስተጋብራችን የበለጠ ሲጠናከር ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሚቀየር ነገር አይደለም፡፡
የአስተሳሰብ ለውጥ እውን የሚሆንበት ሂደት በጣም የተራዘመ እንዳይሆንና እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ግን የኢዴፓ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ እንግዲህ መንግስት ኢኮኖሚው በደብል ዲጂት እያደገ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡ ኑሮ ግን መንግስት ከሚገልፀው የተለየ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ? ኢኮኖሚውን በሚመለከት፣ የኛ አመለካከት ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይለያል፡፡ በመጀመሪያ እድገት አለ ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን መንግስት ሁሌም በሚናገረው መጠን ደብል ዲጂት እድገት አለ ብለን አናምንም፡፡ አንዳንድ አለማቀፍ ድርጅቶች እንደሚገልፁት እድገቱ ወደ ስምንት ሰባት ፐርሰንት አካባቢ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ አቅሙን ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ በእጃችን የለም፤ ሊኖረንም አይችልም፡፡ ነገር ግን ከአጠቃላይ ግንዛቤ ተነስተን ስናየው፤ መንግስት ከበታች አካላት እያገኘ ያለው መረጃ ትክክል ነው ብለን አናምንም፡፡ በብዙ ምክንያቶች የተዛባ መረጃ ነው ከታች ወደ ላይ የሚመጣው፡፡ የሚመጣውን ዳታ አምኖ መቀበል ያስቸግራል፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርላማ በነበርኩበት ጊዜ፣ የመረጃ ምርምራ ወይም ኦዲቲንግ ሲስተም ያስፈልገናል እል ነበር፡፡ የገንዘብ እና የአሠራር ኦዲቲንግ ብቻ ሳይሆን የመረጃዎች ትክክለኛነት ለመፈተሸ ኦዲት መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ስናነሳ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ይሄን ሃሳብ የሚቀበለን አልነበረም፡፡ አሁን ግን መረጃዎችን ኦዲት ማድረግ አለብን የሚል ሃሳብ በመንግስት እየተነሳ እያየን ነው፡፡ ይሄ የኢኮኖሚ እድገት አለ የሚባለው፡፡ መኖሩ ጥር ጥር የለውም፡፡ በምን ይገለፃል? ስለመኖሩ ህብረተሰቡ ውስጥ የምናያቸው እንቅስቃሴዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የልማቱን እንቅስቃሴ እንውሰድ፡፡ በመንግስት በኩል ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እየፈሰሰ መሠረተ ልማት እየተስፋፋ ነው፡፡ ይሄ በየትም አገር ቢሆን የኢኮኖሚ እድገትን ያመጣል፡፡ የግሉ ክፍሉ ኢኮኖሚ ከድሮ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍም በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የግንባታ እንቅሰቃሴ አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ እድገቱ ሙሉ በሙሉ ጤናማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ችግሮች የሉበትም ማለት አይደለም፡፡ ዕድገቱ መንግስት በሚለው መጠን ነው ማለት አይደለም፡፡
የእድገቱ መጠን መንግስት እንደሚለው ሳይሆን፣ ስምንትና ሰባት ፐርሰንት ይሆኖል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄም ቢሆን መጥፎ እድገት አይደለም፤ ጥሩ እድገት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ደረጃ ላለ ድሃ አገር ከስድስት ፐርሰንት በታች የወረደ እድገት፤ ኢኮኖሚው እንደተኛ (ሪሴሽን ውስጥ እንደገባ ነው የሚቆጠረው፡፡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ማደግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የሌሎችም አገራትም ታሪክ ያንን ነው የሚያሳየው፡፡ እንደ አሜሪካና እንደ እንግሊዝ አገር አይነት ትልቅ ኢኮኖሚ ውስጥ ሶስትም አራትም ፐርሰንት ማደግ ከባድ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ኢኮኖሚ ተይዞ ግን፤ ደብል ዲጂት ማደግ ይቻላል፡፡ መጣ የሚባለው እድገት በህብረተሰቡ ህይወት ውስጥ መታየት አልነበረበትም ወይ? ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡ አንድ ኢኮኖሚ ማደግ ሲጀምር ሁሉንም ህብረተሰብ ይጠቅማል ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ በየትም አገር ሆኖ አያውቅም፡፡ እንኳን ዘጠና ሚሊዬን ህዝብ ያለበት አገር ይቅርና፣ 3ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገርም ኢኮኖሚው ማደግ ሲጀምር ሁሉም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ነው ተጠቃሚው እየበረከተና እያደገ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነት ይታያል። ድህነት ብቻ አይደለም በርሃብም የሚሰቃዩ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መኖራቸው ግን እድገት የለም ወደሚለው ድምዳሜ አይወስደንም፡፡ እድገትም ባለበት አገር ሰው ይራባል፤ ሰው በድህነት ይማቅቃል፡፡ እንኳን በእኛ በጀማሪ አገር ቀርቶ፣ የዳበረ እድገት አላቸው የሚባሉ አገሮችም የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፡፡
እነዛ ሰዎች ስላሉ ግን ያ አገር አላደገም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የካፒታሊስት (የነፃ ገበያ) ስርዓት ውስጥና በአንድ ጊዜ ሃብት በእኩል መጠን ሊዳረስ አይችልም፡፡ በሂደት ነው፡፡ እንግዲህ የመንግስት ሚና እዚህ ላይ ነው የሚጠበቀው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እድገት መኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው ችግር ሌላ ነው። አሁን የምናየው እድገት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መሠረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ሚያመጣ ነው ብዬ አላምንም ዘላቂነት የለውም፡፡ አሁንም የዝናብ እርሻ ጥገኛ ነኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ኢኮኖሚ ዘላቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ ማኑፋክቸሪንግ ተረስቶ ነው የኖረው፡፡ እኛ ለኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ስንናገር አይቀበሉንም ነበር፡፡ በእርግጥ ለእርሻው ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የግድ ነው፡፡ ሰማንያ በመቶ ህዝብ በእርሻ ላይ ጥገኛ ሆኖ እርሻውን መዘንጋት አይቻልም፡፡ ግን በተመሳሳይ ሁኔታ ለኢንዱስትሪውም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ፤ ኢኮኖሚው በየዓመቱ ከእርሻ ጥገኝነትን ወደ ኢንዱስትሪው እስካልተሸጋገረ ድረስ፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ በዚህ ከተመዘነ የአገራችን ኢኮኖሚ ፈተናውን ወድቋል፡፡ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ወዲህ የገበሬ መጠን ምን ያህል ቀነሰ ብትይ፣ ከሶስት ፐርሰንት በላይ አልቀነሰም፡፡ አሁንም የእርሻ ጥገኛ ነን፡፡ አጭሩ መዋቅራዊ የሆነ ለውጥ አላመጣም፡፡ ግን እድለኞች ሆነን፣ በአለፉት ዘጠኝና አስር ዓመታት ጥሩ ዝናብ አለ፡፡ ይሄ ዝናብ ቢቋረጥ የምናወራለት የኢኮኖሚ እድገት እንክትክት ብሎ ነው የሚወድቀው፡፡ ለፓርቲው ስራ እና በትምህርት ወደ ውጭ አገራት ሲጓዙ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ስለአገሪቱ ፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳይ ይወያያሉ? በተለያየ አጋጣሚ ውጭ አገር ሄጄ የኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማየት ለማታዘብ እድል አግኝቻለሁ፡፡
በደፈናው ውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲህ ነው ብሎ ለመፈረጅ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ዝም ብሎ ስራውን የሚሠራ አለ፡፡ ገባ ወጣ የሚል አለ፡፡ አገር ቤት ገብቶ ብዙ ስራ የሚሠራ አለ፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣ የሰላሳና የአርባ ዓመት የቆየ አለ፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ሄጄ ተመልሻለሁ፡፡ ከፓለቲካው የራቀ አለ፡፡ አይነቱ ብዙ ነው፡፡ በውጭ አገር የለው ተቃዋሚ ሃይል እየሰራው ያለው ፖለቲካ ግን በአብዛኘው ለአገር የሚጠቅም አይደለም፡፡ የነሱ ተፅዕኖ ባይኖር፣ እዚህ አገር ያለው ፖለቲካ የተሻለ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ የዳያስፖራ ፓለቲካ፣ የአገሪቱን ፓለቲካ ወደ ጽንፈኝነት የሚገፉ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሆነ አገሪቱን እየጠቀማት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲበላሽ፣ ወደ ፅንፍ የከረረ አቅጣጫ እንዲሄድ የማድረግ አዝማሚያ ነው የማየው፡፡ ግን ኢዴፓን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአሜሪካ በአውሮፓ አላችሁ፡፡ አይደለም? አዎ ኢዴፓ በውጭ አገራት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አለን፡፡ ነገር ግን እዚያ ያለው መንፈስ እንከተላለን ማለት አይደለም፡፡ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታና በዳይስፖራ ተቃውሞ የሚያስተጋባው ነገር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ እነሱ የሚሉትን ከሰማሽ፤ እዚህ አገር አንድ ሰው በጠዋት ከቤቱ ወጥቶ ማታ በሰላም ይመለሳል ብለሽ አታስቢም፡፡ ሰው ስራ ሰርቶ እንጀራ በልቶ ይኖራል ብለሽ አታስቢም፡፡ ይሄ ሲባል ግን፣ ሁሉም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ እንዲያው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዳይስፖራ ከፖለቲካው ርቆ የሚኖር ነው፡፡ ‹‹ሳይለንት ማጆሪቲ›› እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡
በፖለቲካው በጣም ገንነው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ከአገር ከወጡ ብዙ ዓመት የሆናቸውና አንዳንዶቹ ሆን ብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ነገር አይፈጠርም ተብሎ ማውራት ተገቢ ይመስላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተተረማመሰች ብሎ መናገር ይጠቅመናል ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ፡፡ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልና የሚገባው የዳይስፖራው ማህበረሰብ አሁን እያደረገ ያለው ነገር በጣም ጐጂ መሆኑን ተገንዝቦ ይሄን ነገር መለወጥ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች በቀላሉ የሚለወጡ ናቸው ማለት ይከብዳል። ካልተለዋወጡ ግን ህዝቡ ስለነሱ ያለውን ግምት መለወጥ ይችላል፡፡ ‹‹ውጭ አገር ያለ ፖለቲከኞች የተማሩ፣ ገንዘብ ያላቸው፣ ዲሞክራሲ ባለበት አገር የሚኖሩ ናቸው ስለዚህ ከአገራችን ጥሩ ነው የሚያስቡት፤ እውቀት አላቸው›› ብሎ ማሰብ በራሱ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምን ያህል ፖለቲካችንን እየጐዳው እንዳለ እንቅስቃሴያቸውን መገንዘብ አለበት፡፡ ዛሬ ዛሬ የፓርላማ ስብሰባዎችን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? አንድ የተቃዎሚ ፓርቲ ተመራጪ ብቻ ናቸው፤ በፓርላማ ውስጥ የሚታዩት? እውነት ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በፊት አስራ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ፓርላማ ውስጥ ነበሩ፡፡ በ1997 ዓ.ም. የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ወደ ሰማኒያ ያህሉ ፓርላማ ገብተዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ሁላችንም ተጠራርገን ወጣን፤ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ይሄ የሚያሳየው የአገሪቱ የዲሞክራሲ ሂደት ከመሻሻል ይልቅ የኋሊት መመለሱን ነው ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የተቃዋሚው ጐራ በሂደት እየተጠናከረ ከመምጣት ይልቅ እየተዳከመ መምጣቱን ነው የሚያሳየው፡፡ በዋናነት በ1997 ምርጫ ከተሠራው አጠቃላይ ስህተት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ምህረት የለሽ ሆኖ በሃይል የማፈን ጥረት አደረገ፡፡
በሌላ በኩል አብዛኛው የተቃዋሚ ጐራ፣ ህዝብ የጠሰውንና እጁ ውስጥ የገባውን የምርጫ ውጤት ይዞ በአግባቡ እየተጠቀመ መቀጠል ሲገባው፣ ፓርላማ አልገባም ብሎ ህብረተሰቡን በምርጫ ሂደት ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎታል፡፡ ያኔ በቅንጅት ፓርቲዎች መካከል ቅራኔ ሲፈጠር፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርን እንረከብ፤ ‹‹ፓርላማ አንገባም›› በሚለው ውሳኔ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሂደት የኋሊት ለአስራ አምስት ዓመት የሚመልስ ስህተት መሆኑን ገልጸን ነበር፡፡ በዚያ ስህተት ሳቢያ ነው ዛሬ ዋጋ እየከፈልን ያለነው፡፡ ያኔ በአግባቡ ያገኘነውን የፓርላማ ወንበር ተረክበን፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርንም ተረክበን በመስራት ህዝቡን ከነስሜቱ ይዘን ብንቀጥል፤ ኖሮ እስከአሁን መንግስት የመሆን እድል ይኖረን ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ያኔ የኛን ሃሳብ መስማት ያልፈለጉ ጎራዎች፤‹‹ መንግስትን በሁለት እና በሶስት ወር እንጥለዋለን፤ ዕድሜ የለውም›› ብለው ነበር የሚናገሩት፡፡ ኢህአዴግ አልቆለታል፤ ነበር የሚሉት። ታሪካዊ ስህተት ነው የተፈፀመው፡፡ አሁንም ቢሆን፣ ተቃዋሚው ጎራ በነገሩ የፅንፍ ፓለቲካ የሚንዙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሌላ 15 ዓመት ወደኋላ ይሄዳል፡፡ ኢህአዴግ ወደፊት ለሃያና ለሰላሳ ዓመት በስልጣን ላይ የመቆየት እድል ያገኛል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ ይሄንን አለን፡፡ አሁን እየታየ ያለው አሳዛኝ የፓለቲካ ሁኔታ ለእኛ አዲስ አይደለም፤ ያኔ የተሠራው ስህተት ውጤት ነው፤ የዘራነውን እያጨድን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እያደገ መሄድ ሲገባው ወደኋላ እየሄደ ነው፡፡ ይሄ ለገዥው ፓርቲ ሆነ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅ ሽንፈት ነው፡፡ የአገር ሽንፈት ነው፡፡ በዚህ ማንም መደሰት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ተቃዋሚዎች በቀጣዩ ምርጫ ራሳቸውን አጠናክረው መምጣት ይችላሉ? ተቃዋሚው ጎራ ራሱን እንዲያሻሽልና እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚገባቸው ሶስት አካላት አሉ፡፡ መንግስት፣ የዲሞክራሲ ሂደቱ የበለጠ እንዲፋፋ አፋዊ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በአብዛኛው ስለ ዲሞክራሲያዊ ሂደት መንግስት እየተናገረ ያለው አፋዊ ነው በተግባር የሚገለፅ አይደለም፡፡ ወረቀት ላይ ይቀመጣል፡፡ በቲቪና በሬዲዮ ሲነገር እንሰማለን፡፡ በተግባር ግን የሚሠራው ከዛ የተለየ ነው፡፡
ሁለተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቆም ብለው ማሰብ አለብን፡፡ “የህዝብ ድጋፍ የለውም” የምንለውን ኢህአዴግን ለ22 ዓመታት ታግለን ለውጥ ያላመጣነው ለምን እንደሆነ ቆም ብለው በሃቅና በድፍረት ራሳችንን መመርመር ካልቻልነው፤ ከዛ ሂደት ተምረን መሠረታዊ የሆነ የአካሄድ ለውጥ እስካላደረግን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊቀየር አይችልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመጠናከር ይልቅ በተቃራኒው እንደውም በሂደት እየተዳከምን የመጣነው ለምንድን ነው? እውን ይሄ የሆነው በኢህአዴግ ተጽዕኖ ብቻ ነው ወይ? የራሳችን የውስጥ ችግር፤ ድክመት፣ ስህተት የለብንም ወይ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች እነዚህን ጥያቄዎች መርምረንና ራሳችንን ፈትሸን ራሱን ገምግሞ መሠረታዊ የመፍትሄ ሃሳብ ይዘን ካልመጣን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሻሻላል ብዬ አላምንም፡፡ ኢዴፓ ይንንን ሃላፊነት ለመወጣት የድርሻውን እየሰራ ነው፡፡ በርካታ ተቃዋሚ ወገኖች ግን ራሳቸውን ለመፈተሽ ዝግጁ አይመስለኝም፡፡ በድፍረት መናገር የምችለው፣ ከኢዴፓ በስተቀር ‹‹እኔ ስህተት አለብኝ፤ እስከአሁን የመጣንበት ጉዞ ስህተት ነበረበት፡፡ ያ ስህተት ነው ደካማ ያደረገን›› ብሎ የገመገመ ሌላ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም፡፡ አብዛኛው ተቃዋሚ ‹‹እኛ ስህተት የለብንም፤ ሁሌም ስህተት የሚፈጥረው ከገዢው ፓርቲና ከሌሎች ነው›› ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ራሱን ገምግሞ ተገቢ የመፍትሔ ሃሳብ የማያመነጭ ተቃዋሚ፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ለራሱም፣ ለሀገሩም አይሆንም፡፡ ሶስተኛው አስተዋፅዖ ከህዝብ ነው የሚጠበቀው። ምክንያቱም ህዝብ ነው የጉዳዩ ባለቤት፡፡ እኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊዎች ነን፡፡ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ግን ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ ለውጥ የሚመጣው ግን የዳር ተመልካች በመሆን አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲና፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡
ህብረተሰቡም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው እንዲወጡ የሚፈልግ የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ግን ፍላጎት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ስህተቶችን በአግባቡ ማወቅና እንዲታረሙ መታገል አለበት፡፡ ተቃዋሚ ስለሆኑ ብቻ በአዘኔታና በርህራሄ ‹‹ተቃዋሚዎች ናቸውና መተቸት የለባቸውም›› ማለት የለበትም፡፡ ፓርቲዎች ስህተት ሲሰሩ ካየ፣ ህብረተሰቡ መንግስትን ተቃዋሚዎችንም እየተቸ እንዲስተካከሉ ማገዝ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ የመነጨ ስለሆነ ህብረተሰቡ በገንዘብና በእውቀት ካልረዳቸው በስተቀር በሆነ ተአምር ተጠናክረው ሊወጡ አይችሉም፡፡ የህዝቡ መገለጫዎች ናቸው ስለዚህ ህብረተሰቡ ተቃዋሚዎች እንዲጠነክሩ የሚፈልግ ከሆነ፣ በተግባር አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው የአገራችንን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችለው፡፡ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ገዢው ፓርቲ ያወጣቸው አዳዲስ ህጐች አሉ፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የፕሬስ ህጉ፤ የፓርቲ ምስረታ አዋጅ፣ የኤንጂኦ ህግ ተቃዋሚዎችን ለማዳከም ገዢ ፓርቲ የፈጠረው ጫና ነው የሚል አስተያየት በስፋት ይደመጣል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? በአንድ በኩል፤ አዎ መንግስት እየፈፀመ ያለው ድርጊት፤ እያወጣቸው ያሉ ፖሊሲዎችና ህጎች፣ ለተቃዋሚ ጐራ መዳከም የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ብቸኛ ምክንያቶች ናቸው ማለት ግን አይደለም። ራሱ የተቃዋሚ ጐራ ችግሮችም ለሱ መዳከም ምክንያት መሆኑን ቀደም ብዬ ጠቅሼዋለሁ፡፡ ገዢው ፓርቲ ውስጥ የምናያቸው፣ የጭፍን ስሜታዊነት፣ የሙስና፣ የዘረኝነት፣ የአምባገነንነት፣ ችግሮች፤ ሳይቀነሱ ሳይደመሩ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም እናያቸዋለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚጎድለው ዲሞክራሲያዊ ባህሪ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጎድሎ ይታያል፡፡
ስለዚህ መንግስት የሚፈጥረው ጫና ለተቃዋሚዎች መዳከም አንድ ምክንያት ነው እንጂ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ እኮ ጠንካራ ነው የሚባለው፤ መንግስት የሚያደርግበትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ማሸነፍ ሲችል ነው፡፡ መንግስት ተጽእኖ የማያደርግ ከሆነማ ሁሉን ነገር የተመቻቸ ከሆነማ ትግልም አያስፈልግም። አገራችን እንደ አሜሪካ ሆናለች ማለት ነው። መንግስት ተፅዕኖ የማያደርግ ከሆነ፣ በጣም የምንመኘው ደረጃ ላይ በቀላሉ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ተዝናንተን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው በምርጫ እየተወዳደርን አሸናፊና ተሸናፊ ልንሆን እንችላለን ማለት ነው፡፡ ግን እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀርቶ ጨርሶ አልተጠጋንም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ጫና የሚያደርግ መንግስት ነው ያለን፡፡ ይህን ለመለወጥም ነው የፖለቲካ ትግል እያካሄድን ያለ፡፡ ህዝቡን አስተባብረንና አታግለን፤ የመንግስት ጫና እንዲቆምና ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይልቅስ ትልቅ እንቅፋት የሆነብን ውስጣዊ ችግር እንዳለብን መገንዘብ አለማቻላችን ነው፡፡ ውስጣዊ ድክመቶችን ለመፈተሸ አለማድረጋችን ነው ካንሠር ሆኖ የሚበላን፡፡ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚዎች ጥምረት እየፈጠሩ የህዝቡን ትኩረት በመሳብ በምርጫ ውጤት አምጥተዋል፡፡ የፓርቲዎችን ብርቱ ፉክክር የሚያካሂዱበት ነፃነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለ2007 ዓ.ም ምርጫ ግን ጥምረት የመፍጠር ህዝቡን የማንቀሳቀስና ብርቱ ፉክክር የማካሄድ ሁኔታ ጎልቶ አይታይም፡፡ ኢዴፓስ ለቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባል? በቀጣዩ ምርጫ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ አንደኛ ነገር ገዢው ፓርቲ ከስህተቱ እየተማረ አይደለም፡፡ አሁንም በየቀኑ የሚነግረን፤ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ሞልቶ እንደተትረፈረፈና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ ምንም ችግር እንደሌላቸው ነው፡፡ ይህቺ አገር በልማት ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲም እያደረገች እንደሆነ ነው ኢህአዴግ የሚነግረን። ይሄ ቀልድ ነው፡፡ በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ኢህአዴግ እንደሚለው አይደለም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት በአግባቡ በዚች አገር እንዲያብብ እያደረገ አይደለም።
ገዢው ፓርቲ ላይ ቁርጠኝነት እየታየ አይደለም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም አብዛኛው ውስጣዊ ድክመታቸውን ሳይፈትሹ ነባሩን አስተሳሰብና አቀራረብ እንደያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በ2007 ዓ.ም ምርጫ፣ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ቢመጣ የሚችለው እነዚህ ሁለት ጐራዎች ከስህተታቸውና ከችግራቸው ተምረው የተግባር ማሻሻያዎችን ሲያደርጉ ነው። ይሄን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ አሁን የቀረው አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ መንገዳቸውን ካላስተካከሉ፣ ምርጫው ከአለፉት ምርጫዎች የተሻለ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ በሌላ በኩል አብሮና ተቀናጀን የመስራት ፍላጎት ቢኖር ኖሮ ያለ ጥርጥር የተሻለ ነገር መስራት ይቻል ነበር፡፡ ተቃዋሚው ጎራ እርስ በርስ ተቻችሎ እንዲሰራ የሚያደርግ ሃይል ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ አቶ ልደቱ በሚቀጥለው ሳምንት፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ያለውን የኢህአዴግ፣ የመንግስትና የአገሪቱን ሁኔታ ይተነትናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሦስት ዋና ዋና ፈተናዎች ምን እንደሆኑ በመዘርዘር የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባሉ። የአረቡን አለም አዝማሚያዎችንና የግብጽና የአባይ ጉዳዮችን እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ስደትን በተለከተም አቶ ልደቱ ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡

የራስን እድል በራስ መወሰን፣ እርስ በርስ እስከማጣላት…

ሌላው ኢትዮጵያዊ የተዋረደበት፤ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን – በኦጋዴን!

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ተከበረ የተባለውን የብሄሮች ቀን ምን ያህሎቻችሁ እንደተከታተላቹህ አላቅም። ላላያችሁት ግንዛቤ ለመፍጠር ያህል… ዘንድሮ በአሉ የተከበረው ሱማሌ ክልል፣ በኦጋዴን ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን በመንገር ወጋችንን እንጀምራለን። ይህ ዝግጅት እስከዛሬ በትግራይም፣ በአማራውም ክልል ተደርጓል… ሆኖም በአሉ ላይ ሁሉም የየብሄሩን ባህል ለማሳየት ሲጥር እንጂ፤ አንደኛው ብሄር ሌላውን ሲሰድብ ያየንበት አጋጣሚ አልነበረም። የዚህ አመቱ የብሄር ብሄረሰቦች ወይም የብሄረተኞች ቀን ሌላውን ኢትዮጵያዊ በመውቀስ ላይ የተመሰረተ ነበር።
“አማራው፣ ደገኛው፣ የመሃል አገር ሰው…” እያሉ ቀጠሉ አስተያየት ሰጪዎቹ። በአሉን ምክንያት በማድረግ በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች ወቀሳቸውን ቀጠሉ፤ “የመሃል አገር ሰዎች ‘ሽርጣም ሱማሌ’ እያሉ ይጠሩን ነበር” አለ። እኛንም በሃሳብ ወደኋላ መለሰን። የመሃል አገር ሰው ይህንን ቃል አይጠቀምበትም ለማለት አይደለም። ነገር ግን “ሽርጣም ሱማሌ” የሚለውን ቃል መስማት የጀመርነው፤ በኢትዮጵያ እና ሱማሌ ጦርነት ወቅት ነው። “ሽርጣም ሱማሌ” የሚለውን አባባል ሁሉም የመሃል አገር ሰው እንደማይጠቀምበት ሁሉ፤ በቴሌቭዥን መስኮት ላይ ብቅ ብለው ሌላውን ኢትዮጵያ የሰደቡት እና ያሰደቡትም መላውን የኢትዮጵያ ሱማሌ እንደማይወክሉ እናውቃልን። በመሆኑም ይህ ጽሁፍ በሁሉም የኢትዮጵያ ሱማሌዎች ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ የማያውቁትን ታሪክ ለማሳወቅ ያህል የተዘጋጀ መሆኑን ልብ ይበሉ።

በዳዊት ከበደ ወየሳ
በ1969 ዓ.ም. ሱማሌ ኢትዮጵያን ስትወር፤ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አፈናቅለዋል፤ ገድለዋል፤ በሺህ የሚቆጠሩትን ማርከው ወስደው አገራቸው ውስጥ አስረዋል። ሱማሌዎች ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ታዲያ ሽርጥ እንጂ ሱሪ ታጥቀው አይደለም። በዚያን ወቅት ታዲያ የኢትዮጵያ ልጆች ዳር ከዳር “ሆ” ብለው ሲነሱ፤ በወገናቸው ላይ የደረሰው በደል ቢያንገበግባቸው፤ “ይሄ ሽርጣም ሱማሌ” ብለው ቢሳደቡ ሊገርመን አይገባም። ከዚያ በፊት በነበሩት ጦርነቶች ፈረንጆች ኢትዮጵያን ሲወሩ፤ “ይሄ ሶላቶ” ብለው እንደሚጠሯቸው ጠላት የነበረውን የሱማሌ ታጣቂ “ይሄ ሽርጣም” እያሉ በመፎከር፤ የገባበት ገብተው ደምሠውታል፤ ዳግመኛም የኢትዮጵያን ድንበር እንዳይሻገር አድርገውታል።Ethiopian flag, Green, yellow and red
በ1970 የሱማሌ ጦር ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ ተደመሰሰ። ከጅጅጋ እና አካባቢው ተፈናቅለው የነበሩት የኢትዮጵያ ሱማሌዎች ወደ ድሮ መንደራቸው ተመልሰው፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሰላማዊ ኑሯቸውን ቀጠሉ። “ሽርጣም ሱማሌ” የሚለውም አባባል እየቀረና እየተረሳ መጣ። ዘንድሮ በሱማሌ ክልል፣ በአሉ ሲከበር… ሌላው ኢትዮጵያዊ ለሱማሌ ኢትዮጵያ የሰራው ውለታ ተረስቶ፤ የመሃል አገር ሰዎች “ሽርጣም ሱማሌ እያሉ ይሰድቡን ነበር” የሚል የጥላቻ መልዕክት ሲተላለፍ ሰማን።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ቀጠለ። “ድሮ ያስተማሩኝ ሰዎች ስማቸው ‘በቀለ፣ መኮንን፣ በየነ’ ነበር። አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል። አስተማሪዎቻችን ስማቸው መሃመድ እና አብዱል ሆኗል።” በማለት ለኢህአዴግን መንግስት ምስጋና ሲያቀርብ ስንሰማ፤ ጆሯችንን ማመን አቅቶን ተገረምነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ሲጀመር፤ የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት የመጀመሪያ መምህራን የመጡት ከግብጽ አገር ነበር። በኋላም ላይ ከህንድ ድረስ መምህራን እየመጡ አስተምረዋል፤ ወይም አስተምረውናል። በውጭ ሰው ስለተማርን… “ለምን የውጭ ሰው አስተማረን?” ብለን አንቆጭም፤ ይልቁንም ለእነዚህ መምህራን አክብሮት እና ምስጋናችንን እናቀርባለን እንጂ። በሱማሌ የተመለከትነው ግን ከዚህ የተለየ ነበር… እቺም እድሜ ሆና… እነበቀለ፣ መኮንን እና በየነ የሚባል ስም የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ስላስተማሯቸው የሚናደዱ ሰዎችን ለማየት በቃን።
ደግሞም አንድ ሌላ እያሳቀ የሚያናድድ ነገር ሰማን። ሌላው አስተያየት ሰጪ እንዲህ አለ። “አካባቢያችን ልጅ ምግብ አልበላም ብሎ ሲያስቸግር፤ ‘አማራ መጥቶ እንዳይበላብህ’ በማለት ልጁ አማራ ሳይመጣበት ቶሎ እንዲበላ እናደርግ ነበር።” አለ።
“ጉድ እኮ ነው የሱማሌ ኢትዮጵያ ህዝብ አማራውን ይህን ያህል ይጠሉት ነበር? ማስፈራሪያስ አድርገውት ነበር?” እያልን ተገርመን ሳናበቃ ይኸው ሰውዬ ንግግሩን ቀጠለ።
“በሌላ በኩል ደግሞ የመሃል አገር ሰዎች (አዲሳባ ያለው ሌላው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው) ልጆቻቸው ምግብ አልበላም ብለው ሲያስቸግሯቸው፤ “ሱማሌ እንዳልጠራብህ!” ብለው ሲያስፈሯቸው፤ ምግቡን ጥርግ አርገው ይበሉ ነበር።” ሲል ሰማን። አብረውኝ ኢቲቪን ይመለከቱ የነበሩ “የመሃል አገር” ሰዎችን በጣም አሳቃቸው። እርስ በርስ ተያየንና “ሱማሌ እንዳይመጣብህ!” ተብሎ ምግብ ሲበላ የነበረ ከመሃላችን ነበር?” ብሎ ጠየቀ አንዱ…
ሌላኛው “እኛ አያጅቦን ነው የምናውቀው” ሲል ትንሽ አሳቀን።
“ሱማሌ ሳይመጣብህ!” ተብሎ እያስፈራሩ ምግብ ያስበሉት ይፍረደን” በማለት በጉዳዩ ላይ ስቀን ልናልፍ እንችል ይሆናል። ነገር ግን … ለአማራው ድርጅት ‘ቆሜያለሁ’ የሚለው ብአዴን/ኢህአዴግ ነገሩን እንዴት አይቶት ይሆን?
የብሄር በሄረሰቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ የሚተላለፈው የጥላቻ አስተያየት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ኢቲቪን ከመዝጋታችን በፊት ሌላ አስተያየትም አደመጥን። ሰውየው እንባ እየተናነቃቸው፤ “መናገሻ ከተማችንን አዲሳባን ለማየት እንኳን አይፈቀድልንም ነበር።” ብለው ሲሉ፤ በራስ ተፈሪ መኮንን ዘመን የነበሩ የሱማሌ ፖሊሶች ታወሱን። በወቅቱ በአዲስ አበባ፤ በፖሊስነት ተቀጥረው ሰአት እላፊ እና ጸጥታ የሚያስከብሩት የመጀመሪያ ባለደሞዝ የአዲስ አበባ ፖሊሶች የሱማሌ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። እናም “አዲስ አበባን ለማየት እንኳን አይፈቀድልንም ነበር” እያሉ የሚያለቅሱትን አዛውንት አይተን፤ “ወደ አዲስ አበባ መሳፈሪያ ካላጡ በቀር የባቡር መስመር ከተዘረጋ ራሱ፤ መቶ አመት አልፎታል”። በማለት ታዝበናቸው ዝም አልን።
ሌላዋ ሴት ደግሞ ቀጠለች። ሴትዮዋ መናገር ስላለባት ብቻ የምትናገር ነው የምትመስለው… “የድሮ እና የአሁኑን ሳስተያየው በጣም ብዙ ልዩነት አለው” ብላ ጀመረች። ልጅቷ እንኳንስ ስለቀዳማዊ ሃአይለስላሴ ዘመን ቀርቶ ስለደርግ ለማውራት እድሜዋ የሚፈቅድላት አይደለችም። ወሬዋን ግን በድፍረት ቀጠለች። “የድሮና የአሁኑ በጣም ልዩነት አለው… ዑውውውው።” በማለት የአሁኑን አዳነቀች። አድናቆቷን ሳታቋርጥ “የድሮ እና የአሁኑን ልዩነት ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል” ብላ በቃላት እጥረት ምክንያት ልዩነቱን ሳትነግረን ቀረች።
ሌላው ደግሞ እንዲህ አለ። “ይሄ አካባቢ ለወታደራዊ ጦር ካምፕ ይጠቀሙበት ነበር እንጂ፤ ለህዝቡ ግድ አልነበራቸውም።” አለን። እውነት ነው። ፈረንሳይ ከጅቡቲ አልፋ ወደ ኢትዮጵያ የመስፋፋት ብዙም ህልም አልነበራትም። እንግሊዝ እና ጣልያን ግን… ሁለቱም ከሱማልያ ግዛቶቻቸው ተነስተው፤ ኦጋዴን እና አካባቢውን ጨምረው እስከ ሃረር ድረስ ለመግዛት፤ ግልጽ የሆነ እቅድ እና ሙከራ አድርገው ነበር። ሱማሊያ ነጻ ከወጣች በኋላ ደግሞ ከራሽያ ባገኘችው የጦር መሳርያ በመታገዝ እጅግ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አድርጋለች። በዚህ ጊዜ ሁሉ ሰራዊቱ ከመሃል አገር እየተነሳ፤ ኦጋዴን እና አካባቢው በውጭ ሃይሎች ስር እንዳይወድቅ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ይህ ሌላውን አገር በወታደራዊ ኃይል የመከላከል ስራ… ዛሬ ስሙ እና ውለታው ተረስቶ “አካባቢውን የወታደር ካምፕ አደርገውብን ነበር” በሚል ወቀሳ መቀየሩ ይገርማል።
አብረውን የነበሩት ጓደኞቼ በኢቲቪ ተናደዋል። ቴሌቪዥኑን ከመስበራቸው በፊት በሰላም ዘጋነውና ሰላማዊ ጨዋታችንን ጀመርን። “ለመሆኑ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደገኛ፣ የመሃል አገር፣ ክርስቲያን፣ አማራ…” እየተባለ ቅጽል እየወጣለት መሰደብ አለበት ወይ? ይህ ደገኛም ሆነ ነፍጠኛ ያሉት ኢትዮጵያዊ ለዚያ ህዝብ ውለታ አላደረገምን? ዝርዝር ውስጥ አንገባም። ሆኖም በታሪክ ቅኝት ወደኋላ መለስ ብለን የእውነትን ማህደር በማገላበጥ ታሪክን እስኪ እንመርምር። እንዲህ ነው።
ወደ አጼ ምኒልክ ዘመን እንሂድ… በፊት በቱርኮች፤ በኋላ ደግሞ በግብጾች ሲተዳደር የነበረው ህዝብ የጠመንጃውን አፈሙዝ በኢትዮጵያውያን ላይ አነጣጥሮ እንደነበር ይታወቃል። በ1524 ዓ.ም. ግራኝ አህመድ እና አሊ ኑር እንደገነኑት ሁሉ፤ በ1876 ዓ.ም. ደግሞ አሚር አብዱላሂን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ገዢዎች ጉልበታቸው የደረጀበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ነዋሪውን በቁጥጥራቸው ስር አውለው፤ “በክርስቲያን መንግስት አንገዛም” ማለታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከዚያ እምነት ውጪ የነበሩትን የገደሉበትና ያጠፉበት ታሪክ ነው ያለን። (ይህም በአረብኛ ተጽፎ የሚገኝ ሰፊ ታሪክ ያለው ጉዳይ ነው) አሚር አብዱላሂም ቢሆን፤ ለአጼ ምኒልክ “አልገብርም” ማለት ብቻ ሳይሆን፤ “አንተም እንደኛ ካልሰለምክ በስተቀር፤ በክርስቲያን ንጉሥ አንገዛም” በማለት ለአጼ ምኒልክ፣ ሽርጥ፣ መቁጠርያ እና መስገጃ ምንጣፍ ነበር የላከላቸው።
አጼ ምኒልክ የተላከላቸውን ሽርጥ፣ መቁጠሪያ እና መስገጃ አብረዋቸው ለነበሩ ሙስሊሞች ሰጥተው፤ ፊታቸውን ወደምስራቅ ኢትዮጵያ አዙረው፤ በአሚር አብዱላሂ የሚመራውን ጦር፤ ጨለንቆ ላይ ገጠሙት። በዚያ የጨለንቆ ጦርነት በርካታ ኢትዮጵያውያን አለቁ። ከሚንልክ ጋር የነበሩ የአማራ ተኳሾች እና የኦሮሞ ፈረሰኞች፤ የአሚር አብዱላሂን ጦር አሸነፉት። ጥር 18 ቀን፣ 1879 አካባቢው በምኒልክ ጦር ነጻ ወጣ። አሚር አብዱላሂም በጅጅጋ አድርጎ አገር ጥሎ ጠፋ።
በኋላ ላይ የአሚር አብዱላሂ ዘመዶች ወደምኒልክ ዘንድ መጥተው፤ “እባክዎን አገሩን እንዳያጠፉት” ቢሏቸው፤ “እኔ አገር አቀናለሁ እንጂ አላጠፋም። እዚህ ድረስ የመጣሁትም ሃይማኖት ለማጥፋት አይደለም። ሁሉም ሰው እንደየ እምነቱ ያድራል።” ብለው ወደጀጎል በሰላም ሲሸኙዋቸው፤ ከነሱም ጋር እነበጅሮንድ አጥናፌ እና እነሻቃ ተክሌ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዘው ሀረር ገቡ። ከዚያ በኋላ አካባቢው በርግጠኝነት የኢትዮጵያ ግዛትነቱ ታውቆ፤ በአምስቱም የጀጎል በሮች ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንዲሰቀል ሆነ። 3ሺህ ወታደሮችም ከራስ መኮንን እንዲቀሩ አድርገው፤ ክልሉ እንደገና በኢትዮጵያ መንግስት ስር ይተዳደር ጀመር።
አጼ ምኒልክ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፤ የማረኩትን የግብጽ ወታደሮች አልገደሏቸውም። ይልቁንም ግብጾቹ የአሚር አብዱላሂን ጦር ለማበረታት ወታደራዊ ማርሽ ያሰሙ ነበር። አሁንም የምኒልክ ጦር በድል አድራጊነት ወደ አዲስ አበባ ሲገባ፤ አጼ ምኒልክ እነዚህኑ የጦር ሙዚቀኞች ታምቡር እያስመቱና ጥሩንባ እያስነፉ በወታደራዊ ስነ ስርአት አዲስ አበባ ሲገቡ ህዝቡ ግራና ቀኝ ተሰልፎ በታላቅ ደስታ እና እልልታ ተቀበላቸው። ያንጊዜ ታዲያ ማርከው ያመጡት ግብጾቹን ብቻ ሳይሆን፤ ለማዳ እርግቦች በሽቦ ቤት ያሉ እርግቦች እና ትላልቅ ሰሎግ ውሻዎች ጭምር ነበር። ያኔ ታዲያ እንዲህ ተባለ…
የምኒልክ ነገር፣ ይመስለኛል ተረት፤
አሞራው በቀፎ፣ ውሻው በሰንሰለት።
ይህ የሆነው የካቲት 28፣ 1879 ዓ.ም. ነው። እንግዲህ ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው እውነት ይህ ሆኖ ሳለ፤ የአካባቢው ሰዎች “ክልላችንን የጦር ካምፕ አደረጉብን” በማለት ምኒልክን እንደጨፍጫፊ እና ተስፋፊ ሲያዩ “እንቁላል ለመጥበስ መጀመሪያ ቅርፊቱን መስበር ያስፈልጋል” ከማለት ሌላ ብዙም የምንለው አይኖርም። ይልቁንስ ከአስር አመታት በፊት ይመስለናል… በዚሁ ኢቲቪ የተመከትነው አንድ ለቅሶ ነበር። ስለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል፤ ምኒልክ እና አሚር አብዱላሂ ጦርነት ያካሄዱበት ጨለንቆ ድረስ ሄደው፤ መሬቱን ቆፍረው የሟቾችን አጽም ከመቶ አመት በኋላ በማውጣት፤ “ምኒልክ የጨፈጨፏቸው…” ብለው ደረት እየመቱ ሲያለቅሱና ሲያስለቅሱ አይተን፤ “ወይ ታሪክ!?” ብለን ያለፍንበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።
በሱማሌ ክልል የተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እና በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰው ውርደት ምን ያህሉን ሰው እንዳበሳጨው ለማወቅ ያስቸግራል። እኛ ግን እንላለን… “የአካባቢው ሰዎች ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ወይም ታሪካችንን እና ማንነታችንን አያውቁም ማለት ነው። ሰው ሱማሌ፣ ኦሮሞ ወይም አማራ ስለሆነ አዋቂ አይሆንም። አገር እና ብሄር ሰውን አይለውጥም፤ ትምህርት ግን ሰውን ይለውጣል” ስለዚህ አሁንም ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለን የጋራ ታሪካችንን እንጨዋወት፤ በዚያው እንማማር፤ እንለወጥ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይህ አካባቢ ከጥንት ጀምሮ በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ተይዞ የነበረ ክፍለ ግዛት ነው። በ10ኛው ክፍለዘመን የሱማሌ ነገድ ከታጁራ ቤይ ተነስቶ መስፋፋት ሲጀምር የኦሮሞን ህዝብ እየተገፋ፤ በዋቢ ሸበሌ እና ጁባ ወንዝ መሃል በሚገኘው ቤናዲር በሚባለው ቦታ ላይ እንዲቆይ አድርጎት ነበር። በኋላም ኦሮሞዎቹን… ከታች የባንቱ ህዝብ ከላይ ሱማሌ ሲያስቸግራቸው ወደ ወላቡ፣ አበያ፣ ባሌ ድረስ ዘልቆ ራሱን በገዳ ስርአት እያደራጀ ቆይቶ፤ የግራኝ አህመድ ልጅ ወራሽ የሆነውን አሊ ኑርን ሐዘሎ ላይ ገጥሞ በ1551 ዓ.ም. እስከሚደመስሰው ድረስ በመሃል ብዙ ታሪኮች አልፈዋል። ከ10ኛው እስከ20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አካባቢው በዚህ አይነት ምስቅልቅል ውስጥ ነው የቆየው።
በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የነበረው ምስቅልቅል እንዳለ ሆኖ፤ በተለያዩ ጊዜያት ከሱማልያ ግዛት የጦር መሳርያ ይዘው በመግባት፤ የኦሮሞውን ህዝብ በመግደል እና ከብቱን በመዝረፍ፤ ህዝቡን በማፈናቀል ብዙ ግፍ ተሰርቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ክልል፤ በሌሎች ላብ እና ደም የተገነባ ክልል ነው። ይህን በማለት ወደኋላ ተመልሰን የምንቀይረው ነገር የለም። ሆኖም የማያውቁትን ወይም እያወቁ ሊያውቁ የማይፈልጉትን አንዳንድ ነገሮች ብናስታውሳቸው ክፋት የለውም።
በምኒልክ ዘመን ከተፈጠሩት አኩሪ ገድሎች መካከል የአድዋ ጦርነት አንደኛው ነው። ይህ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በድል ከተጠናቀቀ በኋላ፤ በጦር ተማራኪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ምኒልክ ዘንድ ምርኮኞችን አቀረቧቸው። ምኒልክ ምርኮኞች እንዲገደሉ አላደረጉም። ፈረንጅ ተማራኪዎችን ወደ አዲስ አበባ ይዘው ሲመለሱ፤ በኤርትራ እና በሱማሌ ተወላጆች ላይ ለየት ያለ ፍርድ ሰጡ። “ከአውሮፓ ወራሪ ጋር ሆነው የገዛ ወገናቸው ላይ ጥይት መተኮሳቸው ያሳዝናል። አሁንም ቀሪው ህዝብ እነሱን እያየ እንዲማር፤ ተንበርክከው የተኮሱበት ግራ እግራቸው እና ቃታ የሳቡበት ቀኝ እጃቸው ይቆረጥ።” ብለው ፈረዱ እንጂ አልገደሏቸውም።
ወደ አሁኑ የሱማሌ ክልል ልውሰዳቹህ። አካባቢው በ1879 ነጻ ከወጣ በኋላ ህዝቡ በሰላም መኖር ቢጀምርም፤ ኦሮሞዎቹ መሬት እና ከብታቸውን መነጠቃቸው ሊቆም አልቻለም። በወቅቱ የነበሩት የአካባቢው ኦሮሞዎች በተደጋጋሚ በሚደረግባቸው የድንበር ውጊያ ምክንያት ከብቶቻቸውን እየተዘረፉ፤ መሬታቸውን እየተነጠቁ፤ የሞቱት ሞተው፤ የቀሩት አካባቢውን እየለቀቁ ወጡ። ባለንበት ዘመን ደግሞ ሰዎቹን ብቻ ሳይሆን የሰጡትን ስያሜ ጭምር ሊቀይሩት ሲጥሩ ተመለከትን። ለምሳሌ “ጅጅጋ” ማለት በኦሮምኛ “ዝቅ ዝቅ” እንደማለት ነው (የአካባቢው ከፍታ ዝቅ ያለ በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው)። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ጅጅጋ” ማለታችውን ትተው “ጅግጅጋ” በሚል መጤ ስያሜ ለመቀየር እና አዲስ ስም ለመስጠት የሚሯሯጡ ሰዎችን ታዝበናል።
የቅርቡን ታሪክ ትተን… እንደገና ወደኋላ እንመለስ። ይህ ሁሉ ግፍ በኦሮሞዎቹ ላይ ሲሰራባቸው፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዝም አላሉም። ይልቁንም በራስ መኮንን አስተዳደር ወቅት… የሱማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦችን በሚያጣሉት የድንበር ቦታዎች ላይ በሙሉ፤ ነፍጥ የያዙ ወታደሮች ተመደቡ። በኋላ ክልሉን ለቀው ሊሄዱ ሲሉ፤ ህዝቡ እንቢ ብሎ መሬት እየሰጠ፤ ልጆቻቸውን እየዳሩላቸው ኑሯቸውንም እዚያው አደረጉ። እነዚህ ነፍጥ አንጋቾች ወይም ነፍጠኞች…. አብዛኛዎቹ ከሰሜን ሸዋ የተውጣጡ ጎበዝ አልሞ ተኳሾች ነበሩ። ሱማሌው እንደለመደው የኦሮሞውን ከብት እና እርሻ ለመዝረፍ ድንበር እያለፈ ሲመጣ፤ በጥይት እየለቀሙ ስርአት አስያዙት። የ85 አመት አዛውንት የሆኑት አቶ ሉልሰገድ ጎበና የሚነግሩን ቁም ነገር አለ… ቀደም ሲል በ1879 ምኒልክ ድል ሲያደርጉ እነሻቃ ተክሌን ሰንደቅ አላማ አስይዘው ወደሃረር መላካቸውን ተጨዋውተን ነበር። (የሻቃ ተክሌ ልጆች ደግሞ ፊታውራሪ ዝቅ አድርጌ እና ግራዝማች መኩሪያ ብዙ ታሪክ ያላቸው ጀግኖች ናቸው።) የሻቃ ተክሌ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ ናቸው – አቶ ሉልሰገድ። በወቅቱ ልጅ ነበሩ።
በአያታቸው ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ። የነገሩኝን ዝርዝር ታሪክ ሰብሰብ አድርጌ ላስነብባችሁ። እንዲህ አሉኝ… “በኋላ ላይ አያቴ ግራዝማች መኩርያ ተክሌ ወደ ጅቡቲ ድንበር አስተዳዳሪ ሆነው ተመደቡ። ከአፋሮች ጋር ጥሩ ወዳጅ ሆነው ነበር። ሱማሌዎቹ ተደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ ሲዘልቁ፤ አፋሮቹ መጥተው ይነግሯቸዋል። ከዚያም ግራዝማች ሱማሌዎቹን እየተከታተሉ ይቀጧቸው ነበር…” እኚህ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ኑሯቸውን እዚሁ አድርገው፤ እስከ2ኛ የጣልያን ወረራ ድረስ ዘልቀዋል። ከጣልያን ጦርነት በኋላ ኤጄርሳ ጎሩን አስተዳድረዋል። በዚህ አይነት ወልደው እና ከብደው የኖሩትን ሰዎች ነው ታድያ… ዛሬ በብሄር ብሄረሰቦች ሽፋን የሚሰድቧቸው።
“ክልላችንን የጦር ካምፕ አደረጉት” አልነበር የተባለው? እንግዲያው ሌላም ታሪክ እንጨምር። በ1953 ዓ.ም. በዋርዴር እና በገላዲን አካባቢ የሱማሌ ጦር በወገናችን ላይ ጉዳት ሲያደርስ፤ በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የ3ኛ ክፍለ ጦር አንድ ሻምበል ተንቀሳቅሶ ድል ተጎናጽፎ ነበር። በዚያው አመት ጄነራል አማን አምዶም ቡርበርዴን እና ቡክሲን አልፎ ሲመጣ… በጥቂት እግረኛ፣ መድፈኛ እና ፓራ ኮማንዶ ወታደሮች ወሰን አልፈው የመጡ የሱማሌ ወራሪዎችን ደምስሠዋል። ኢትዮጵያውያን በዚህ የኦጋዴን በርሃ የተሰዉት አካባቢውን የጦር ካምፕ ለማድረግ ሳይሆን ህዝቡን ከወራሪ ለመጠበቅ መሆኑን ለማወቅ ዲግሪ መጫን አይኖርብንም። በዚህ የምስራቁን ድንበር በማስከበር ላይ ከተሰማሩት ጀግኖች መካከል፤ በኦጋዴን በርሃ የእድሜውን ማምሻ የጨረሰውን ጀግናው አብዲሳ አጋን መጥቀስ ያስፈልጋል። የሱማሌ ባህል እና ብሄራዊ ማንነቱ እንደተከበረ ሆኖ፤ የኢትዮጵያውያን የህይወት መስዋዕትነት ሊዘነጋ አይገባም።
ዘንድሮ በሱማሌ ክልል የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር፤ ሌላውን ብሄር በመሳደብ ከሚከበር ይልቅ… ሌላው ብሄረሰብ ለዚህ ክልል ያደረገውን መልካም ነገር በማስታወስ፤ ታሪካቸውን በማወደስ… ሌላውን ኢትዮጵያዊ የሚያከብሩበትና የሚያመሰግኑበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆን ነበር። ይህ ግን ሳይሆን ቀረና፤ የትላንቱ ታሪክ ተረስቶ… ጆሯችን የስድብ ውርጅብኝ ለማዳመጥ በቃ።
እሩቅ ባልሆነው በትላንት ታሪካችን… አካባቢው በሱማሌ ወራሪ ሃይል ሲያዝ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ ስንብት እናደርጋለን። በወቅቱ የሱማሌ ጦር ከራሽያ ያገኘው የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ነበር። ይህን ሃይል በመያዝ በምስራቅ በኩል እስከ አዋሽ ያለውን የኢትዮጵያ መሬት ለመያዝ በቅተው ነበር። በገላዲን፣ በጅጅጋ፣ በደገሃቡር፣ በቀብሪደሃር፣ በጎዴ… እስከ ድሬዳዋ ድረስ የሱማሌ ጦር በምድር እና በአየር እየታገዘ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ወርሯል። ይህ ሁሉ ወረራ ሲደረግ ታዲያ… የሱማልያ ጦር ዝም ብሎ… መንገዱ አልጋ ባልጋ ሆኖለት አይደለም የገባው። በያንዳንዱ ግንባር የኢትዮጵያ ወታደሮችን እየገደለ፤ ሰላማዊ የሆነውን የአካባቢውን ነዋሪ እየጨፈጨፈ ነበር – ድሬዳዋ ድረስ የዘለቀው።
እነዚህን ሁሉ አካባቢዎች መልሶ በማጥቃት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። በአካባቢው የነበረው 3ኛ ክፍለ ጦር እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል የፈጸሙት ታላቅ ጀብዱ ምንግዜም በታሪክ የሚወደስ ነው። F-5 ተዋጊ ጀቶች ከደብረዘይት እየተነሱ የሱማሌን እግረኛ በመትረየስ ሲረመርሙት፤ እግረኛው የኢትዮጵያ ጦር ደግሞ ሱማሌውን እግር በ’ግር እየተከተለ መግቢያ ያሳጣው ነበር። ከአየር ኃይል አብራሪዎች መካከል እነሜ/ጄነራል አምሃ ደስታ፣ ሜ/ጄነራል ፋንታ በላይ፣ ኮ/ል አስማረ ጌታሁን የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ደምሴ ቡልቶ እና ሌሎች… ከምንም በላይ ደግሞ በዚህ ጦርነት ላይ ህይወታቸውን እና አካላቸውን ያጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ ለኢትዮጵያ ሲሉ ከየመን የመጡ መድፈኞች እና የኩባ ወታደሮች ጭምር፤ የከፈሉትን መስዋዕትነት ለአንድ አፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም – ክብር ለነሱ ይሁን።
ኦጋዴን እና አካባቢው “ራሴን አስተዳድራለሁ” ብሎ ስራ መጀመሩ ደስ ያሰኛል እንጂ፤ ማንንም አያስቆጣም። ነገር ግን አሁን ያለው አይነት ጥላቻ፤ የአንድ መጥፎ ነገር አመላካች ነው። ሌላው ኢትዮጵያ ለዚያ አካባቢ ህዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የማንሰጠው ከሆነ፤ በርግጥም ችግር አለ ማለት ነው። አንዳንድ የሱማሌ ኢትዮጵያ ሰዎች ሌላውን ብሄር እንዲህ የሚጠሉት ከሆነ፤ “ምናለበት ታላቂቱ ሶማልያ በገዛችን ኖሮ?” የሚል አንደምታን ይፈጥራል።
በኦጋዴን ወይም በሱማሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ሲከበር፤ በአካባቢው ያሉትን የኦሮሞ ተወላጆች በማቀፍ በልዩነት ውስጥ አብረው መኖራቸው እንደጥሩ ምሳሌ ማሳየት ይቻል ነበር። በብሄር ብሄረሰቦች በአል ሰበብ… ሌላውን ህዝብ ከመሳደብ ይልቅ፤ ስለመስዋዕትነቱ ማመስግን ምንም ክፋት የለውም። ህዝብን ማመስገን ባንችል እንኳን፤ ምናል አምላካችንን ብናመሰግን? አምላክን በትንሹ ማመስገን ካልቻልን ያለንን ያሳጣናልና ተመስገን ማለትን እንወቅበት።
የማመስገን ነገር ከተነሳ አንድ የስንብት ታሪክ እናውጋ።
እኚህ ሰው… በኢትዮ-ሶማልያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪ ነበሩ። በአየር ላይ ሆነው፤ የሱማሌ ተዋጊ ጀቶች ከፊት እና ከኋላ ሲመጡባቸው፤ በአየር ላይ እየተታኮሱ ቆይተው እሳቸው አቅጣጫቸውን ቀይረው ሲምዘገዘጉ፤ ሁለቱ የሱማሌ የጦር ጀቶች እርስ በርስ እንዲጋጩ አድርገው… ጸጥ አሰኝተዋቸዋል። እኚህ የአየር ኃይል አብራሪ በኋላ ላይ የሚያበሩት ጀት ተመትቶ እሳቸው በፓራሹት ወርደው ህይወታቸው ተረፈ። ሆኖም በሱማሌዎች መማረካቸው አልቀረም። ከሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በሱማሊያ እስር ቤት ለአስራ አንድ ከታሰሩ በኋላ ተፈቱ። በእስር ህይወታቸው ያጋጠማቸውን ነገር ሲያጫውቱን እንዲህ አሉ።
“የታሰርኩት በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ነው። እጅ እና እግሬ በካቴና ታስሯል። ከላይ ጣርያው ስለተሸፈነ የጸሃይ ሙቀትን እንጂ ብርሃኗን አይቼ አላውቅም። ወደውጭ የሚያወጡኝ ከጨለመ በኋላ በመሆኑ፤ ቀስ በቀስ የአይኔ ብርሃን ደከመ። እንዳልሞት ያህል ጥቂት ምግብ እና ውሃ ይሰጠኝ ነበር። በዚህ አይነት ለብዙ አመታት ስቆይ አምላኬን አማርሬው አላውቅም። አንድ ቀን ግን አምላኬን አማረርኩት። ‘ለምን እንዲህ ታሰቃየኛለህ?’ ብዬ በአምላኬ ላይ አዘንኩበት። የዚያኑ ቀን የነበርኩበትን እስር ቤት ለመጎብኘት አንድ የሱማሌ ወታደራዊ መኮንን መጣ። መኮንኑ እንደመጣ… እኔ ከጨለማው እስር ቤት እንድወጣ አዘዘ። ከዚያም እጅ እና እግሬ እንደታሰረ እሱ ፊት ቀረብኩ። የሱማሌው መኮንን እጅ እና እግሬ የታሰረበትን ሰንሰለት አይቶ ተቆጣ።”
“እንደዚህ አይነት ከፍተኛ እስረኛ እንዲህ ነው የሚታሰረው?” ብሎ አፈጠጠባቸው። አሳሪ ወታደሮች ግራ በመጋባት ዝም አሉ። እኔም አምላኬ ለቅሶዬን ሰማ። በእጆቼ እና በእግሬ ላይ የታሰረው ሰንሰለት ሊፈታልኝ ነው።” ብዬ ደስ አለኝ።
“የጦር መኮንኑ ቁጣውን ሳይቀንስ ሰንሰለቱን ፍቱ።” አላቸው። ከብዙ አመታት በኋላ ሰንሰለቱ ተፈታልኝ። የሱማሌው መኮንን አሁንም እየተቆጣ… “እንዲህ አይነት ከፍተኛ እስረኛ የሚታሰረው እንደዚህ ነው።” ብሎ… ቀኝ እጄን፣ ከቀኝ እግሬ ጋር፤ ግራ እጄን ደግሞ ከግራ እግሬ ጋር እንዲታሰር አዘዘ፤ እንደትእዛዙም ሆነ። በዚህ አይነቱ አዲስ አስተሳሰር… ቢያንስ ቆሜ እሄድ የነበርኩት ሰው አጎንብሼ ቀረሁ። በፊት እጅና እግር ለየብቻ በታሰሩበት ወቅት እንደልቤ እተኛ ነበር። አሁን ግን ለመተኛትም ተቸገርኩ። በፊት የነበረው አስተሳሰር ናፈቀኝ። ያንን ሁሉ አመት ስታሰር አንድም ቀን አምላኬን አማርሬው የማላውቀው ሰው፤ አሁን እርሜን አንድ ቀን ባማርር የባሰ ነገር መጣብኝ።” በማለት… ሰው ባለው ነገር ማመስገን እንዳለበት አስተምረውናል።
እኚህ በሱማሌ ጦርነት ወቅት ለአገራቸው ትልቅ ውለታ የሰሩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪ ታደለ ይባላሉ። (የአየር ኃይል ማዕረጋቸውን አላውቀውም) ከ11 አመታት እስር በኋላ ከሱማሊያ እስር ቤት ተፈትተው አገራቸው ከገቡት ኢትዮጵያዊ አንዱ ናቸው። ለ11 አመታት ብርሃን ባለማየታቸው የአይናቸውን ብርሃን ሊያጡ ተቃርበው፤ በህክምና ነገሮች ወደነበሩበት ተመልሰውላቸዋል።
እኚህ አብራሪ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ አንድ ልጅ ወለዱ፤ ስሙንም “በፀጋው” አሉት። ሃያ ምናምን አመታት ተቆጠረ። በፀጋው ታደለ ኢትዮጵያ አድጎ ለትምህርት ወደ አትላንታ መጥቶ፤ በታዋቂው ሞርሃውስ ዩኒቨርስቲ ሲመረቅ፤ ከትምህርት ቤቱ በሙሉ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገቡ፤ ድንቅ ተማሪ ተብሎ… ሁሉንም ተማሪ በመወከል ንግግር ያደረገው እሱ ነበር። በእለቱ እንግዳ ሆነው የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ንግግራቸውን ከመጀመራቸው በፊት፤ መምህራኑን አመሰገኑ። ለዚህ ኢትዮጵያዊ ወጣት አድናቆታቸውን ለገሱት።
ስለሱማሌ እስር ቤት አስከፊነት እና ስለጭካኔያቸው አቶ ታደለ ከማንም የበለጠ አደባባይ ወጥተው መናገር ይችላሉ። እሳቸው ግን ያለፈውን እንዳለፈ ትተው፤ አዲስ ህይወት በመጀመራቸው ራሳቸው ተከብረው፤ ሌላውን ኢትዮጵያዊ የሚያስከብር ልጅ ለትውልድ አስረከቡ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኦጋዴን ወይም የኢትዮጵያ ሱማሌ ከሽግግር መንግስቱ ግዜ ጀምሮ እስካሁን አስር የክልል ፕሬዘዳንቶች ተፈራርቀውባታል። ከነዚህ ፕሬዘዳንቶች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ እና ሶማልያ ጦርነት ወቅት የሶማልያ አየር ኃይል ባልደረባ የነበረና ኢትዮጵያን በአየር ሲደበድብ የነበረ ሰው ነው። አንበሳው የኢትዮጵያ ጦር ተጠናክሮ በመጣበት ወቅት… በፋፈም ሸለቆ በኩል አድርገው ወደ ሃርጌሳ ይሮጡ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፤ በብሄር ብሄረሰቦች በአል ሽፋን ሌላውን እየሰደቡት ነው። እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ ተግባር የማይደገም ስለመሆኑ ምንም ዋስትና የለንም። እነሱ ሌላውን ደገኛ፣ የመሃል እና የዳር አገር ሰዎች እያሉ የጥላቻ መርዝ ሲነሰንሱ፤ የኛ ጉልበታችን እውነትን መናገር ነው፤ ታሪክን ማስተማር ነው።
በመሆኑም በኦጋዴን ወይም በሱማሌኢትዮጵያ ክልል ውስጥ… ለአንደኛው ብሄር ወይም ለሌላው ሃይማኖት ሳይሉ… ለኢትዮጵያ ድንበር መከበር እና ለህዝቡ አንድነት ብለው የህይወት መስዋዕት ለከፈሉት ጀግኖች ሁሉ ኢትዮጵያዊ አክብሮት አለን። ስለነሱ ክብር… በጨዋ ኢትዮጵያዊነት ራሳችንን ዝቅ እናደርጋለን… እንደየእምነታችንም በህሊናችን እናስታውሳቸዋለን። እናም ክብር እና ማዕረግ ለነሱ ይሁን።

ሰማያዊ ፓርቲ በዲሲ ከተማ ያደረገው ሰብሰባ በከፊል

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል በአውሮፓ እና በአሜሪካ ላይ ፓርቲያቸውን በማስተዋወቅ ይገኛሉ :: ይህን አሰማልክቶ በዛሬው ቀን መስከረም 15 በዲሲ ከተማ ሰብሰባው በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ ተጠናቋል::

የቁጫ ነዋሪዎች መኖር አልቻልንም ሲሉ ምሬታቸውን ገለጹ

በጋሞጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ ከማንነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ መፍቴ አጥቶ እንደቀጠለ ባለበት ወቅት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን የአነጋግረናቸው የአገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል።
በዛሬው እለት በርካታ የአገር ሽማግሌዎች የጸጥታ ሀይሎች እያደረሱባቸውን ያለውን ስቃይ ለማስታወቅ በጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጽህፈት ቤትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢገኙም የሚያነጋግራቸው አጥተው ተመልሰዋል። አገር ሽማግሌዎቹ ጉዳያቸውን ለጠ/ሚንስተሩ ለማምልከት በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ ቢጓዙም እስካሁን የሚቀበላቸው  አላገኙም።
እንዲሁም ዛሬ ጠዋት ቀደም ብሎ ፍርድ ቤት በዋስ የለቀቃቸው ከ40 በላይ የከተማዋ ታዋቂ ሰዎች ተመልሰው በአርባ ምንጭ እስር ቤት እንዲታሰሩ ተደርጓል። የሽማግሌዎቹ መታሰር በወረዳዋ ሌላ ውጥረት መፍጠሩም ታውቋል።
ጠበቆች፣ መምህራንና በርካታ ፖሊሶች ከህዝቡ ጥያቄ ጎን እጃቸው አለበት በሚል ታስረዋል።በአካባቢው የተሰማራው የፌደራል ፖሊስ ህዝቡን በዘር በመለያየት ግጭት ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ፖሊሶቹ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ድበደባ እና የተለያዩ ስቃዮችን እየፈጸሙ መሆኑም ነዋሪዎች ገልጸዋል
በጉዳዩ ዙሪያ ወረዳውን ባለስልጣናት ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም

ከሳውድ አረቢያ ከሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ የመንግስት እንቅስቃሴ እየተተቸ ነው

ኢሳት ዜና :-የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የላችሁም በሚል ከሳዑዲዓረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ቁጥሩ መንግስት አስቀድሞ ካሰበው እጅግ አሻቅቧል፡፡ በዚህ ም ምክንያት ተመላሾቹን ለመቀበልና ለማቋቋም  መንግስት በቂ በጀት አለመያዙ እንደ አገር አሳፋሪ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
መንግስት የተመላሾቹ ቁጥር 23 ሺ ገደማ መሆኑንና እነዚህም ወገኖች ለመመለስ መመዝገባቸውን በመግለጽ ለተመላሾቹ 50 ሚሊየን ብር እንደመበ መግለጹ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ የተመላሾቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ከታወቀ በሁዋላ እንደገና መረጃውን በማሻሻል ተመላሾቹ ከ50 እስከ 80 ሺ እንደሚገመቱ ይፋ አደርጎአል፡፡ ይሁን እንጅ እስትናንት ድረስ ከ100 ሺ በላይ ሰዎች መመለሳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ከነዚህ መካከል 8 ሺህ የሚሆኑት ነፍሰ ጡር መሆናቸው ተገልጿል ፡፡
መንግስት ለተመላሾቹ 50 ሚሊየን ብር መመደቡን ከመግለጽ ውጪ መልሶ ለማቋቋም ምንም ያሰበው
ነገር አለመኖሩን የጠቀሱት ምንጮቹ  ተመላሾቹን ተቀብሎ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ማረፊያ ካቆየ በኃላ ክልሎች ስራ ይሰጡዋቹሃል በማለት እያባበለ ወደትውልድ አካባቢቸው እንዲሄዱ እያደረገ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡ተመላሾቹ  በሰው አገር መከራና ስቃይን ከማሳለፍ ባሻገር  ያፈሩትን ሐብትና ገንዘብ ይዘው መመለስ አለመቻላቸውን ያስታወሱት እነዚሁ ምንጮች በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉትንና  በተስፋ መቁረጥ የተጎዱትን ወገኖች በባዶ እጅ ወደ ቤተሰብ መስደድ እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል ፡፡

አለማቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት የሳውድ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ምርመራ እንዲያደርግና እርምጃ እንዲወስድ አሳሰበ

ኢሳት ዜና :-ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣው መግለጫ የሳውዲ የጸጥታ ሀይሎችና የሳውዲ ዜጎች በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሀይል እርምጃ በመውስድ ጉዳት አድርሰዋል። በኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የሳውድ አረቢያ መንግስት አስፈላጊውን  ምርመራ በማድረግ በአጥፊዎቹ ላይ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል ያለው ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በቶሎ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እስከዚያው በቂ ምግብ፣ መጠለያና የህክምና አገልግሎት እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
የሳውዲ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ዜጎች በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያጥላሉ ቅስቀሳዎች ይደረጉ እንደነበር ድርጅቱ አያይዞ ጠቅሷል።